by ዘ-ሐበሻ
August 19, 2020
የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) ልሳን
ኢትዮጵያችን ቅጽ 4 ቁጥር 6 ነሐሴ ፲፫ ቀን ፪ ሺህ ፲፪ ዓ.ም.
የ27 ዓመት ህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ በሁለት ዓመት ብልጽግና/ኢሕአዴግ አገዛዝ ቢገላበጥ መሠረታዊ የሀገራችን ችግር ካልተሰበረ ሕዝባችንም ከሰቀቀን ኑሮ፣ ኢትዮጵያችንም ከትርምስ አንፈወስም፡፡ ሀገራችን ከዘርና ቋንቋ አከላለል ተላቃ ወደ ሌላ ፌደራላዊ አስተዳደር ለምሳሌ በአውራጃ አከላለል፣ ተፈጥሮን ያማከለ ወይም በባለሙያዎች በተጠና ቋንቋና ዘርን ያላማከለ ሌላ የአስተዳደር ቀጣናዎች ካልተመለሰች የዘር ፍጅት፣ የንብረት ውድመት፣ የኑሮ ምስቅልቅል ጊዜ እየጠበቀ የሚያገረሽ በሽታ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ የአንድን ብሔር ቋንቋና ባህሉን ማክበር፣ ዘሩንና ማንነቱን ለማወቅ በዘርና ቋንቋ መሸንሸን ያተረፈው ቢኖር ለሕዝብ እልቂትን፣ ለሀገር ውድቀትን ነው፡፡ በቅርቡ በሻሸመኔና በአጋሮ የደረሰው የንብረት ውድመት የወገኖች እልቂት፣ በድሬዳዋ የተናደው የራስ መኮንን ሐውልትና የወደመው ንብረት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የታሰበው ተመሳሳይ ጉዞ የ29 ዓመቱ የከፋፍለህ ግዛ ሕገ መንግሥት ውጤት ነው፡፡
የሰሞኑ የሀገራችን ግርግርና ውድመት የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ መጣ ይባል እንጂ ከግድያው በፊትም የታቀደ መሆኑ ታውቋል:: ትላንት የነበረው ተቀጣጣይ የዘረኝነት ፈንጂ አድማሱን እያሰፋ፣ ውጥኑን “እያሳካ”፣ በሕገ መንግሥት እየተደገፈ የተከሰተ የዘር ማጥፋት ፈንጂ ውጤት ነው፡፡ የዛሬ 29 ዓመት ወያኔ ሥልጣን እንደያዘ ተጀምሮ የነበረው የበደኖና አርባ ጉጉ ፍጅት ተቸኮለ ተባለለት እንጂ አልተወገዘም፡፡ ሀገርና ሕዝብ ብሎም ትውልድን ማድቀቅና በተዛባ ታሪክ አቅጣጫ ማሳት መቅደም አለበትና ወያኔ/ህወሓት/ኢሕአዴግ በሦስት ስም፣ በአንድ ባህሪይ በስመ ሕገ መንግሥት ሀገሪቷንና ሕዝቡን ቆላልፈው ያዙት፡፡ 27 ሙሉ ዓመት ሀገር አንጡራ ሀብቷ እጅጉን ተዘረፈ፡፡ በስብሰናል፣ ገምተናል እስኪባልልን ድረስ እውነትም ሀገር ተራቆተች፣ ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ በደርግ ቀይ ሽብር ጭፍጨፋ የተቀጠፈው ትውልዷ ታሪክ ሳያገግም በወያኔ ትውልድ ማምከን ተተካ፡፡ ሀገሬ ብሎ በአንድነት የተነሳ ትውልድ በዘመነ ወያኔ ዘሩን ፍለጋ አተኮረ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት ይቀጭጭ ዘንድ ታሪክ ብረዛው ተጧጧፈ፡፡ እነሆ በመንግሥት ደረጃ በረቀቀ ዘዴ የሚከናወን ዘርና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ፍጅት በሀገራችን እየተካሄደ ነው፡፡
