ከ 57 ደቂቃዎች በፊት

አርማ

በኦሮሚያ ለተቃውሞ በተጠሩ ሰልፎች ምክንያት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።

በክልሉ በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ ባሉ ከተሞች የሰዎች ህይወት ማለፉን ኮሚሽኑ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ እንደደረሰውም በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

የሰዎች ህይወት ያለፈውም የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ መሆኑንም ጠቅሷል።

‹‹የመንግስት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ስራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው›› የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ መናገራቸውም በመግለጫው ተካቷል።

በዚህ አመት በኦሮሚያ ክልል ከተከሰቱ ግድያዎች ይህ መታከሉ አሳሳቢና አሳዛኝም ነው ሲል ገልፆታል

‹‹የኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ በሚዲያዎችና በሪፖርቶች የተለያየ መረጃ እንደወጣ ያስታወቀው መግለጫው ኢሰመኮ ስለደረሰው ሞትና ጉዳት መጠን ለማረጋገጥ ከነዋሪዎች፣ አይን እማኞች፣ ሆስፒታሎችና አስተዳር አካላት መረጃ በማሰባሰብ ላይ ነው ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢሰመኮ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ጉዳዩን ለማጣራት በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪውን አቅርቧል

በኦሮሚያ ክልል የሃረርጌ ዞኖች፣ በምዕራብ አርሲ ዞን እና በድሬዳዋ ከተማ ባጋጠሙ ግጭቶች ቢያንስ 4 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ፖሊስ፣ የሆስፒታል ምንጮች እና የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።