23 ሀምሌ 2020, 15:15 EAT

ባሕላዊ መድኃኒቶች
የምስሉ መግለጫ, በአፍሪካ ውስጥ የተለያዩ ባሕላዊ የኮቪድ-19 መድኃኒቶች እንዳሉ ቢነገርም ፈዋሽነታቸው ግን አልተረጋገጠም

ለኮሮናቫይረስ የሚሆን መድኃኒትን ከባሕላዊ መድኃኒቶች ለማግኘት የሚደረግ ጥረትን የሚደግፍና የሚያማክር ኮሚቴ በዓለም ጤና ድርጅት እና በአፍሪካ የበሽታ መከላከያ ማዕከል አማካይነት ተቋቋመ።

በኮሚቴው ውስጥ የሚሳተፉት ባለሙያዎች የአፍሪካ አገራት ባሏቸው ባሕላዊ መድኃኒቶች ዙሪያ በሳይንስ፣ ደኅንነታቸውን የተጠበቀ በማድረግና በጥራት በኩል እንደሚያማክሩ ተገልጿል።

ይህ ባሕላዊ መድኃኒቶችን ለኮሮናቫይረስ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፈው ኮሚቴ አገራት በመድኃኒቶቹ ላይ በሚያደርጉት ሙከራ ወቅት አስፈላጊውን ዓለም አቀፋዊ የጥራት ደረጃዎችን የጠበቁ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ከዓለም ጤና ድርጅት የወጣው መግለጫ ገልጿል።

“ዓለም ለኮሮናቫይረስ የሚሆን የመከላከያ ክትባት እና የፈውስ መድኃኒት ለማግኘት በምትጥርበት ወቅት፤ በባሕላዊ ህክምናው ዘርፍ ያለውን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ሳይንስን መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል” ሲሉ የአፍሪካ አካባቢ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ማሲዲሶ ሞይቲ መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ይህ የባለሙያዎች ኮሚቴ የተመሰረተው ከተለያዩ እጸዋት ተዘጋጀውን የኮቪድ-19 መድኃኒት ነው በማለት በስፋት ስታስተዋውቅ የነበረችው ማዳጋስካር በበሽታው የተያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን ማግኘቷን ተከትሎ ነው።

በዚህ በማዳጋስካር ተገኘ በተባለው የኮሮናቫይረስ መድኃኒት ላይ የናይጄሪያ ተመራማሪዎች ፍተሻ አድርገው በእርግጥ ወረርሽኙን የመፈወስ ይዘት ማግኘት እንዳልቻሉ በዚህ ሳምንት አሳውቀዋል።

የማዳጋስካሩ ፕሬዝደናት ሳይቀሩ ስለመድኃኒቱ ፈዋሽነት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው ተደጋጋሚ ማብራሪያ የሰጡ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ የአገሪቱ ምክር ቤት እንደራሴዎች በበሽታው መያዛቸውና ሁለት ደግሞ መሞታቸው የመድኃኒቱን ነገር ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ወረርሽኙ በሕዝቡ ውስጥ ተዛምቶ በየዕለቱ በርካታ ማዳጋስካራዊያን በበሽታው መያዛቸው ከመነገሩ በተጨማሪ የህክምና ተቋማት እየጨመረ በሚሄድ ከአቅማቸው በላይ በሆነ የህሙማን ቁጥር እየተጨናነቁ ነው ተብሏል።