25 ሀምሌ 2020, 11:27 EAT

የባርያ ንግድ በዘረ መል ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ጥናት ይፋ ተደረገ

ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ያሳተፈ አንድ ትልቅ የዘረ መል ምርምር ተካሂዷል። ጥናቱ፤ ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በባርያ ንግድ ከአፍሪካ ለአሜሪካ የተሸጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተመለከ አዲስ መረጃ አስገኝቷል።

የባርያ ንግድ አሁን ባለው የአሜሪካውያን የዘረ መል መዋቅር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ጥናቱ ያመለክታል።

ጥናቱ የመደፈር፣ የመሰቃየት፣ የበሽታ እና የዘረኝነትን ጫና ያሳያል።

ከ1515 እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ከ12.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ተሸጠዋል።

ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች፣ ወንዶችና ሕፃናት ወደ አሜሪካ እየተወሰዱ ሳለ ሕይወታቸው አልፏል።

የዘረ መል ምርምሩ የተካሄደው ‘23ኤንድሚ’ በተባለ ድርጅት ነው። በ ‘አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ሂውማን ጄነቲክስ’ መጽሔት የታተመው ጥናት፤ ከሁለቱም የአትላንቲክ ክፍሎች አፍሪካዊ የዘር ሀረግ ያላቸውን 30 ሺህ ሰዎች አካቷል።

የማሕበረሰብ ዘረ መል ተመራማሪው ስቲቨን ሚሼሌቲ ለኤኤፍፒ እንዳሉት፤ የሚያገኙትን የዘረ መል ውጤት ከባርያ ንግድ መርከቦች ጋር ለማነጻጸር አቅደው ነበር ጥናቱን የጀመሩት።

አብዛኛው ግኝታቸው ከታሪካዊው ሰነዶች ጋር ይጣጣማል። ሰዎች ከየትኛው የአፍሪካ አካባቢ እንደተወሰዱ እና አሜሪካ ውስጥ የት ለባርነት እንደተዳረጉ ከሚያሳዩ ሰነዶች ጋር አብዛኛው ውጤታቸው ተመሳሳይ ነው።

ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ግኝቶቻቸው ከታሪካዊው ትርክት ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዳላቸው ተመራማሪው ይናገራሉ።

ብዙሃኑ የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸው አሜሪካውያን መነሻቸው የዛሬዎቹ አንጎላ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። ይህም ዋነኛው የባርያ ንግድ መስመር ነው።

ከሰዎች ብዛት አንጻር፤ የዘር ሀረጋቸው ከናይጄሪያ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ በአሜሪካ እና በላቲን አሜሪካ የተጋነነ ትርክት እንዳለ ጥናቱ ጠቁሟል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ የዚህ መረጃ መነሻው በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1619 እስከ 1807 የነበረው የባርያ ንግድ ነው። ናይጄርያውያን ከካረቢያን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይሸጡ ነበር።

“ምናልባትም የአትላንቲክ የባርያ ንግድን የተመረኮዘውን ምጣኔ ሀብት ማስቀጠል ስለተከለከለ ሊሆን ይችላል” ይላሉ ተመራማሪው።

በሌላ በኩል የሴኔጋል እና የጋምቢያ ተወላጆች ቁጥር በርካታ መሆኑ በታሪክ አለመታየቱ ተመራማሪዎቹን አስገርሟል። እነዚህ አገሮች የባርያ ንግድ ከተጀመረባቸው መካከል ናቸው።

ተመራማሪዎቹ ይህንን በተመለከተ ሁለት እውነታዎች ላይ ደርሰዋል። አንደኛው አብዛኞቹ ሰዎች በሩዝ እርሻ እንዲሠሩ መደረጋቸው ነው። ቦታው ወባ የተስፋፋበትና አደገኛም ነበር።

በቀጣይ ዓመታት ወደዚህ አካባቢ የተላኩት በርካታ ሕፃናት በሕይወት መትረፍ አልቻሉም።

ጥናቱ እንደሚያሳው፤ በባርነት የተሸጡ ሴቶች በአሜሪካ ይደርስባቸው የነበረው ስቃይ አሁን ባለው የዘረ መል መዋቅር ላይ ጫና አሳድሯል።

አብዛኞቹ በባርነት የተሸጡት ወንዶች ነበሩ። ሴት አፍሪካውያን ይደረስባቸው የነበረው መድልዎ ዛሬ ያለው የዘረ መል መዋቅር ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ተመራማሪዎቹ ለዚህ ምክንያቱ በባርነት የተሸጡ ሴቶች መደፈራቸው፣ ለበርካታ ወሲባዊ ጥቃት መጋለጣቸውም ነው ይላሉ።

በላቲን አሜሪካ 17 አፍሪካውያን ሴቶች ከአንድ አፍሪካዊ ጋር መጣመራቸው ለዘረ መል መዋቅሩ መለወጥ ምክንያት መሆኑን አጥኚዎቹ ይናገራሉ።

ለዚህ ምክንያቱ ‘ብራንክውሜንቶ’ የተሰኘው ጥቁሮችን ነጣ ወዳለ የቆዳ ቀለም የመለወጥ ፖሊሲ ነው። “በርካታ አውሮፓውያን በግብረ ሥጋ ግንኙነት አፍሪካዊ የዘር ግንድ ያላቸው ሰዎችን የቆዳ ቀለም እንዲለውጡ ተደርጓል” ይላሉ ተመራማሪው።

በብሪትሽ ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችው አሜሪካ ሁለት አፍሪካውያን ሴቶች ከአንድ አፍሪካዊ ጋር ያጣመራሉ የሚለው ትርክትም ሴቶችን የሚበዘብዝ ነበር።

የአትላንቲክ የባርያ ንግድ ሊቆም ሲል፤ በባርነት የተሸጡ ሰዎች ልጅ እንዲወልዱ በማስገደድ፤ ባርያ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት እንደነበረ ጥናቱ ያሳያል።

አሜሪካ ውስጥ ሴቶች ከወለዱ ነፃ እንደሚወጡ ቃል ይገባላቸው ነበር። ዘረኛው ፖሊሲ አንድ ዘር ከሌላው ጋር እንዲቀላቀል አይፈቅድም ነበር።

ለጥቁሮች መብት የሚታገለው ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ንቅናቄ የባርያ ንግድ እና ቅኝ ግዛት በጥቁር አሜሪካውያን እንዲሁም በመላው ዓለም ባሉ ጥቁሮች ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ አጉልቶ ያሳያል።

በቅኝ ግዛት ዘመን በባርያ ንግድ የተሳተፉ ሰዎች ሀውልቶች እንዲነሱ የሚጠየቀውም ለዚሁ ነው። የባርያ ንግድ ምልክት የሆኑ ሰዎችን ማሞገስ ያክትም የሚለው እንቅስቃሴም ቀጥሏል።