የ27 ዓመቱን የኢሕአዴግ/ህወሓት አገዛዝ እጅግ ብዙ ስለተባለለት ደግመን ውሃ አንወቅጥም፡፡ አሁን ግድያውና ፍጅቱ ያለው በ28 ወሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ብልጽግና አገዛዝ በመሆኑ በሻሸመኔና በሌሎች አካባቢዎች የደረሰው የሰው ልጆች እልቂት ዘርንና ሃይማኖትን ያነጣጠረ መሆኑን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት ሰላም ብሎ ችግኝ በሚተክልባት ሀገር የሰው ልጅ እየታረደ ነው፣ ዶር ዐብይ መናፈሻ እየገነቡ ሲፈነድቁ የነዋሪዎች ቤት፣ ንግድ ቤት፣ ተንቀሳቃሽ ንብረት በተቀነባበረ መልኩ እየጋየ ነው፡፡ ጠ/ሚሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሰብስበው ሲፈላሰፉ ክርስቲያን፣ ነፍጠኛና የሌላ ዘር መጤዎች ክልልላችንን እንድትለቁ እየተባለ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው፡፡ ምን እንደሚደረግ ግራ የተጋባንበት ይህ አስከፊ ዘመን ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ሀገራችንና ሕዝባችንን እጅጉን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ዘፍቋታል፡፡ ከፍጅቱ የተረፉት ከቤተሰብ አባላት ቢያንስ አንድ ሰው አጥተዋል፣ መላ ቤተሰቡም የጋየ ቀላል አይደለም፡፡ እነኚህ ወገኖች የሚበሉት የላቸውም፣ ቤት የላቸውም፣ አልባሳት የላቸውም፡፡ መንግሥት ከነሱ ስቃይ ይበልጥ ፈረስና ብስክሌት የሚጋለብበት መናፈሻ ጥሞታል፡፡ የአንድ ሰው ሀዘን እንኳ በባህላችን አርባ፣ ሰማንያ እየተባለ ይታወሳል፡፡ እውን የሻሸመኔውና የሌሎች አካባቢ ፍጅት ሀዘን ከውስጣችን ወጥቶ ነው ስለ አዲስ አበባ ፓርክ የሚደሰኮረው? ወይስ የፖለቲካውን አቅጣጫ የቀየሩ፣ የሸውዱ መስሏቸው?
በዚህ ሁለት ዓመት ከአራት ወር በጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አገዛዝ የተከሰተውን በመጠኑ እናስቀምጠው፦ ቡራዮ ፣ በዶዶላ፣ በአርባ ጉጉና በብኖ በደሌ፣ በሶማሌ ክልል የታረዱ ክርስቲያኖች፣ በሲዳማ ዞን በቤንዚን የተቃጠሉ የሃይማኖት አባቶች፣ በለገጣፎ በሰበታና በሰንዳፋ የንጹሃን ቤት በላያቸው ላይ የፈረሰ፣ በወለጋ ወደ 22 የሚጠጉ ባንኮች ዘረፋ፣ በአጣዬ በካራ ቆሬና በኬሚሴ የተካሄዱ የንጹሃን ጭፍጨፋ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጌድዮ ህዝብ መፈናቀል፣ በቤኒሻንጉል እየተካሄደ ያለው እልቂት፣ እስካሁን መዳረሻቸው ያልታወቀው ታፍነው የተወሰዱት ተማሪዎች፣ በአማራው ክልል የሚካሄደው ያላቋረጠ ፍጅት፣ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ፣ ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ ሰዓረ መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ አቶ ምግባሩ ከበደ እና የአማራ ልዩ ኃይሎች ግድያ ፣ በጥቅምት ወር አቶ ጃዋር “ተከብብያለሁ” ማለቱን ተከትሎ 86 ንጹሃን የደረሰው ጭፍጨፋ የተካሄደው በዚህ ሁለት ዓመት ለውጥ አይሉት ነውጥ ዘመን ነው፡፡
