በሁከት ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች የት እንዳሉ ቤተሰቦች እንደማያውቁ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

26 July 2020

ዮሐንስ አንበርብር

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሳምንታት ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የሚገኙበትን ቦታ ቤተሰቦቻቸው በተሟላ ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳዮችን ገምግሞ ዓርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ተሳትፈዋል ተብለው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተያዙ ሰዎች ያሉበትን ቦታ፣ ቤተሰቦቻቸው በተሟላ ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻሉ መረዳቱን አስታውቋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ታሳሪዎች በሚመለከት ኮሚሽኑ በቅርቡ ለመመልከት በዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት፣ በርካታ ታሳሪዎች ያሉበትን ቦታ ቤተሰቦቻቸው በተሟላ ሁኔታ ያላወቁ ስለመሆኑ ጥቆማ እንደ ደረሰው ገልጿል።

በተለይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አመራሮችን ጨምሮ በርካታ አባሎቻቸው መታሰራቸውንና ያሉበትን ቦታና ሁኔታ ለማወቅ አለመቻላቸውን፣ ለኮሚሽኑ ማስታወቃቸውን አመልክቷል።
 

በመሆኑም ሁሉም ታሳሪዎች ለቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ በስልክ እንዲያስታውቁ እንዲደረግ፣ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ማቅረቡንና አፈጻጸሙንም እንደሚከታተል አስታውቋል።

በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የፖሊስ ኮሚሽን አባላት በቁጥጥር ሥር የሚያደርጓቸውን ታሳሪዎች ወዲያውኑ ለቤተሰባቸው ያሉበትን ቦታ በስልክ እንዲያሳውቁ ሊደረግ እንደሚገባም፣ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል።

ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ባለው የሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ሊያከናውኑ የሚገባው ጉዳይ፣ ሁሉም ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ በማናገር ያሉበትን ቦታ ማሳወቃቸውን ማረጋጥና በተፋጠነ ምርመራ በዋስትና መብት ወይም በነፃ ሊፈቱ የሚገባቸውን ታሳሪዎች በመለየት፣ በአፋጣኝ መለቀቃቸውን ማረጋገጥ ነው፤›› ማለታቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወሰው ኮሚሽኑ፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታም ኮሚሽኑ ሥልታዊ ክትትል እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።

በዚህ ረገድም እስካሁን እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋና  ይልቃል ጌትነት (ኢንጅነር)ን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ በተከታታይ እንደተከታተለ አስታውቋል፡፡

 በተለይም እነ አቶ ጃዋር መሐመድና እስክንድር ነጋ በመጀመርያ ላይ ታስረው ይገኙ የነበረበትን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ያለውን እስር ቤት፣ እንዲሁም አሁን የሚገኙበትን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኘውን እስር ቤት፣ በተጨማሪም በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን ጊዜያዊ የእስር ቤት ኮሚሽኑ ጎብኝቶ ታሳሪዎችንና ኃላፊዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።

ኮሚሽኑ የእነ አቶ እስክንድር ነጋ የእስር አያያዝ ጎብኝቶ እንዲሻሻሉ ብሎ ባቀረበቸው ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ መደረጋቸውን፣ እንዲሁም ከነገሩ ሁኔታ አንፃር በዋስትና መብት ሊለቀቁ ስለሚገባቸው የተወሰኑ ታሳሪዎች የሰጠው ምክር ሐሳብም በሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተግባራዊ መደረጉን በመልካም ዕርምጃነቱ ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡

በቅርቡ ባደረገው ድጋሚ ክትትል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋና አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ ስድስት ታሳሪዎች አሁን የሚገኙበት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኘው እስር ቤትም ንፅህናው የተጠበቀ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚያገኝ፣ ታሳሪዎቹ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከቤተሰብ አቅርቦት የሚቀበሉበትና ለመተያየት የሚችሉበት እንደሆነ አስታውቋል።

በአጠቃላይ የእነዚህ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ግለሰቦች አያያዝ ተቀባይነት ባለው ደረጃ  መሆኑን፣ በተወሰነ ሁኔታ ከወቅቱ የአየር ፀባይና ከሕንፃው ባህሪ የተነሳ የመቀዝቀዝ ፀባይ ያለው በመሆኑ ቅዝቃዜውን ለመቀነስ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን እንዳስተዋለ መግለጫው ያስረዳል፡፡

በዚህ እስር ቤት ካሉት ታሳሪዎች ውስጥ አቶ ሐምዛ ቦረናና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ የሕክምና ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ፣ አቶ ሐምዛ ከኮሚሽኑ ጉብኝት ማግሥት ወደ ሕክምና እንደሄዱ፣ አቶ ሸምሰዲንም በአፋጣኝ የሕክምና ጉብኝት እንደሚያገኙ እንዳረጋገጠ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ከታሳሪዎች መጠነኛ ቅሬታ መቅረቡን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ካቀረቡት ቅሬታ ውስጥ ከቤተሰብ ጋር በተገቢው መጠን ተቀራርቦ ለመተያየት አለመቻላቸውና የክፍሎቹ መቀዝቀዝ፣ የፀሐይ መቀበያ ጊዜ ማጠር፣ የመብራት መቋረጥ፣ የታሳሪዎች ለረዥም ጊዜ ለብቻ መቆየትና የመሰሉ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሷል።

እነዚህ ችግሮች ሊሻሻሉ ስለሚችሉበት መንገድ ኮሚሽኑ ከኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ያደረገ መሆኑንና አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታተለው አስታውቋል።  በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ታሳሪዎች ውስጥ የኦኤምኤን ጋዜጠኞች የነበሩ አቶ ጉዮ ዋርዮና  አቶ ሙሐመድ ሲራጅ፣ የኦፌኮ አባል አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ እንዲሁም ሦስት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችና በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠለፋ ጉዳይ ተጠርጥረው የተከሰሱ ታሳሪዎችን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችንም ኮሚሽኑ መጎብኘቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች በእስር ወቅትም ሆነ ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያው ከመጡ ጀምሮ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳልተፈጸመባቸው፣ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያው ውስጥ የእስር አያያዙ በአጠቃላይ አነጋገር መልካም ቢሆንም በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አንፃር ከፍተኛ አሥጊ ሁኔታ መኖሩን አመልክቷል።

የንፅህና መጠበቂያና የመከላለያ ቁሶች አቅርቦት እጥረት መኖሩን፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው እያደገ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ሥጋት እንዳሳደረባቸው ከእስረኞቹ መረዳቱን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የተወሰኑ ታሳሪዎች ገና ከቤተሰብ ጋር ያልተያዩ መሆናቸውንና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ታሳሪዎችም በውጭ አገር የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ለማነጋገር ዕድል አለማግኘታቸውን ባደረገው ጉብኝት መረዳቱን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣  ዘግይቶም ቢሆን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ታሳሪዎች ከአገራቸው ኤምባሲ ኃላፊዎች ጋር መገናኘት እንደቻሉ አመልክቷል።

አንድ ታሳሪ በእስር ወቅት ፖሊስ ተገቢ ያልሆነ እንግልት እንደፈጠረባቸውና በጥፊና በእርግጫ  እንደመታቸው፣ እንዲሁም ሁለት ታሳሪዎች በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ውስጥ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት አጠቃላይ ሁኔታው አስፈሪና አስጨናቂ እንደነበር፣ እንዲሁም በቁጥጥር ሥር በዋሉበት የመጀመርያው ቀን ምሽትና አዳር ያለ ምግብ፣ ውኃና ያለ ብርድ ልብስ ኮሪደር ላይ ለማሳለፍ መገደዳቸውን ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ገልጿል፡፡

በአንፃሩ በቁጥጥር ሥር ከዋሉና በተለይም አሁን ወደሚገኙበት ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ከመጡ በኋላ የእስር አያያዙ የተሻሻለ መሆኑን፣ ፖሊሶቹም በከፍተኛ የሙያ ሥነ ምግባር የሚሠሩ መሆናቸውን ከታሳሪዎቹ እንደተገነዘበ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በተማሪዎች እገታ ጉዳይ ተጠርጥረው ከታሰሩት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በኦሮሚያ ክልል ደምቢዶሎ ከተማ ታስረው በቆዩበት ወቅት፣ የተማሪዎቹን ጠላፊዎች ታውቃላችሁ በሚል ጥርጣሬ በተደጋጋሚ እንደተደበደቡ፣ እንደተገረፉ፣ በሽጉጥ የማስመሰል ግድያ (Mock Execution) እንደተፈጸመባቸው እንደገለጹለት ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል። በአንፃሩ ወደ አዲስ አበባ የፌዴራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ከመጡ ጀምሮ ምንም ዓይነት ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳልተፈጸመባቸው፣ በአጠቃላይ የእስር አያያዛቸው መልካም እንደሆነ ከራሳቸው መረዳቱን አስታውቋል፡፡

ነገር ግን ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለት ታሳሪዎች ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ እስከ ጉብኝቱ ቀን ድረስ አለመለቀቃቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡  

ኮሚሽኑ በተለይም የተወሰኑት ታሳሪዎች በኦሮሚያ ክልል ደምቢዶሎ ከተማ እስር ወቅት፣ ተፈጽሟል የተባለውን ድብደባና የማሰቃየት ድርጊት እንደሚያጣራም አስታውቋል፡፡  በአብዛኞቹ ታሳሪዎች የተነሳው ሌላው ተደጋጋሚ ቅሬታ የወንጀል ምርመራ የሚወስደው ጊዜ፣ ብዙ ታሳሪዎች ገና ቃላቸውን ያልሰጡና መርማሪ ፖሊስ ያላናገራቸው መሆኑ፣ በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መሆኑን ታሳሪዎቹን አነጋግሮ መረዳቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ እንደተገነዘበው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት እጅግ ውስን በሆነ የሰውና የፋይናንስ አቅም በርካታ ጉዳዮችን በማጣራት ከፍተኛ የሥራ ጫና ያለባቸው ቢሆንም፣ በተቻለ መጠን የምርመራ ሥራውን ማቀላጠፍና በዋስትና መብት ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች በአፋጣኝ መለየት ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል፡፡

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ሁኔታ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምርመራ ሥልት ላይ ተመሥርቶ፣ በበቂ ማስረጃዎች የተደገፈ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ዓይነት በተገቢው መጠን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን አዋቅሮ ወደ ሥራ ማሰማራቱንም አስታውቋል።