28 ሀምሌ 2020

ኃይሌ ገብረሥላሴ

በዘመናዊው ዓለም የኢትዮጵያ ስም በበጎ እንዲነሳ ካደረጉ ሰዎች መካከል ኃይሌ ገብረሥላሴ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሰው ነው። ኃይሌ በአገሪቱ ውስጥ ከህጻን እስከ አዋቂ የሚታወቅና ስሙ ዘወትር የሚነሳ ድንቅ አትሌት ነው።

ኃይሌ በሩጫው መስክ የአገሩን ገጽታ በታላላቅ የዓለም መድረኮች ላይ በአውንታዊ መልኩ ሲያስነሳና ሲያስወድስ ቀይቶ ጎን ለጎንም በተለያዩ የኢንቨሰትመንት ዘርፎች ላይ በመሰማራት በጥረቱ ያገኘውን ሐብት አፍስሶ ለእራሱና ለወገኖቹ ጠቃሚ የሆኑ ምጣኔ ሃብታዊ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ከሳምንታት በፊት በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። ከዚህ ባሻገርም በርካታ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች ላይ በተፈጸመው ጥቃትም ከፍተኛ ውድመት መድረሱም ተገልጿል።

በተለይ በሻሸመኔና በባቱ ከተሞች ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለንብረቶች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

በእነዚህ ከተሞች ከወደሙ ንብረቶች መካከል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለማችን የሩጫ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀሱ ጥቂት ብርቅዬ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው የኃይሌ ገብረሥላሴ ሁለት ትልልቅ ሆቴሎች ይገኙበታል።

ኃይሌ ገብረሥላሴ በከተሞቹ ውስጥ የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ እንግዶችን ከሚያስተናግዱ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥቂት ሆቴሎች መካከል ቀዳሚ በሆናቸው በሁለቱ ሆቴሎቹ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ቢሰላ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ሊበለጥ እንደሚችል ለቢቢሲ ግምቱን ገልጿል።

“ትክክለኛ ቁጥሩን አላወቅንም፤ እስከ 290 ሚሊዮን [ሊደርስ ይችላል]። እንዲሁ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ብለን ነው የያዝነው” የሚለው ኃይሌ ስሌቱ ሲሰራ የወደሙ ወይንም የጠፉ ዕቀዎችን ለመመልሰ ቢሞከር ዛሬ ገበያው ላይ ባላቸው ዋጋ መሰረት መሆኑን ይገልፃል።

የጉዳት መጠን

“ሻሸመኔ የነበረው ሆቴላችን ባለሦስት ኮከብ ነው፤ እርሱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሟል። በጣም ብዙ የለፋንበት ቤት ነበር” ይላል ኃይሌ የእርሱ ንብረት በሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ለቢቢሲ ሲዘረዝር።

“የዝዋዩ ሪዞርት ደግሞ . . . እንዲያውም ዝም ብሎ ቀፎው ቆሟል፤ መስታወቶቹ ረግፈዋል፤ ስፓው ተቃጥሏል፤ የአካል ብቃት ማዕከሉ ተቃጥሏል። ግምጃ ቤቱ፣ የልብስ ማጠቢያ ክፍሉ፣ የምግብ ማብሰያ ክፍሉ በሙሉ ተቃጥለዋል። እንግዳ መቀበያ ክፍሉን ጨምሮ አንዳንዶቹ ደግሞ ተርፈዋል፤ ግን ብዙዎቹ ዕቃዎች ተዘርፈዋል።”

በሁለቱ ከተሞች ወደሥራ ተመልሶ የመግባት ሐሳብ ስለመኖር ያለመኖሩ የተጠየቀው ኃይሌ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ያለመደረሱን የሚጠቁም ምላሽ ሰጥቷል።

“የሻሸመኔውን ሆቴል የምንሰራው ከሆነ እንደገና ከመሬቱ ጀመረን ቆፍረን ነው የምንሰራው። የዝዋዩን እንኳ ማደስ ይቻላል፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደሥራ መመለስ ይቻላል” ሲል ግምቱን ይናገራል።

በሁለቱ ሆቴሎች ቁጥራቸው ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ሠራተኞች ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፤ እንደ ኃይሌ ገለፃ። “እነርሱ ከሥራ ውጪ ሆነዋል።”

ሥራቸውን ያጡት እነዚህ ግለሰቦች በከተሞቹ በሚገኙ ሌሎች ሆቴሎችና ሪዞርቶች ተቀጥረው እንዳይሰሩ እንኳ እነርሱን ሊቀጥሩ የሚችሉ ተመሳሳይ ተቋማት በአብዛኛው የጉዳት ሰለባ ሆነዋል እንደሆኑ ይናገራል ኃይሌ።

“ይህ ትልቅ ቀውስ ነው፤ በአገሪቱ የሥራ አጡ ቁጥር በበዛበትና ብዙ ወጣቶች ሥራ በሌላቸው በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ ሥራ አጥ መፍጠር ነው” የሚለው ኃይሌ፤ በሌሎች ተቋማትም ላይ በደረሰው ተመሳሳይ ጉዳት የእንጀራ ገመዳቸው የተበጠሰ ወይንም የሳሳ ግለሰቦች ቁጥር ሲታሰብ ችግሩን ይበልጡኑ ያገዝፈዋል ሲል ያስረዳል።