እነዚህ የፍጅት፣ ዘረፋ፣ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የመንግሥትና የክልል ታጣቂና ጸጥታ አስጠባቂ ኃይሎች በአሉበት ሀገር ነው፡፡ ጠ/ሚሩ ለነዚህ ድርጊቶች አልሰማሁም ከማለት ጀምሮ የሟች ዘር ቆጠራ ምላሻቸው እንደተጠበቀ የሰሞኑን ዘርና ሃይማኖትን ተገን ያደረገ ፍጅት በተወሰኑ ቡድኖች መካከል የተደረገ “ግጭት” አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው የመንግሥት ጥረት እራሱንም ወደ ተጠያቂነት ይከተዋል፡፡ ቀደም ሲል “ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው” እንዳሉት ጠ/ሚሩ እሳቸውና መንግሥታቸው እየተጠቃ ላለው ዘር፣ እየወደመ ላለው ንብረት፣ እየተቃጠሉ ላሉት አብያተ ክርስቲያን ከሰለቸ ማስመሰል የዘለለ የችግሩን መሠረታዊ ጉዳይ ሊፈቱ ጥረት ሲያደርጉ አልተስተዋሉም፡፡
ኢትዮጵያ በምንም መንገድ በዘርና ቋንቋ ተሸንሽና ሀገራችን ሰላምን አታመጣም፣ እድገትም አታሳይም፡፡ ለዚህም ነው ገና ከጅምሩ የወያኔ/ኢሕአዴግ መወገድ ከነሕገ መንግሥቱ ካልሆነ የሰቀቀንና የጭንቅ ኑሮ የየዕለት እንደሚሆን ችግሩን እየተጋፈጠ ያለው ሕዝብ መስካሪ ነው፡፡ ቅድሚያ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት ዳግም እንዲያብብ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የሰው ልጅ በከንቱ ከሚታረድ የወያኔን በታታኝ ሕገ መንግሥት በመናድ ሕይወት ቢከፈል ይመረጣል ፡፡ መብትና ነጻነት ሕይወት ይጠይቃልና በዚህ ሁለት ዓመት የፈሰሰው ደም ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህን መርዘኛ ሕገ መንግሥት ተገን ተደርጎ የተጀመረው የዘርና ሃይማኖት ፍጅት ላለመቀጠሉ ምንም ዋስትና የለም፡፡ የጠ/ሚር ዶክተር ዐብይ መንግሥት አንድን ዘርና ሃይማኖትን ተገን አድርጎ ሲዋቀር መሠረቱ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ “ከእጅ አይሻል ዶማ” እንዲሉ ብልጽግና ፓርቲ ስም ቀየረ እንጂ የዘር ስብስብ ነው፡፡ ይህ የዘርና ቋንቋ አከላለል በቅርቡ ሲዳማን ክልል እንዳደረገ ሁሉ ለሌሎቹ ደቡብ ክልሎች የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ሕገ መንግስቱ “የክልል ልሁን” ጥያቄ ያስተናግዳል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተገነባበት ዋልታ መገነጣጠል በመሆኑ አሁን መቀሌ የመሸገው የህወሓት ቡድን ትግራይን በሕገ መንግሥቱ መሠረት የማይገነጥልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ኦሮሚያም ጭንቅ የሆነበት የአዲስ አበባ ጉዳይ ቢሆንም በዚህ አካሄድ መንግስትነቱን አውጆ ሀገር ልትበታተን እንደምትችል ያለንበት አፋፍ መስካሪ ነው፡፡
አንዳን ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስት፣ ሲቪክ ማኅበረሰብ የሰሞኑን የዘር ፍጅት አስመልክቶ “ተጠያቂዎች ለፍርድ ይቅረቡ” ሲሉ አጠፋችሁ ባይባልም ዋናው ተጠያቂና ለዚህ እልቂት ኃላፊነት መውሰድ የሚገባው መንግሥት መሆኑን ከታሪክ ልንማር ይገባናል፡፡ ደርግ በ1967 ዓ.