ከ 3 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት አዳዲስ አስር ሹመቶችን ሰጥተዋል።
ከሰሞኑ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ አባልነታቸው የታገዱት አቶ ለማ መገርሳ ከመከላከያ ሚነስትርነታቸው ተነስተዋል።
በአቶ ለማ ምትክ ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚንስትር ሆነው መሾማቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፌስቡክ ገፅ ከሰፈረው መረጃ መረዳት ተችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምትክ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነቱን ቦታ የተረከቡ ሲሆን፣ ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ መሾማቸውንም መረጃው ጠቁሟል።
ሌሎቹ ሹመቶች ተስፋዬ ዳባና ፍቃዱ ጸጋ በምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግነት፣ ዮሐንስ ቧያለው፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ እንደአወቅ አብቴ፤ የብረታ ብረት ኢንጅኔሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደ ማርያም፤ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ናቸው።
https://twitter.com/PMEthiopia
Office of the Prime Minister – Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስር ሹመቶችን ዛሬ ሰጡ:- –
ዶ/ር ቀንዓ ያደታ የመከላከያ ሚኒስትር
– ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
– ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
– ታከለ ኡማ፤የማዐድንና ነዳጅ ሚኒስትር
– ተስፋዬ ዳባ፤ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ
– ዮሐንስ ቧያለው፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግነኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
– ንጉሡ ጥላሁን፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር
– እንደአወቅ አብቴ፤ የብረታ ብረት ኢንጅኔሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር
– ፍቃዱ ጸጋ፤ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
– ፕሮፌሰር ኂሩት ወልደ ማርያም፤ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ
234 133 people are Tweeting about this
የጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት ቃለ አቀባይ የነበሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ካሉበት ኃላፊነት ተነስተው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሹመት እንደተሰጣቸውም መረጃው ጠቁሟል።
የሚኒስትሮቹ ሹመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ቀርቦም መፅደቅ ያለበት ሲሆን ፤ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት እረፍት ላይ መሆኑም ይታወቃል።
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስመልክቶ ፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ማገልገል ደስታ እንደሰጣቸውና የከተማዋን ችግሮች ለመቅረፍ የተቻላቸውን ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
“አዲስ አበባን መምራት ትልቅ ዕድል ነው። ደጋግመን እንደምንለው፤ “በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን እድል” ላለማባከን ጥረናል። በሁሉም ውስጥ የነዋሪዎቻችን ብርቱ ድጋፍ አብሮን ነበር። አዲስ አበባን እንደስሟ ለማድረግ በደስታ፤ በፍላጎትና በፍቅር ስንተጋ ምርኩዝ ለሆናችሁን ሁሉ፤ ከልቤ አመሰግናለሁ! በፍጹም ቅንነት ላጎደልናቸው ነገሮችም ይቅርታ እጠይቃለሁ” በማለት መልዕክታቸውን አስፍረዋል።