28 ሀምሌ 2020, 14:59 EAT

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ፓርቲያቸው በመጪው የፈረንጆች ዓመት ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ በማድረግ እንደመረጣቸው አስታወቀ።

የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ናሽናል ሪዚስታንስ ሙቭመንት ለ2021 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዩዌሪ ሙሴቪኒን እጩ አድረጎ ማቅረቡን ያስታወቀው ዛሬ ነው።

እጩ ሆነው የቀረቡት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ፤ ለውድድር የሚቀርቡት የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በህዳር ወር ላይ ሲያፀድቅ ነው።

ለ34 ዓመታት ኡጋንዳን ያስተዳደሩት ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ፤ ተወዳድረው ካሸነፉ ለተጨማሪ አምስት ዓመት ስልጣን ላይ ይቆያሉ ማለት ነው።

በሚቀጥለው ዓመት ታኅሳስ ወር ላይ ለሚካሄደው ምርጫ ሌሎች ፓርቲዎች እስካሁን ድረስ እጩዎቻቸውን አላሳወቁም።

ነገር ግን የፕሬዝዳንቱ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው ድምጻዊውና ፖለቲከኛው ሮበርት ኪያጉላኒ ወይንም በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቦቢ ዋይን በአገሪቱ ወጣት መራጮች ዘንድ ትልቅ እድል አለው ተብሎ ከአሁኑ ግምት ተሰጥቶታል።

በ2017 የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን የሚገድበውን ሕግ ሽሮታል።

የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህ የሥልጣን ዘመንን የሚገድበው ሕግ በመነሳቱ ዩዌሪ ሙሴቪኒ የእድሜ ልክ ፕሬዳንት እንዲሆኑ እድል ተሰጥቷቸዋል ይላሉ።

ባለፈው ወር የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የ2021 ምርጫ በታኅሳስ ወር እንደሚካሄድ የገለፀ ሲሆን፤ ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ አይቻልም ሲል አስታውቋል።

በኡጋንዳ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው ምርጫ የምረጡኝ ዘመቻ ማድረግ የሚፈቀደው በሬዲዮ፣ ቲቪ እና በበይነ መረብ አማካእነት ብቻ ነው።

በኡጋንዳ ሬዲዮ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነት ያለው መገናኛ ብዙሃን ነው።

በአገሪቱ የሚገኙ አብዛኛው ሬዲዮ ጣቢዎች አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው በምርጫ ዘመቻው ወቅት የበላይነት ሊኖረው ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።