ም. ኅዳር ወር 60 የዓጼ ኃ/ሥላሴ ባለሥልጣናትን ሕግ ጥሶ በአንድ ምሽት ሲፈጅ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ሚና ቢጎላም በወቅቱ የነበረው ደርግ የተባለው ቡድን እንደ መንግሥትነት ይጠየቃል፡፡ ደርግ ይህን እርምጃ ሲወስድ ደባልቆ ከቀድሞው ባለሥልጣናት ጋር ያልተያያዙ በወቅቱ ቋንቋ ስድስት ተራማጆችን እረሽኗል፡፡ በወቅቱም የፍየል ወጠጤ እየዘመረ የፊውዳልና የባላባት እርዝራዥ እያለ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ፈጅቷል፡፡ ዛሬም የምናየው የአምባጋነኖች ተመሳሳይ ባህሪ ነው፡፡ እስቲ እውን የእነ እስክንድር ነጋና ባልደረቦቹ፣ የይልቃል እስርና ጥፋት ከአሸባሪው ጀዋር ይያያዛል? ለዶር ዐብይ ለጊዜው ግርግር አመችቷቸው ይሆናል እንጂ መፍትሄ እንደማይሆን እንጠቁማለን፡፡ ኦነግና የዶር ዐብይ መንግስት የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ሊተገብሩ ያሰቡትን “ባልደራስ” እንዳይሳካ ቅርቃር ከቷቸው ነበርና ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው አሥረውታል፡፡ ዶር ዐብይ የእስክንድርን በባልደራስ አመጣጥ እጅጉን ስለገባቸው ነው በንዴት “ጦርነት አውጃለሁ” ያሉት፡፡ አልተዉትም ጦርነቱንም ጊዜ ጠብቀው እስክንድርንና ባልደረቦቹን በማሰር ጀምረውታል፡፡
ደርግ በ1970 ዓ.ም. ካካሄደው የቀይ ሽብር ፍጅት በቀደምትነት በፖለቲካ ውሳኔ፣ በፍየል ወጠጤ፣ በቤት ለቤት አሰሳ፣ በነጻ እርምጃ እየገፋበት የመጣውን ግድያ ነው በቀይ ሽብር ስያሜ ትውልድ የፈጀው፡፡ በዚህ ሂደቱ በበርካታዎች የሚታወሰው አረመኔው ግርማ ከበደ በየካቲት 1969 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ቀይ ሽብርን በአራት ኪሎና አካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ጀመረው፡፡ በአራት ኪሎ አካባቢ ግርማ ከበደ በእጁ የገቡትን ወጣቶች በስልጣኑ መግደሉን ስለተያያዘው በአካባቢው ወጣት ዝር ማለት አልቻለም፡፡ በቀጣይነት ከብርሃነ ሰላም ማተሚያ ቤት የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡሯን ዳሮ ነጋሽ ጨምሮ ስምንት ወገኖችን አውጥቶ ቢረሽን አበጀህ ነበር የተባለው፡፡ በቀጣይነት ከትምህርት ሚኒስትር ሊረሽናቸው ያወጣቸው ወገኖች ውስጥ የመንግስቱ ኃይለማርያም የአጎት ልጅ በመኖሩ ነው ግርማን ለእስር የዳረገው፡፡ ይህ ሰበብ ሁኖና በወቅቱ የነበረውን ሕዝባዊ ቁጣ ለማስታገስ ደርግ ወዲያውኑ ግርማ ከበደን በአደባባይ ሲረሽነው ቀይ ሽብርን ጠልቶ ሳይሆን ፍጥነቱንና ቀደም ቀደም ማለቱን ለመግታት በአኳያውም የሕዝብ ድጋፍ ያገኘ መስሎት የወሰደው እርምጃ ነበር፡፡ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የጀዋርና የበቀለ ገርባ ወደ እሥር መግባት በዘር ፍጁቱ ላይ ቀደም ቀደም ማለታቸው ሌላ ሕዝባዊ ቁጣ ይቀሰቅሳል በሚል እንጂ በአንድ ዘር የበላይነት የተገነባው ብልጽግና ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርጎ ያነጣጠረበት በተለይ የአማራ፣ ጉራጌ፣ ደቡብ ወገኖች፣ ጋምቤላ ወገኖች እልቂት አሳስቦት እንዳልሆን መናገር ይቻላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያችን ችግሮች ምንጭ መሆኑን ብንረዳም ይህን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል፤ ለመቀየር ወይም በአዲስ ለመተካት ጊዜና አሠራር ይጠይቃል፡፡ ይህንን እንቀበል፤ ነገር ግን ይህ እስኪፈፅመ ድረስና በዚሁ ሕገ መንግስትም የተደነገጉ የዜጎች መብቶች፤ በተለይ በሰላም የመኖር ዋስትና ይከበር ዘንድ፤ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ እንዚህን ጉዳዮች በጥልቀት እንዲመረምር እንጠይቃለን፡
