30 ሀምሌ 2020

የህዳሴ ግድብ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት መከናወኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ደስታቸውን ሲገልጹ ግብጽ ግን በነገሮች አካሄድ ምንም ደስተኛ እንዳልሆነች እየታየ ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአባይ ወንዝ ላይ እና ዙሪያ ምንም አይነት የልማት ስራዎችን እንዳትሰራ ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት የነበረ ሲሆን ማንኛውም አይነት ከወንዙ ጋር የተገናኘ ስራ ደግሞ የውሃውን መጠን ሊቀንሰው ስለሚችል ግብጽ ጉዳዩ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው በማለት ስትከራከር ቆይታለች።

በአጎርጎሳውያኑ 2011 ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ሰአት ለመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን ውሃ መያዝ ችሏል። በዚህ ዓመት የክረምት ወቅት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያትም ግድቡ 4.9 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ አጠራቅሟል።

የውሃ ሙሌቱ የተጀመረው ደግሞ ግብጽ ሙሌቱን በተመለከተ ሁሉንም የሚያስማማ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ነው ብላለች። ከመጀመሪያውኑም ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌቱ መጀመር የለበትም በማለት ግብጽ ስትከራከር ነበር።

በሚቀጥሉት ከአራት እስከ ስድስት ዓመታት በግድቡ እንዲኖር የሚፈለገው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን ሙሉ በሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅና ስራ ሲጀምር በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ ይሆናል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በትንሹ ለአስር ዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ድርድር እዚህ ግባ የሚባል ስምምነት ላይ መድረስ ባይቻልም ኢትዮጵያ ግን ላለፉት ሰባት ዓመታት የግድቡን ግንባታ ስራ አላቆመችም ነበር።

ግብጽ ላለፉት ዓመታትም የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማትና አገራትን በመጠቀም በግድቡ ዙሪያ በቻለችው መጠን ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ሞክራለች። ነገር ግን ከሰሞኑ ግብጽ የተሸነፈች ይመስላል፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ጀምራለች።

ከዚህ በኋላ ግብጽ ምን ማድረግ እንዳለባትና እንደምትችል ግራ የተጋባች ትመስላለች። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ወታደራዊ መፍትሄ እንደ አማራጭ ሊቀርብ እንደሚችል ማሰብ ይቻላል።

የግብጽ ባለስልጣናት እስከመጨረሻው በሰላማዊ ድርድር እንደሚያምኑ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ነገር ግን ሁሉም አይነት አማራጭ ከግምት ውስጥ ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።

አሁን ግን ግድቡ መሞላት መጀመሩን ተከትሎ ግብጽ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ላይ እምነት እንዳላትና ኢትዮጵያ ለብቻዋ የምትወስነውን ውሳኔ እንደማትቀበለው ገልጻለች።

ግብጽ በረሀማ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ እንዳላት በተደጋጋሚ በመግለጽ የታላቁ ሕዳሴ ግብድ ግንባታ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው ብላለች። የአባይ ወንዝ ደግሞ ለግብጻውያን የመጠጥ እና የግብርና ውሃ ዋነኛ ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያም አባይን የህልውና መሰረቴ ነው በማለት ትከራከራለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት

”በጋራ ጥረታችን ግድባችንን እዚህ ደረጃ ስላደረስነው መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ” ብለው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ደግሞ አባይ ከወንዝነት አልፎ ሐይቅ መሆኑን በመግለጽ አባይ የእኛ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህም ሰአት ነበር ግብጻውያን የፈሩት ነገር እንዳልቀረ የተገነዘቡት። አንድ ግብጻዊ ጋዜጠኛም ኢትዮጵያ በአገሩ ላይ የበላይነት እንደተቀዳጀች በመግለጽ ጨዋታው ግን አሁንም አለመጠናቀቁን ፅፏል።

አክሎም ” ኢትዮያውያን እኛ ያለ አባይ መኖር እንደማንችል መቀበል አይፈልጉም። እነሱ ከተለያዩ ወንዞች በየዓመቱ እስከ 950 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያገኛሉ። ይህ ቁጥር ደግሞ እኛ ከምንፈልገው ግማሹ ማለት ነው” ሲል ጽፏል።

አሁንም እንደሚቀጥል የሚገመተው ድርድር ፍሬ አልባ የሚሆን ከሆነ ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድና የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ታስባለች።

ነገር ግን ጉዳዩ በአምስቱም ቋሚ የምክር ቤቱ አባል አገራት ተቀባይነት ማግኘቱ አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም ቻይና እና ሩሲያ እራሳቸው ያልፈቱት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ጉዳይ አለባቸው።

በዚህ ላይ ውሳኔ ሰጡ ማለት የእነሱም ጉዳይ ሊነሳባቸው ነው ማለት ነው፤ ይህንን ደግሞ አይፈልጉትም።

ግብጽና ኢትዮጵያ መስማማት በሚችሉባቸው ቀላል ጉዳዮች ላይ እንኳን መስማማት አለመቻላቸው በቀጠናው አለመረጋጋትን ሊፈጥር እንደሚችል እሙን ነው።

ግብጽ እንደምትለው በግድቡ ምክንያት ድርቅ ወይም ማንኛውም አይነት ውሃ እጥረት የሚያጋጥማት ከሆነ አብሮት የሚመጣው መዘዝ ከሰሜን አፍሪካ እስከ አውሮፓ ድረስ የሚሄድ ነው።

በሁለቱ ትልልቅ የአፍሪካ አገራት መካከል ደግሞ ጦርነት ቢከሰት ኪሳራው ለሁሉም የአፍሪካ አገራትና ለመላው ዓለምም ነው።