August 18,2020

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ ላይ የለጠፈውን ተንቃሳቃሽ ምስል ‘የአምነስቲን የውስጥ ሂደት ያልተከተለ ነው’ አለ።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ፤ ባለፈው ዓርብ በአምነስቲ ትዊተር ገጽ ላይ የወጣው የአንድ ደቂቃ ቪዲዮ ‘የአምነስቲን የውስጥ ሂደት የተከተለ አይደለም’ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ፍሰሃ የተንቀሳቃሽ ምስሉን ይዘት ሲያስረዱ፤ “ከሃጫሉ ግድያ በኋላ የተፈጠረውን ግርግር የሚመለከት ነው። ስለነበረው ግጭት እና ስለታሰሩ ሰዎች ነው” ይላሉ።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ከወጣ በኋላ በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ፤ ሪፖርቱ ወይም ዘገባው ሚዛናዊ አይደለም በሚል ሲተቹት ነበር።

አቶ ፍሰሃም የተሰጡ አስተያየቶችን መታዘባቸውን እና ምስሉ ከድርጅቱ ማሕበራዊ ገፅ እንዲወርድ መደረጉን ይናገራሉ።

“ተንቀሳቃሽ ምስሉ የኛን የውስጥ ሂደት ሳያሟላ ነበር የወጣው። በዚያ ምክንያት ነው ያወረድነው። ለተፈጠረው ችግርም ይቅርታ ጠይቀናል” ብለዋል አቶ ፍሰሃ።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የተገኘው ስህተት ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ፍሰሃ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። “አንድ ለሕዝብ የሚቀርብ ነገር ማለፍ የሚገባው ሂደት አለ። ይሁን እንጂ ቪዲዮ የተወሰኑትን ሳያሟላ በስህተት ተጭኗል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

አምነስቲ ከመንግሥት ውጪ በሌሎች ኃይሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ፍሰሃ፤ ከዚህ አንጻር መንግሥት ግጭቶችን የማስቆም እና የመከላከል ግዴታውን በተመለከተ እንመለከታለን ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረ ሪፖርትም ከመንግሥት ውጪ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተመልክተናል ያሉ ሲሆን፤ “አሁንም ከሰኔ 23 በኋላ የተፈጠረውን ብሔር እና ኃይማኖት ተኮር የሚመስሉ ጥቃቶችን እየመረመርን ነው። ጥናታችንን አልጨረስንም። ወደፊት የጥናታችንን ግኝት የምናስታውቅ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ፍሰሃ አንዳንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አምነስቲ ትናንት ይቅርታ የጠየቀበትን ጉዳይ ድርጅቱ ግንቦት ወር ላይ ካወጣው ሪፖርት ጋር ማያያዛቸው ስህተት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አምነስቲ በግንቦት ወር በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በአንዳንድ ቦታዎች ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ያወጣው ሪፖርት ስህተት መሆኑን ገልጾ ይቅርታ ጠየቀ ሲሉ ዘግበዋል።

“ዓርብ ዕለት የወጣው ተንቀሳቃሽ ምስል ከሰኔ 23ቱ ግርግር እና እሱን ተከትሎ ስለሞቱ እና ስለታሰሩ ሰዎች ነው የሚመለከተው። ከዚያ ሪፖርት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በዚያ ሪፖርታችን ውስጥ ያሉት ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች አሁንም አሉ። የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘገባ ተገቢ አይደለም” ብለዋል አቶ ፍሰሃ ተክሌ።