1) በየክልሉ በተለይ ኦሮሚያ በሚባለው ወስጥ ያሉ “ኦሮሞ አይደላችሁም፣ መጤ፣ ነፍጠኛና የነፍጠኛ ዕምነት ተከታዮች ናችሁ” ለተባለው ሕዝብ መንግሥት በማያሻማ ቋንቋ ባለበት የመኖር መብቱን መግለጽና፤ ለዚህም እንሚሠራ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡ ይህ በተግባርም ከታገዘ በገዛ ሀገሩ መከራ ለሚደርስበት ለሕዝቡ ሰላምና ዋስትና ይሰጣል፡፡ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ሚናቸው ከየት እንድሆነ ያሳያል፡፡
በዚህ በኦሮሚያ ለአለፉት ሁለት ዓመታትም፤ ከዚያም በፊትም፤ የሚደረጉ የዘርና ሃይማኖት ተኮር ፍጅትና የቤት፣ የንብረትና የዕምነት ተቋማት ውድመት ዋናው ዒላማው የዘር ማጥራት መልዕክቱ፤ ከክልላቻን ውጡ፤ እንግዲህ “ይዘገያል እንጂ መች ይረሳል በደል” እንዲሉ አሁን ይህን ዕልቂት እያዩ የሚያድጉት ሕፃናት፤ ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ምን እንደሚያደርጉ መገመት ይቻላል፡፡ የፍልስጤም ወጣቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ ከልጅ ልጅ የደረሰ መፈናቀል አጥፍቶ ጠፊዎችን ፈጥሯል፡፡ የዛሬ 10፣ 20ና 30 ዓመት ኢትዮጵያችን ለዓለም መፍታት እንዳስቸገረውና 70 ዓመታት ያስቆጠረው የእሥራኤልና የፍልስጤም ዓይነት ችግር ይድረስባትን?
2) የፖለቲካ ሰዎች “ፈዴራል መንግሥቱ ደካማ ነው ክልልሎችን ለመቆጣጠር አቅም ያንሰዋል” ሲሉ ይሰማል፡፡ ሊሆንም ይችላል፤ ነገር ግን ከሁለት ዓመት በላይ ይህንን ሰበብ ማቅረብ ተገቢ አይመስለንም፡፡ እንደሚባለው የመከላከያውና ደህንነቱ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ራሱ “ለውጡን” በሚያግዝ መልኩ እንደ አዲስ ተዋቅሯል፡፡ መሬት ላይ ወደ ተራው ሕዝብ የወረደ ሰላምና መረጋጋት ግን አይታይም፡፡ ይህ የፌዴራል መንግሥቱ “አቅም ግንባታ” “ላም አለኝ በስማይ” እየሆነ ነው፤ ልክ እንደ ወያኔ “ዴሞክራሲ”፡፡
3) መንግሥትና ገዢው ብልፅግና ፓርቲ፤ አዲስ አበባ የፌዴራል ዋና ከተማ እንደሆነች፤ የማንኛውም ክልል ባለቤትነት የሌለባት መሆኑንና አዲስ አበቤውም ተረጋቶ እንዲኖር፤ ከስጋት ነፃ እንዲሆን ማድረግ ይገባዋል፡፡ በተለይ የኦሮሙማ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ከአለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በተደጋጋሚና በሚያወጧቸው መግለጫዎችና የአደባባይ ንግግሮች “አዲስ አበባ ኬኛ” ብለዋል፡፡ ይህ በከተማዋ ኗሪ ላይ ስጋት መፍጠሩ ለመንግሥት ይሳነዋል? ወይንስ ዒላማና መልዕክቱ የኦሮሚያው ዓይነት ነውና አስተሳሰቡን “ማለማመድ” ነውን?
4) ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌሎችም ባለሥልጣኖች ስለምርጫ ማውራት ጀምረዋል፤ እንግዲህ ኢትዮጵያችንን ከኮረናው ወረርሽኝ በስላም ያሻግራት እንጂ ምርጫውም ይደረስበታል፤ ነገር ግን ማሳስብ የምንፈልገው፤ ምርጫ ያለሕዝብ ቆጠራ ታማኝነትም ተቀባይነትም አይኖረውም፡፡ ለዚህ ምክንያቶቹን በሌላ ፅሁፍ እንመለስበታልን፡፡ በአጭሩ ግን በዴምክራሲ “የሕዝብ ቆጠራ (ሴንሰስ) ሥልጣንን ከገዥው ወይም አስተዳዳሪው እጅ አውጥቶ ለተገዥው ወይም ለተስተዳዳሪው ሕዝብ ይሰጣል” ይባላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለምርጫው ያለው ቁርጠኘነት አስቀድሞ መደረግ ላለበት የሕዝብ ቆጠራም መሆን ይገባዋል፤
5) የክልል “ልዩ ኃይል” ለሚባል ወታደራዊ ተቋም በዙር በዙር ምልመላ፤ ሥልጠናና ምረቃ ሲደረግ በዜና ይሰማል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከ30 ዙር በላይ ልዩ ኃይል እንደተመረቀ ተነግሯል፡፡ በኢትዮጵያችን በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚባለው ያለው ሰላምና አለመረጋጋት፤ የክልልና ፌዴራል መንግሥት ሃላፊዎች ግድያ፤ የባንኮች በጠራራ ፀሐይ ዘረፋና፤ በይበልጥ ግና ዘርና ሃይማኖት ተኮር ፍጅት ጋብ ሲል አይስተዋልም፤ እንዲያውም ሲባባስ ነው የሚታየው፡፡ ታዲያ ይሄ “ልዩ ኃይል” ተግባሩና ፋይዳው ምንድን ነው? በጀቱስ ከየት ነው የሚመጣው? መንግስት ይህንን “ልዩ ኃይል” በመከላከያ ማስገባትና፤ ተጨማሪ ምልመላና ስልጠናዎችን ማስቆም ይገባዋል፤
6) ፍትህ ሲፈፀም መታየት አለበት የሚል ብሂል አለ፡፡ አሁን በኢትዮጵያችን ባለው ሁኔታ ይህ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡ አንድ ጉዳይ ለማንሳት ብቻ፤ በጅማ የሚገኝ ሆቴልን በመኪናና በባጃጅ ተጓጉዞ የመጣ ነውጠኛ ቡድን ከ70 በላይ በሚሆኑ መኝታ ክፍሎች በእያንዳዳቸው ውስጥ ቤንዚን እያርከፈፈከፈ በእሳት አጋይቷል፡፡ እንግዲህ አቃጣዩ፤ መኪናና ባጃጅ አቅራቢው፤ ሾፌሩ፤ ቤንዚን አዳዩ በቀን ይህን ወንጀል ሠርተው ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ተመልሰው ማስፈራሮና ዛቻ ሲያደርጉ ፍትህ እንኳን ተፈፀመ፤ ተጀመረ ይባላል? እንዲህ ዓይነት ወንበዴዋች ላይ ሕግ እርምጃ ሲወሰድ ነው ፍትህ ሲፈፀም ታየ የሚባለው፤ የሚታየው ግን ተስፋ ሰጪ አይደለም፤
ሁልጊዜም ስለፍትህ ስንጮህ ዳግም እንዳይደገም ነው፡፡ ትውልድ የመተረው ቀይ ሽብር መሪ ፋሽስቱ መንግሥቱ ኃ/ማርያምና ግብረ አበሮቹ ጉዳይ ሕግ አይቶት የሕግ ውሳኔ ተግባራዊ ቢሆን ዳግም ፍጅት ባልተከሰተ፡፡ ኢሕአዴግ ገና ሥልጣን እንደተቆጣጠረ በኦነግ የተደረገው የበደኖና አርባ ጉጉ ፍጅት ሕግ አይቶት ቢሆን በየጊዜው የሚከሰቱ ፍጅቶች ባልቀጠሉ፡፡ መርሳት ችግራችን ሆነና ቢዘነጋም የሕግ ባለሙያዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ በመረጃ አስደግፈው የጮሁበት 1997 ዓ.ም. እልቂት የሕግ ፋይል ተከፍቶለት ቢሆን ያለ ሕግ ግድያ ዳግም ባልተደገመ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ ዘመንም ለሥልጣን እንደበቁ “የቀን ጅብ” ተብሎ ተፎክሮና የሕዝብን ልብ አንጠልጥሎ ወንጀለኞችን ከለላ ከመስጠት ይልቅ ወደ ሕግ ቀርበው ቢሆን የቡራዮና የለገጣፎ እልቂትና መፈናቀል ባልተከሰተ፡፡ የለገጣፎን መፈናቀል አልሰማሁም በማለት፣ በቡራዮ እልቂት ተከላካይ ወጣቶችን ለእስር ከመዳረግ አግባብ ያለው የፍርድ ሂደት ቢያየው ሌሎች ባልተቀጣጠሉ ነበር፡፡ እና ይህ ሁሉ ትንታኔ በሀገር ሀብት ውድመትና በሕዝብ ላይ የሚደረገው ፍጅት ተጠያቂው ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርጎ በዘርና ቋንቋ ሀገር ከፋፍሎ እያስተዳደረ ያለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ መሆኑን ደፍሮ ለመናገርና ሕዝብን ለማስተማር ዝግጁ ሲኮን መፍትሄ የሆነውም ትግል እንዴት ሀገርና ሕዝብ ሊያድን እንደሚችል ይተለማል፡፡ ትግል ለማካሄድ በቅድሚያ ማንን እንደሚታገሉ ማወቅ ይጠይቃልና፡፡ ዶክተር ዐብይ አሕመድ በራሳቸው አካሄድ የሕዝቡን ድጋፍና ስሜት እጅጉን ጎድተውታል፡፡ ጉዳያችን ከሀገራችን፣ ጉዳያችን ከሕዝባችን ነውና ወገኖቻችን እየታረዱ፣ ታርደው እየተቆራረጡ፣ መላ ቤተሰብ ከነሕይወታቸው እየተቃጠሉ፣ አስከሬን መሬት ለመሬት እየተጎተተ፣ እርጉዞች እየተተለተሉ፣ ያውም በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ መናፈሻ ግንባታ ብሎ ውስኪ ለመራጨት፣ ሽንጥ ለመቁረጥ ዕቅድ ማውጣት እውን በእውቀት ልቆ መገኘት ነው ወይስ ጊዜ የሚያሳየን ድብቅ ግብ አዝሏል?
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን!
የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ከዓለማችን ይርቅልን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን!!!
አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ
ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. (August 19, 2020)
ማሳሰቢያ ፡
- ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
- «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።
ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com
ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com
ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin