ከ 6 ሰአት በፊት

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የዱከም ከተማ ውስጥ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በኮሮናቫይረስ በተያዘ ግለሰብ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ 44 ሰዎች በኮሮናቫይረሰ መያዛቸው ተነገረ።
ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑት ከአርባ በላይ ሰዎች መካከል በሐዘን ላይ ያሉ የሟች የቤተሰብ አባላትን እንደሚጨምር የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጄ አብደና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለወረርሽኙ መተላለፍ ምክንያት የሆነው ግለሰብ ህይወቱ ያለፈው ባለፈው ሳምንት ባጋጠመው የመኪና አደጋ ሲሆን በአስክሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ ነበር የኮሮናቫይረስ እንደነበረበት የታወቀው።
ቢሆንም ግን በትራፊክ አደጋ የሞተው ወጣት የምርመራ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አስከሬኑ ለቤተሰብ ተሰጥቶ አስፈላጊው ዝግጅትና ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ እንዲቀበር ከተደረገ በኋላ ሟች አስከሬን ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ታወቋል።
ይህንንም ተከትሎ የሟች ቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች እና በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙና ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ ሰዎችን የመለየት እና ምርመራ የማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት እስከ ሰኞ ድረስ በንክኪ ምክንያት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ በተባሉ ሰዎች ላይ በተደረገው ልየታና ምርመራ መሠረት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 44 መድረሱን አቶ ደረጄ አብደና ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው ላለፉ ሰዎች በሚከናወን የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አማካይነት የሚከሰተው የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ለበሽታው መዛመት አመቺ አጋጣሚዎች እየሆኑ እንደመጡ አመልክተዋል።
በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች አስከሬን ጋር ከሚደረግ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ንክኪ ባሻገር በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስለሚገኙ ከሐዘኑ ታዳሚ ጋር በሚኖረው መቀራረብ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ለመተላለፍ እድል እንደሚያገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በቀብር ሥነ ሥርዓትና በማስተዛዘን ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች የሚታደሙ ከመሆናቸው ባሻገር ርቀትን መጠበቅና የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም አምብዛም ስለሆነ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን ከፍ እያደረገ ነው ብለዋል አቶ ደረጄ።
ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወረዳ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ አካባቢ በጥንቃቄ በጎደለው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተሳተፉ በርካታ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ መጋለጣቸው ይታወሳል።
በኮቪድ – 19 የሞተ ሰው የቀብር ሥነ- ሥርዓት እንዴት መፈጸም አለበት?

1. አዘገጃጀት
በአገራችን በሁለት ዓይነት ሁኔታ አስክሬን ለቀብር ይዘጋጃል፤ ይህም በህክምና ተቋማት እና ከህክምና ተቋማት ውጪ የሚከናወን መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በቅድሚያ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ እንዳለፈ በአቅራቢያ ለሚገኝ የጤና ተቋም ማሳወቅና የጤና ተቋሙ በአስከሬን አያያዝ ያሰለጠናቸውን ሰዎች በመላክ አስክሬኑ በጥንቃቄ መዘጋጀት አለበት።
በመሆኑም አስክሬኑን የሚያዘጋጀው ሰው የእጅ ጓንቶች፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲሁም ገዋን ማድረግ ይጠበቅበታል። አካባቢውንም በጸረ ተህዋስ ኬሚካል በመርጨት ማጽዳት ያስፈልጋል።
ሟች የተጠቀመባቸው ቁሳቁሶችና አልባሳት በበረኪና ወይም ኬሚካል ማጠብና መልሶ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ሌሎች ዕቃዎች ወይም ቁሳቁሶች በተመሳሳይ መልኩ ከጸዱ ማቃጠል ላያስፈልግ ይችላል።
2. አሸኛኘት
በኮቪድ-19 የሞተን ሰው አስክሬን ከማዘጋጀት በተጨማሪ የአስክሬን አሸኛኘት ዋናው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ሳያውቁ ከአስክሬኑ ጋር የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ንክኪ ሊፈጠሩ ይችላሉ።
ከዚህም ባሻገርም በቀብርና በሐዘን ሥነ ሥርዓት ወቅት ሰዎች ስለሚሰበሰቡ በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላው ሊተላለፍ ይችላል። በመሆኑነም አስክሬን የሚሸኙ ሰዎች ቁጥር እጅግ ማነስ ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና ጭምብል መጠቀም ያስፈልጋል።
3. የግብዓተ መሬት አፈጻጸም
አንድ በኮቪድ-19 የሞተ ሰው አስክሬን ከተዘጋጀና ከተሸኘ በኋላ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም ቀብሩን የሚከናውኑት ሰዎች ከሌሎች ጥንቃቄዎች ባሻገር ቢያንስ ጓንት ማድረግ አለባቸው።
በሐይማኖታዊም ሆነ በሌላ ምክንያት አስክሬኑ በሳጥን የማይቀበር ከሆነ በወረርሽኙ የሞተ ሰው በአስክሬን ሻንጣ (በላስቲክ ተጠቅልሎ )መቀበር አለበት።
በዚህ ሁኔታም ከሟቹ በድን አካል ላይ የሚመነጭ ፈሳሽ ለኖር ስለሚችል ጓንት፥ ተደራቢ ጋዎን እና ማስክና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።