31 ሀምሌ 2020, 08:36 EAT

ጎምቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጪው ህዳር የሚካሄደው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡትን ሃሳብ ተቃወሙ።
ፕሬዝዳንቱ ምርጫው እንዲራዘም ፈልገው የነበረው በፖስታ የሚሰጥ ድምጽ ማጭበርበር አያጣውም ከሚል ስጋት ነው።
በሪፐብሊካን የበላይነት የሚመራው ሴኔት አባል የሆኑት ሚች ማክኮኔል እና በህግ መምሪያ ምክር ቤት ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ሪፐብሊካን የሚወክሉት ኬቨን ማክ ካርቲ ናቸው የትራምፕን ሃሳብ የተቃወሙት።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርጫውን የማራዘም ሥልጣኑ የላቸውም፤ የትኛውም የምርጫ ማራዘም እቅድ መጽደቅ ያለበት በኮንግረሱ ነው ተብሏል።
ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳር ወር የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፖስታ የሚሰጥ ድምጽ ወደ ማጭበርበርና የተሳሳተ ውጤት ያመራል በሚል ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሃሳብ አቅርበው ነበር።
ምርጫው የሚዘገየው እስከመቼ ድረስ እንደሆነ ሲናገሩም ሰዎች “በአግባቡ፣ ደህንነታቸውና ምስጢራቸው ተጠብቆ” መምረጥ ሲችሉ ብለው ነበር።
• ዶናልድ ትራምፕ መጪው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲዘገይ ጠየቁ
• ጭምብል የማይለብሱ የአሜሪካ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አባላት ይባረራሉ ተባለ
• አውሮፓ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሰጋታል?
የፕሬዝዳንቱን ስጋት የሚያረጋግጥ መረጃ ያለው በጣም አነስተኛ ቢሆንም እርሳቸው ግን በተደጋጋሚ በፖስታ የሚሰጥ ድምጽን በመቃወም ሲናገሩ ይደመጣሉ።
የአሜሪካ ግዛቶች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በፖስታ የሚሰጥ ድምጽን ቀለል ማድረግ ይፈልጋሉ።
ሴናተር ማ ኮኔል አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከዚህ በፊት አንዴም ዘግይቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።
” በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም። በጦርነት፣ በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ እያለን አንኳ በፌደራል ደረጃ የተያዘ ምርጫ በወቅቱ ተካሂዶ ነው የሚያውቀው። በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይም ያንን ነው የምናደርገው’ ብለዋል።
ማክ ካርቲም የእርሳቸውን ሃሳብ በመደገፍ ” በፌደራል በሚደረግ የምርጫ ታሪክ ይህ ተከስቶ አይታወቅም፤ ስለዚህ ምርጫችንን በታቀደለት ጊዜ እናከናውናለን” ብለዋል።
የትራምፕ ደጋፊ የሆኑት ሴናተር ሊንድሲ በበኩላቸው ምርጫውን ማራዘም “መልካም ሃሳብ አይደለም” ብለዋል።
ነገር ግን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ በፕሬዝዳንቱ ሃሳብ ላለመጠለፍ ሲታገሉ ተስተውሏል።
ጋዜጠኞች፣ ፕሬዝዳንቱ ምርጫውን ያራዝሙት እንደሆነ ሲጠይቋቸው ” በእንዲህ ያለ የህግ ትርጓሜ ውስጥ ” መግባት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
የትራምፕ ዳግም ምርጫ ቃል አቀባይ ሆጋን ጊድሊ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ጥያቄ ነው ያነሱት” ሲሉ ተከላክለዋል።
በአሜሪካ ህግ መሰረት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርጫውን የማራዘም መብት የላቸውም።
የምርጫውን ቀን መቀየር የሚያስፈልግ ከሆነ መጽደቅ ያለበት በኮንግረሱ እና በህግ መወሰኛ ምክር ቤት ይሆናል።
የህግ መወሰኛ ምክር ቤትን ደግሞ የሚቆጣጠሩት ዲሞክራቶች ሲሆኑ ከአሁኑ አስቀድመው አንዳንድ ምክር ቤት አባላት የምርጫው መራዘምን ሃሳብ ተቃውመውታል።
የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወደ 2021 ለመግፋት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግን እንደሚጠይቅ የሕገ መንግሥት ባለሙያ የሆኑ ግለሰቦችን ጠቅሰው አሜሪካ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ስድስት የአሜሪካ ግዛቶች በህዳር ወር የሚካሄደውን ምርጫ በአጠቃላይ “በፖስታ በሚሰጥ ድምጽ” ለማድረግ አቅደው ነበር።
እነዚህ ግዛቶች ዋሺንግተን፣ ኦሪገን፣ ኮሎራዶ፣ ሃዋይ፣ ዩታህ እና ካሊፎርኒያ ናቸው።
እነዚህ ስድስት ግዛቶች ለተመዘገቡ መራጮች ወዲያውኑ በፖስታ ድምጽ መስጫ የሚልኩ ሲሆን፤ ፖስታዎቹም በምርጫ ቀን ተመልሰው የሚላኩ አልያም በምርጫ ጣቢያ የሚመለሱ ይሆናል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ሃሳብ የተሰማው የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት በ1930 ከገባበት ድቀት በባሰ መጎዳቱን የሚያሳይ መረጃ ከወጣ በኋላ ነው።