20 ሀምሌ 2020

ክትባት

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተሰርቶ ሙከራ እየተደረገበት ያለው የኮሮናቫይረስ ክትባት የሰውነትን የመከላከል ሥርዓትን እንደሚያጎለብትና ደኅነነቱ የተጠበቀ መሆኑ ተገለፀ።

በክትባቱ ሙራ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት የተሳተፉ 1,077 ሲሆኑ የተሰጣቸው ክትባት ጸረ ተህዋሲ [አንቲቦዲ] እንዲያዳብሩና ነጭ የደም ህዋሳታቸው ኮሮናቫይረስን መከላከል እንዲችል ሆኗል ተብሏል።

የዚህ ምርምር ውጤት ግኝት በጣም ተስፋ ሰጪ የተባለ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ በሽታውን የመከላከያ አቅምን ለማግኘት በቂ መሆን አለመሆኑ ያልታወቀ ሲሆን ሰፊ ሙከራ እየተካሄደም ይገኛል።

ይህ ምርምር የተደረገው በቅድሚያ ክትባቱ ለበርካታ ሰዎች ቢሰጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ይሆናል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነው ተብሏል።

ክትባቱ የሚሰራው እንዴት ነው?

ይህ ባልተጠበቀ ፍጥነት የተሰራው ክትባት ሲኤችኤዲ0ኤክስ1 ኤንኮቪ-19 (ChAdOx1 nCoV-19) ይባላል።

የተሰራው ቺምፓንዚዎች ላይ ጉንፋን ከሚያስከትል ቫይረስ ዘረመል ተፈበርኮ ነው። ቫይረሱ በጥንቃቄ በላብራቶሪ ውስጥ የተሰራ ሲሆን በቅድሚያ በሰዎች ላይ ኢንፌክሽኖች እንዳያስከትል እንዲሁም ደግሞ “ኮሮናቫይረስ እንዲመስል” ተደርጓል።

በኮሮናቫይረስ ሰበብ ትኩረት የተነፈጉት የዓለማችን ገዳይ ችግሮች

ሩሲያ የኮሮናቫይረስ ክትባት መረጃዎችን ለመመንተፍ ሞክራለች መባሏን ውድቅ አደረገች

የሩሲያ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ምርምርን ኢላማ ማድረጋቸው ተነገረ

ተመራማሪዎች ይህንን ያደረጉት ኮሮናቫይረስ የሰው ልጅ ህዋሶች በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚጠቀምበትን የ”ስፓይክ ፕሮቲን” ጄኔቲክ መመሪያዎችን በመውሰድ ለሚያመርቱት ክትባት ተጠቅመው ነው።

ይህም ማለት ክትባቱ ኮሮናቫይረስን የሚመስል ሲሆን የመከላከል ሥርዓቱም እንዴት አድርጎ ማጥቃት እንዳለበት ይለማመዳል ማለት ነው።

ጸረ ተህዋሲዎችና ህዋሳት ምንድን ናቸው?

እስካሁን ድረስ ስለ ኮሮናቫይረስ ሲወራ ትኩረቱ በአብዛኛው ያለው አንቲቦዲዎች ላይ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ የመከላከያ ኃይላችን አንድ ክፍል ብቻ ናቸው።

አንቲቦዲዎች ትንንሽ ፕሮቲኖች ሲሆኑ የተሰሩትም ቫይረሱ ላይ በሚጣበቁት የመከላከል ሥርዓታችን ነው።

አንቲቦዲዎችን እንዳይሰሩ ማድረግ ከተቻለ ኮሮናቫይረስን እንዳይሰራ ያደርገዋል።

ቲ ሴል ደግሞ የነጭ የደም ሴሎች ዓይነት ሲሆኑ፤ የመከላከል ሥርዓታችንን በማስተባበር እና የትኞቹ ህዋሶች እንደተጠቁና እንደወደሙ ለመለየት ያገለግላሉ።

ሁሉም ውጤታማ የሆኑ ክትባቶች አንቲቦዲን እና ቲ ሴልን ምላሽ ያካተቱ ናቸው።

የቲ ሴሎች ቁጥር ክትባቱን ከወሰዱ ከ14 ቀናት በኋላ ከፍ ያለ ሲሆን የአንቲቦዲዎች ደግሞ ከክትባቱ ከወሰዱ ከ28 ቀን በኋላ ከፍ ብሎ ታይቷል።

ምርምሩ የረዥም ጊዜ የመከላከል አቅም ምን እንደሚመስል ለመለየት በቂ ጥናት አላደረገም።

ደህንነቱ የተጠበቀ ነው?

