26 ሀምሌ 2020

አቶ ዳውድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ-መንበር የሆኑት የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት በፌዴሬል ፖሊስ መከበቡን የፓርቲው ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዳ ኦልጅራ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ ገዳ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት አካባቢ የሚገኘው የጸጥታ ኃይል የሊቀመንበሩን ደኅንነት ለመጠበቅ መሰማራቱን ከፖሊስ መስማታቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት መከበብን ለቢቢሲ ያረጋገጡት አቶ ገዳ የታጠቁ ኃይሎች በመኖሪያ ቤቱ ዙሪያ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።

ኃላፊው፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያ ቤታቸው መውጣትና መግባት እንዳልቻሉና ወደ ውጪ የሚወጡ ከሆነም በጸጥታ ኃይሎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ስጋተቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አቶ ገዳ ከሦስት ቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ከአንድ ቀን በኋላ መፈታታቸውን ገልጸዋል።

“ዋና ሊቀመንበራችን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት። እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው የዕለተ ዕለት ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም” ሲሉ አቶ ዳውድ ከቤታቸው መውጣት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አቶ ገዳ እንደሚሉት አቶ ዳውድ ብቻ ሳይሆኑ በቤታቸው ውስጥ ያሉ የቤተሰባቸው አባላትም ከመኖሪያ ግቢው መውጣትናም ሆነ ከውጪ መግባት ተከልክለዋል።

አቶ ገዳ ካሉት የእንቅስቃሴ ገደብ በተጨማሪ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ስልክ ከሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ እየሠራ አይደለም።

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት ለምን እንደተከበበ የሚያውቁት ነገር አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ገዳ፤ ፖሊስ ይህን ያደረገው ለእሳቸው [አቶ ዳውድ] ደኅንነት ሲባል እንደሆነ ተነግሮኛል ይላሉ።

ይሁን እንጂ “ሰው እንዳይገባና እንዳይወጣ እየከለከሉ ደኅንነት ለመጠበቅ አይመስልም” ይላሉ። “የአቶ ዳውድ ስልክ ስለማይሰራ ከራሳቸው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ከሊቀመንበሩ ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ቢቢሲም ወደ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሞባይል ስልክ ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ በተደጋጋሚ በመደወል ሊያገኛቸው ጥረት ባደረገበት ጊዜ ማግኘት እንደማይቻል እንዲሁም የኔትወርክ መጨናነቅ እንዳለ መልዕክት ብቻ ነበር የሚሰማው።

ሁኔታውን ለማጣራት ቢቢሲ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ የተየቀ ሲሆን እሳቸውም ስለጉዳዩ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚታወስ ሲሆን አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላትም በእስር ላይ ይገኛሉ።

ከእነሱም መካከል የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሚካኤል ቦረን፣ አቶ ኬነሳ አያና፣ የፓርቲው አማካሪ ዶክተር ሽጉጥ ገለታና ኮሎኔል ገመቹ አያና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቀደም ሲል ፓርቲው አሳውቋል።

ኦነግ ለበርካታ ዓመታት መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትረ ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የግንባሩ አመራር በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወቃል።