August 7, 2020

መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

እውነቱን ለመናገር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በአሁኑ ወቅት ብዙ፣ በጣም ብዙ የሚወዘውዟቸውና አብዝተው የሚያስጨንቋቸው ሀገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ ጨርሶ ሊስተባበል አይችልም፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፍጻሜና የውሃው ሙሊት፤
ይህንኑ ተከትሎ የተደቀነባቸው የውጭ ሀይሎች ተጽእኖና የውስጥ መሰሪ ባንዳዎቻቸው የሽብር እንቅስቃሴ፤
መያዣ መጨበጫው የጠፋበት የኦሮሞ ጽንፈኞች ፖለቲካ፤
ድህረ-ሲዳማ ሪፈረንደም ትኩሳቱ እየናረ የመጣው የደቡብ ክልል አደረጃጀት፤
የብሔር ፖለቲካው ጡዘት እዚህም እዚያም እያደረሰ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግጭትና ከኖረበት ቀየ መፈናቀልና ለተለያዩ ሰብአዊ ችግሮች መጋለጥ፤
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እያሽቆለቆለ የመጣው ኢኮኖሚና እርሱ በተራው የፈጠረው ማሕበራዊ ምስቅልቅል፤
የሀገሪቱን ሁለንተናዊ መዳከምና በተለይም ወደብ-አልባነቷን በመንተራስ ሠላምና ደህንነቷን ለመፈታተን ከሁሉም መአዘናት በቀጥታም ሆነ በእጃዙር የሚቀነባበረው ሴራና የሚካሄደው ዘመቻ…

ከብዙዎቹ ማሳያዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡

በርግጥ ከነዚህና ከመሳሰሉት አንገብጋቢ አጀንዳዎች ጋር ሲነጻጸር ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሀ.ት) በትግራይ ክፍለ-ግዛት በተናጠል አካሂደዋለሁ የሚለውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ከሰፈር እድርተኞች ወይም እቁብተኞች አወካከል ጋር የሚያወዳድሩት ምርጫ መሳይ ሽርጉድ ያን ያህል አያስጨንቃቸውም፡፡ ይህንኑ ሀቅ ሰሞኑን ለሰበሰቧቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀር በአደባባይ ሲነግሯቸው ሰምተናል፡፡

ሆኖም በራያ፣ በጠለምትና በወልቃሂት ጠገዴ  አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎቻችን ይህንን የምንተዳዬ አነጋገር ሲሰሙ ምን እንደሚሏቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንሽ አስበዉበት ይሆን?

ህ.ወ.ሀ.ት ራሱ የተወከለበት የሀገሪቱ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግሥቱን ተርጉሞ ስድስተኛው ዙር ምርጫ እንዲራዘም ቀደም ሲል ካሳለፈው ውሳኔ ባፈነገጠ አኳኋን በቆረጣ እየተዘጋጀ ነው በሚባልለት በዚህ የሆያሆየ ምርጫ ወጥቶ እንዲሳተፍ በመቀስቀስ ላይ የሚገኘው ሰፊው የትግራይ ህዝብስ ቢሆን አባባላቸውን በቀላሉ ይቀበለው ይሆን?

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህ.ወ.ሀ.ት ሕገ-መንግሥቱን በጠራራ ጸሃይ ረግጦና በሀይል ደፍጥጦ በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለውን የወሮ-በላ እንቅስቃሴ ከመጤፍ የቆጠሩት አይመስልም፡፡ እንደርሳቸው ስር የለሽ ትንታኔ ከሆነ ረብ-የለሹ የትግራይ ምርጫ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስለማይለውጠው “ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት በከንቱ ከማባከን የዘለለ ሊሆን አይችልም፡፡ የክልሉ መንግሥት ሥልጣን አካላት እድሜ እንደሆነ እንደፌደራሉ መንግሥት አቻዎቻቸው ሁሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አስቀድሞ ባሳለፈው ውሳኔ እኩል ተራዝሟልና ህ.ወ.ሀ.ት በዚህኛው ምርጫ ተመልሶ ቢያሸንፍ እንኳ የተለየ ትርፍ አያገኝም” ካሉ በኋላ “ችግር የሚሆነው ሌላ ተቃዋሚ ድርጅት በክልሉ ተወዳድሮ የፖለቲካ ሥልጣኑን የጨበጠ እንደሆነ ብቻ ነው” ሲሉ አዲስ እውቀት ሊያስጨብጡን ሞክረዋል፡፡

በዚህ ጉራማይሌ አነጋገራቸው ታዲያ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አውቀዉትም ይሁን ሳያውቁት አስቀድመው ያጣጣሉትን ምርጫ ሕጋዊነት በይፋ መቀበላቸውንና ለተፈጻሚነቱ በጽንአት መቆማቸውን የዘነጉት መስለው ታይተዋል፡፡ በመሰረቱ መወገዝ ያለበት ውጤቱ ብቻ ሳይሆን ሂደቱም ጭምር እንደሆነ ተገቢው ግንዛቤ እንዲወሰድበት ያስፈልጋል፡፡

ፈረንጆቹ እንደሚሉት “የመርዛማ ዛፍ ፍሬ መርዛማ” በመሆኑ አንኳሩ ነጥብ በምርጫው ማን ያሸንፋል? የሚለው ሳይሆን ምርጫው ራሱ ሕገ-መንግሥታዊ ድጋፍ አለውን? የሚለው እንደሆነ ከወዲሁ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ተለዋጩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አቋም

እንደኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 8ና አንቀጽ 61 ድንጋጌዎች የተጣመረ ንባብ ከሆነ የሕገ-መንግሥቱ ባለአደራ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች ስብስብ የሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ እንደአንድ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ተቆጥሮ ይህንኑ የበላይ ሕግ የሚተረጉመው የመጨረሻ የሥልጣን አካልም እርሱ እንደሆነ በአንቀጽ 62 ንኡስ አንቀጽ ፺(1) ድንጋጌ ስር በጉልህ ተጠቅሷል፡፡

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ይመስላል፣ እመት ኬሪያ ኢብራሂም እርሳቸው ደጋግመው እንደሚለፍፉት በራሳቸው ውሳኔ ይሁን በድርጅታቸው አስገዳጅ ትእዛዝ ወደመቀሌ ኮብልለው አስደማሚ የክህደት መግለጫ በሰጡ ማግስት አዲስ የተመረጡትና ቃለ-መሀላ ፈጽመው ሥራ የጀመሩት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የትግራይ ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ የጀመረውን የተናጠል እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆምና ወደጤናው እንዲመለስ ሰሞኑን ይፋዊ ማስጠንቀቂያ እንደጻፉለት ሰምተናል፣ አንብበናልም፡፡

ይህ ጸሃፊ ግብዞቹ የህ.ወ.ሀ.ት መሪዎች ለዚህ ማስጠንቀቂያ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ ብሎ ቅንጣት ታህል ባያምንም አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ በልበ-ሙሉነት የተነሱበትን መንደርደሪያ ሕገ-መንግሥታዊነት ያጠይቃል፣ ያደንቃልም፡፡

የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 62 ንኡስ አንቀጽ (9) ድንጋጌ ስር ለፌደሬሽን ምክር ቤት ከሰጣቸው አበይት ሥልጣንና ተግባራት መካከል “የትኛውም ክልል በራሱ ጊዜ ሕገ-መንግሥቱን በአመጽ ወይም በፍጹም ደንታቢስነት ጥሶ ሕገ-መንግሥታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ በሚጥልበት ጊዜ የፌደራሉ መንግሥት አስፈጻሚ አካል ጣልቃ ገብቶ ሀይል በመጠቀም ጭምር የተባለወውን ጥሰት እንዲያስቆም” የሚያዘው ይገኝበታል፡፡

የላይኛው ምክር ቤት በሕገ-መንግሥት ደረጃ የተጎናጸፈው ይህ ወፍራም ሥልጣን ዘግይቶ በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ዓ.ም አማካኝነት ይበልጥ ተጠናክሮ የተደነገገ ሲሆን ዝርዝር አሰራርም ተበጅቶለታል፡፡

የፌደራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ ሲታዘዝ ሊፈጸም የሚገባውን ስነ-ስርአት ለመወሰን በወጣውና ቅርጫት ላይ ተጥሎ በከራረመው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ መሰረት “የትኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የጣለ ስለመሆኑ በራሱ አነሳሺነት ሲያውቅም ሆነ ከህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወይም ከሌላ ከማናቸውም መንግሥታዊ አካል በኩል መረጃ ሲደርሰው ተፈላጊውን ቅድመ-ምርመራ ካካሄደ በኋላ የተባለው አደጋ መኖር/አለመኖሩን ለመወሰን እንዲያመቸው ጉዳዩን በዝርዝር አጣርቶ ውጤቱን ያቀርብለት ዘንድ ለሀገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም አግባብ ላለው ለሌላ የመንግሥት አካል” መመሪያ ሊሰጥ ይችላል፡፡

“የደረሰውን ሪፖርት ወዲያውኑ ተቀብሎ ከመረመረ በኋላም ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ምርመራው እንዲካሄድ በተወሰነበት ክልል ውስጥ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድ ያደርግ ዘንድ” ከፍ ብሎ የተጠቀሰው አንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ (4) ድንጋጌ ለዚሁ ምክር ቤት በማያሻማ ሀይለ-ቃል ሥልጣን ይሠጠዋል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 14 ንኡስ አንቀጽ (2) ፊደል ተራ ቁጥሮች ሀ.ና ለ. ድንጋጌዎች ደግሞ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ በፌደሬሽን ምክር ቤት የሚታዘዘው አስፈጻሚ የመንግሥት አካል የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ምንነት የሚያብራሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህም መሰረት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አሳሳቢነት ተመልክቶ የተደቀነውን አደጋ ሊቀለብስ ወይም በቁጥጥር ስር ሊያውል የሚችል የፌደራል ፖሊስ ሀይል ወይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ (ካስፈለገም ሁለቱን) በክልሉ ውስጥ በጊዜያዊነት ሊያሰማራ” ይችላል፡፡ “ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰቱ ቀጥሎ የአመጹ ደረጃ የሚስፋፋ መስሎ ከታየማ የዚያ ክልል ሕግ ዐውጪ ምክር ቤትም ሆነ ከፍተኛው አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ሳይቀሩ ከስራ እንዲታገዱና ለፌደራሉ መንግሥት በቀጥታ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከማቋቋም” የሚደርስ መሬት-አንቀጥቅጥ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችልም ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራረጧል?

መቸም ጠቅላይ ሚኒስትራችን የብዝሃ-ልሳን ጌታ መሆናቸው በጅጉ ደስ ያሰኛል፡፡ ሰሞኑን ሌላው በህዝብ ዘንድ አቢይ መከራከሪያ ሆኖ የሰነበተው ታዲያ ይህንኑ ማለፊያ ተሰጥዎ አልቀው በመጠቀም ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በትግርኛ ቋንቋ ያደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው፡፡

ያንኑ ቃለ-ምልልስ መነሻ አድርገው “ሰፊው የትግራይ ህዝብ በዚህ ቀውጢ ወቅት ከዶ/ር ደብረ-ጽዮን ገብረ-ሚካኤል ጎን እንዲቆምና እርሳቸውን በተናጠል እንዲደግፍ” ሲሉ ያስተላለፉት የተማጽኖ ጥሪ በተለይ እየተመዘዘ በሰፊው ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዋዛ የወረወሩትን ያንን አባባል ህ.ወ..ሀ.ትን ለመከፋፈል እንደተቀየሰ አዲስ ብልሃት ቆጥረዉታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ‘ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ’ በማለት አቃለው እንደተመለከቱባቸው ታዝበናል፡፡

እንደአንድ የሀገር መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዶ/ር ደብረ-ጽዮን ወቅታዊ አቋም ያላቸው መረጃ ከሁላችንም የተሻለ እንደሚሆን  በማመን እኔ በበኩሌ ከሁለቱም ተቃራኒ ጎራዎች የሚሰነዘሩትን እነዚህን ሽሙጦች ከመጋራት መቆጠቡን መርጫለሁ፡፡ በርግጥ ይህ ያልተጠበቀ ጥሪ ከሁሉም በላይ የፈንቅል አስተባባሪዎችን ክፉኛ እንዳስቀየመባቸው ሰምቻለሁ፡፡

የትላንት አንጋቾች ለከት የለሽ እንጉርጉሮ

ህ.ወ.ሀ.ት ራሱን በራሱ ያቀለለና ከማእከላዊው መንበረ-ሥልጣን እስከወዲያኛው የተገለለ ቡድን ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደክርስቶስ ዳግም ከክብርና ሞገስ ጋር ይመለሳል ብለው ዛሬም ቢሆን በተስፋ የሚጠብቁት የመሃል አገር ቅሪቶቹ በቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ‘ጅብ ከሄደ የሚያለቃቅስ ውሻ’ ይመስል እነሆ ጨለማው ተገፎ በብርሃን ሲተካ በሀሰት ባላንጣዎቹ መስለው ለመታየት እርስበርስ የሚሽቀዳደሙት የቀድሞ ባልንጀሮቹ ነባር የኦ.ህ.ዴ.ድና የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን አባላት ወደመንግሥትና መንግሥት-አደር ወደሆኑ ፓርቲ›‹-መራሽ መገናኛ-ብዙኃን ተቋማት ብቅ እያሉ “ድሮም ቢሆን አዛዥ ናዛዣችን እርሱ ነበር”፣ “እኛ እኮ ከምኑም የለንበት”፣ በማለት አይናቸውን በጨው አጥበው የሚያሰሙን ለከት የለሽ ኑዛዜ ፍጹም አታካች ሆኖብናል፡፡ ይህ አይነቱ የ’እኔ የለሁበትም’ የተኩላ ጩኸታቸው በተሸናፊነት ስነ-ልቦና ታጅቦ በብሔራዊው ቴሌቪዥን አማካኝነት እየተቀነባበረ በየምሽቱ አቢይ ዜና ሆኖ ሲቀርብልን እንደተለመደው ህ.ወ.ሀ.ትን ረግመን እነርሱን ብቻ እንድንመርቅ ታስቦ የሚሰናዳ ይመስላል፡፡

እንዲህ ያለው የአላጋጮች ሙሾ በፍጹም መቆም ይኖርበታል፡፡

የፌደራሉ መንግሥትም ቢሆን በህ.ወ.ሀ.ት ላይ ሊወስድ ያቀደው እርምጃ ካለ ‘ሙያ በልብ ነው’ ብሎ ያለማወላወል መውሰድ እንጂ የዛሬዎቹ የርሱ አባላት ትላንትና ከትላንት ወዲያ የታሪኩ ክፍልና አካል ያልነበሩ ይመስል “ህ.ወ.ሀ.ት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በዘመነ-አገዛዙ ዴሞክራሲያዊና የእውነተኛ ፌደራላዊ ስርአት ጠበቃ  እንዳልነበር አሁን ገና ገባኝ’ እያለ በየመድረኩ ልባችንን ሲበዛ ባያቆስለው መልካም ነው፡፡

አበቃሁ፡፡