FanaBC

On Jul 21, 2020 9,418

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት ዓባላት ቢሮ መሪዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዛሬው እለት ውይይት አካሂደዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተካሄደውን ስብሰባ መርተውታል።

በስብሰባው ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመትን ጨምሮ የቢሮው አባላት የሆኑት የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የማሊ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮችም ታድመዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ በደቡብ አአፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ አመቻችነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን ለማጠናከር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።

በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያም ቴክኒካዊ ውይይቶችን ቀጥሎ ለማካሄድ የጋራ መግባባት ላይ ለደረሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ለግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

የአፍሪካ ህብረት ዓባላት ቢሮ መሪዎች ባሳለፍነው ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ የመነጨ መፍትሔን ማበጀት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዛሬው ውይይትም ባሳለፍነው ሰኔ 19 የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ ነው የተካሄደው።

የአፍሪካ ህብረት ዓባላት ቢሮ መሪዎች እያካሄዱት ባለው ውይይት ላይም የሶስቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች እስካሁን ባደረጉት ድርድር ዙሪያ ያቀረቡትን ሪፖርት ተመልክቷል።

ሪፖርቱን ተከትሎ በተደረገው ውይይትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና የስራ ክንውን ዙሪያ የቴክኒክ ድርድሮችን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ቀጥሎ ለማካሄድ ከስምምነት መድረሳቸው ነው የተገለፀው።

#FBC