ኃይሌ ገብረሥላሴ

የዋስትና ዕጦት

ኃይሌ በሻሸመኔ እና ዝዋይ ከተሞች እንዲሁም በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች በንግድና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሱት ጥቃቶች የሥራ መቋረጥን ማስከተላቸው በመንግሥትን በግብር የሚሰበሰብን ዳጎስ ያለ ገቢ ከማሳጣታቸው ባሻገር ሌሎች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚያስቡ ባለሐብቶች የማስጠንቀቂያ ደወል የሚያሰሙ ናቸው ይላል።

“ሌላው [ጥያቄ] የሚቀጥለው ባለሐብት የተቃጠለች ከተማ እያየ ምን ዓይነት ተነሳሽነት ኖሮት ገንዘቡን ያፈሳል? የሚለው ነው። ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል፤ ሆቴሎች ተቃጥለዋል፤ ሕንፃዎች ተቃጥለዋል፤ የንግድ ተቋማት ተቃጥለዋል፤ የአበባ እርሻ. . . ብዙ ነገሮች ተቃጥለዋል። [. . . ] እንደአገር አጥተነዋል የምለው እርሱንም ነው።”

ኃይሌ በጥቃቱ ለመወደሙት ንብረቶቹና ተቋማቱ የመድን ዋስትና ክፍያ አገኛለሁ የሚል እምነት የለውም።

“እኔ ምናልባትም እዚህ ያጣሁትን በሌሎች የንግድ ድርጅቶቼ አካክሰው ይሆናል፤ ግን አንዲት ነገር የነበረችውና እርሷንም በአንድ ቀን ያጣ ስንት አለ። የአንዳንዶቹን ስትሰማ ሰቅጣጭ ነው፤ በሌሊት ልብስና በነጠላ ጫማ፥ መቀየሪያ ልብስ እንኳን ሳይዙ ወጥተው በየሰው ቤት የቀሩ አሉ።”

በንብረቱ ላይ ስለተፈጸመው ውድመት በአካባቢው ካሉ የማኅበረሰብ መሪዎችና ባለስልጣናት ጋር የስልክ ውይይቶችን ማድረጉን ኃይሌ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ብዙ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ ሆነዋል፤ መንግሥት ቶሎ መልስ እንዲሰጥ እንፈልጋለን፤ እየተነጋገርንም ነው” ይላል። “ብዙ ሰዎች አልቀሰዋል፤ አርባ ስምንትና ሃምሳ ዓመት የለፉበትን ሥራቸውን ያጡ ሰዎች እንባቸውን አፍስሰዋል፤ እነርሱም ፍትሕ ይፈልጋሉ።”

ምላሹ ያለው በዋናነት በመንግሥት እጅ ነው ሲል አጥብቆ የሚከራከረው ኃይሌ ነገሮች እንዲስተካከሉ ከተፈለገ “ፍትሕና ለወደፊቱ ዳግም ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደማይደርሱ ዋስትና ያሻል” ይላል።

“በመጀመሪያ ፍትህ እፈልጋለሁ” ሲል ለቢቢሲ ያስረዳል ኃይሌ።

“ይሄንን የፈፀሙ ሰዎች ወደ ሕግና ፍትህ መቅረብ አለባቸው።”

ከዚህ ባሻገር የሚጠብቀው ዋስትና ግን ከመንግሥትም ብቻም ሳይሆን ከሕዝብም ጭምር መምጣት አለበት ባይ ነው ኃይሌ፤ ላንጋኖ አካባቢ ጥቃት ለማድረስ የተደረገ ሙከራ በአካባቢው ነዋሪዎችና ሠራተኞች መክሸፉን በማውሳት በሌሎችም ስፍራዎች ተመሳሳይ ነገር ሊኖር ይገባ እንደነበር ይናገራል።

“የግለሰብን ንብረት እያጠቃህ ሌላ ግለሰብ መጥቶ ሥራ ይሰራል ማለት ከባድ ነው።”

የፀጥታ ኃይሎችም ይህን መሰሉን ድርጊት መከላከል ነበረባቸው፤ “እርሱን አላደረጉም” ሲልም ኃይሌ ቅሬታውን ገልጿል።

ኃይሌ ለደረሰው ጉዳት ካሣ እንደሚያስፈልግም ይሞግታል።

በቅርቡ በአዳማ በሚከፍተው አዲስ ሆቴሌ በባቱ እና በሻሸመኔ ጥቃቶች ሥራቸውን ያጡና መኖሪያቸውን መቀየር የሚችሉ የተወሰኑ ሰዎችን ለመቅጠር መታሰቡን የሚናገረው ኃይሌ፤ የሰሞኑን መሪር ዜናዎች ግን በጥቅሉ በአገሩ ላይ ያለውን ተስፋ እንዳላሳጡት ይለፃል፦

“አገሬ ነች፣ ኢትዮጵያ ነች፣ የትም አልሄድም። ሞትም ቢመጣ እዚሁ ነው የምጋፈጠው።”