አዎ፤ ነገር ግን የጎንዮሽ ጉዳት አለው።

ክትባቱን በመውሰድ የሚመጣ አደገኛ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት የለውም፤ ነገር ግን ክትባቱን ከወሰዱ 70 በመቶ ያህል ሰዎች ትኩሳት አልያም ራስ ምታት አዳብረዋል።

ተመራማሪዎቹ ይህ ደግሞ በፓራሳታሞል የሚድን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ሳራ ጊልበርት “ክትባታችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ያገለግላል ከማለታችን በፊት በርካታ ሥራ መሰራት አለበት፤ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው” ብለዋል።

ክትባቱ ውጤታማ ሆኖ ለአገልግሎት የሚበቃ ከሆነ ዩናይትድ ኪንግደም አስቀድማ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን አዛለች።

የምርምሩ ቀጣይ ሥራ ምንድን ነው?

እስካሁን ድረስ ያለው የክትባቱ ምርምር ውጤታማ ነው። ነገር ግን ክትባቱ ለሌሎች ቢሰጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ጥናቱ እስካሁን ድረስ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንዳይታመሙ ይከላከላል ወይስ በኮቪድ-19 ቢያዙ የሚያሳዩትን ምልክት ይቀንሳል የሚለውም አልታወቀም።

በዩናይትድ ኪንግደም ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በሚቀጥለው ሙከራ ላይ ይሳተፋሉ።

ይሁን እንጂ ሙከራው ወደ ሌሎች አገራትም እየተስፋፋ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ነው የተባለው በዩናይትድ ኪንግደም ያለው የቫይረሱ ስርጭት መጠን እየቀነሰ በመሆኑ የክትባቱ ውጤታማነትን ለማወቅ አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ነው።

በአሜሪካ 30 ሺህ ሰዎች፣ በደቡብ አፍሪካ 2000 ሰዎች እንዲሁም በብራዚል 5000 ሰዎች የሚሳተፉበት ሙከራ ይደረጋል።

ከዚህ በኋላም “ተግዳሮታዊ ሙከራ” በመባል የሚታወቀው የምርምር ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን በዚህም ወቅት ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች ሆን ተብሎ በኮሮናቫይረስ እንዲያዙ ይደረጋሉ። ምንም እንኳ መድኃኒቱ ስላልተገኘ የሙያ ሥነ ምግባር ጥያቄ ቢነሳም ይህ ግን መከናወኑ አይቀርም ተብሏል።

ክትባቱን መቼ አገኛለሁ?

ከተሳካ የኮሮናቫይረስ ክትባት ውጤታማ መሆኑ የሚረጋገጠው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ነው። ነገር ግን ለሕዝብ በስፋት ጥቅም ላይ በዚህ ወቅት አይውልም።

የጤና ባለሙያዎች ባላቸው የሥራ ሁኔታና ተጋላጭነት፣ በእድሜ በመለየት ክትባቱን በቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል።

ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር በእቅዱ መሰረት ከሄደ ክትባቱ ለተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ቦሪስ ጆንሰን እንዳሉት “በጣም ተስፋ አለኝ፣ ነገር ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ በዚህ ዓመት ወይንም በሚቀጥለው ዓመት ክትባቱን እናገኛለን ማለት ማጋነን ነው። ገና እዚያ አልደረስንም” ብለዋል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ክትባት እዚህ ደረጃ ሲደርስ የመጀመሪያው አይደለም።፤ በቻይናና በአሜሪካ የሚገኙ የተመራማሪዎች ቡድኖችም ተመሳሳይ ውጤት ለህትመት አብቅተዋል