July 25, 2020

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) ዳግማዊ አፄ ምኒልክ “ውሃ ለጎረቤታችን አንከለክልም” እንጂ “ውሃ አንጠቀምም” የሚል ስምምነት አለመፈረማቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በኤዥያና ኦሺኒያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ባለሙያዎች ጋር የዌብናር ኮንፍረንስ አካሂደዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በዓባይና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉት ድርድር ያለ ስምምነት ሲበተን ዋል አደር ብሏል።

ድርድሩ በሶስቱ አገራት ተጀምሮ አሜሪካን አቋርጦ የጸጥታው ምክር ቤትን አልፎ ቢሄድም በኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ወደ አፍሪካ ኅብረት መጥቷል።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚሉት ግብፅ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር 1929 እና 1959 የተፈረመውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ማስቀጠል ትፈልጋለች።

ከዚህም አልፎ ግብፅ እንደ አውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1902 ዳግማዊ አፄ ምኒልክ “ውሃ አንጠቀምም” ብለዋል የሚል የሃሰት ትርክት እያስተጋባች መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተጀመረ ቢሆንም ግብፆች በተሳሳተ መንገድ ተርጉመው ለዓለም እያስተዋወቁት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በወቅቱ የተደረገው ስምምነት “ውሃ ለጎረቤታችን አንከለክልም” እንጂ “ውሃ አንጠቀምም” የሚል አልነበረም ብለዋል ፕሮፌሰር ያፅቆብ።

ይህ በግብፅና በደጋፊዎቿ የሚስተጋባ የተለመደ ማደናገሪያ እንጂ ቀሪው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት አያውቅም ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ስታደርገው የነበረውና ወደፊትም የምታደርገው ድርድር ብሔራዊ ጥቅሟን በማይነካ መንገድ እንደሚሆን በመግለጽ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ አሁንም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር ቀይ መስመሩን አልፎ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ከሆነ እንዲቋረጥ ይደረጋል።

ድርቅን ለመቋቋም፣ ድህነትን ለማጥፋትና እድገት ለማምጣት ምክንያታዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በትብብር መተግበር ነገም ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።

ግብፅ ውሃን የልማትና የጋራ ተጠቃሚነት አጀንዳ ማድረግ ሲገባት የደህንነት ጉዳይ ማድረጓ አሁን ካለችበት ግትር አቋም እንዳትንቀሳቀስ አድርጓታልም ነው ያሉት።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ አቶ ዘርሁን አበበም ግብፅ የያዘችው የምትነዛው ፕሮፖጋንዳና የሀሰት ትርክት አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል ይላሉ።

ዓባይን በጋራ ከማልማት ይልቅ በብቸኝነት መቆጣጠር አለብን ከሚል እብሪት በሕገ መንግስቷ እስከማካተት መድረሷን በመጥቀስ።

https://www.ena.et/?p=96149