August 20, 2020

በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ለባለፉት ሁለት አመታት ሀገራችን የሄደችበት የለውጥ ጉዞ በብዙዎች ትግል እና መስዋዕትነት የመጣ እንደመሆኑ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም በኦህዴድ/ብልጽግና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ የዲሞክራሲ ሽግግሩ እንደተደናቀፈ እና በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በልሂቃን መካከል ሊፈጠር ይችል የነበረው ብሔራዊ መግባባት ሊጀመር እንዳልቻለ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል፡፡–

ዜጎችን አስከፊ ሰቆቃ ውስጥ ከቶ የነበረው የህወሀት አገዛዝ እንዲያበቃ መጠነ ሰፊ ትግል ሲካሄድ መቆየቱ ያታወቃል፡፡ ይህንንም ስርዓት ለመቀየር ሁሉን አቀፍ ትግል ሲደረግ በተለይም፣ ምርጫ 2007ትን በሙሉ አሸንፌያለሁ ካላ በኃላ ከ2008 ጀምሮ ህዝብ ይደርስበት የነበረውን ወደር የማይገኝለት ግፍ ገፈቱ ሞልቶ የፈሰሰበት እና በቃኝ ብሎ ሕዝብ የተነሳበት ወቅት ነበር፡፡ በሀገራችን ለውጥ ለማምጣት የሰብዓዊ ተሟጋቾች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትና መሪዎች የተገደሉበት፣ አካላቸውን ያጡበት ለዘመናት እስርና እንግልት የቀመሱበት እንዲሁም ለስደት ተዳርገውበት የነበረ እልህ አስጨራሽ ትግል እንደነበረ ማንም የማይዘነጋው ሀቅ ነው፡፡ ለህወሀት/ኢህአዴግ ግፍ አገዛዝ አልንበረከክ ብለው በጽኑ የታገሉ ሰማዕታት ትግል ቀንዲል፣ ወጣቱን ትውልድ በይበልጥ በማነሳሳት የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎችን ዳር እስከዳር አንግበው በመውጣት አንባገነኑን ስርዓት አስገድደው ለለውጥ እንዲንበረከክ አድርገውታል፡፡–ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፉት ሁለት አመታት ህዝቡ ተስፋ ሰንቆበት የነበረውን የሽግግር ሂደት ፣በኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ መንግስት ተፈትኖ የወደቀበት ሆኗል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት እና ከዚያ በኋላ የለውጡ ሂደት ሙሉ በሙሉ የባቡሩን ሃዲድ የሳተባቸውን ዋነኛ ምክንያቶች ባልደራስ እንደሚከተለው ይነቅሳል፡-–1 ኦህዴድ/ብልጽግና አዲስ አበባን እና ሌሎች አካባቢዎችን በቁጥጥር ስር ስለማድረጉ–ኦህዴድ/ብልጽግና የባህሪ አባቱ ከሆነው ህወሀት ከወሰደው መጥፎ ድንበር እና ባህል ማጥፋት ስራ መካከል የነባር ህዝቦችን መኖሪያ መጠቅለል እና ማንነታቸውን ማጥፋት ነው፡፡ ይህ በመሣሪያ የሚደረግ የተስፋፊነት ተግባር በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ላይ አጠናክረው ለመያያዛቸው የሰሞኑ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች መሬቱም ሰማዩም የኔ ብቻ ነው የሚለውን የኦህዴድ/ብልጽግና ጉዞ ሲቃወም መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የትግሉን ማዕከልም በዚህ አግላይ የተስፋፊነት አካሄድን ለማስቀረት በሚያስችልበት አኳሃን እንዲሆን አድርጓል፡፡ አቶ ሽመልስ የኦህዴድ/ብልጽግና “የማሳመን” እና “የማምታታት ፖለቲካ” እንደሚያብራሩት አዲስ አበባ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ጌድዖ፣ ሲዳማ፣ አማራ ክልል የመሳሰሉት የሚገኙበት ሲሆን፣ በህገወጥም ሆነ በማንኛውም መንገድ መሬቶቹን ህዝቡን አፈናቅሎ እና ገሎ ለመያዝ እየሰሩ መሆናቸውን ያለምንም እፍረት በግልጽ በመድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡ በዚህ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የናወዙት ኢህዴዶች/ብልጽግና ፖሊሲ ላይ ባልደራስ ከዚህ ቀደም በነበረው ጠንካራ አቋም ምክንያት መሪዎቹ እና አባላቶቹ በውሸት ውንጀላ እንዲታሰሩ መደረጋቸው ይታወቃል፤ ድምጽ አልባ የሆነው ወገን እና በሀገሩ ላይ ተስፋ እንዲያጣ የተደረገው ትውልድ የሆነው ባልደራስ፣ በግዛት ተስፋፊዎች የማሸማቀቅ እርምጃ ሸብረክ ሳይል ዛሬም እንደትናንቱ አቋሙን አጠናክሮ ይገልጻል፡፡–‹‹የአዲስ አበባን ህዝብ ዴሞግራፊ መቀየር›› ዓላማው በማድረግ በገፍ ከኦሮሚያ ወደ ከተማዋ በማስገባት እና የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ በህገወጥ መንገድ ሲያድሉ እንደነበር እና ይህንን ተግባር መቃወማችን ይታወሳል፡፡ አዲስ አበባ ከተማችን የሀገራችን መዲና ከመሆንም አልፋ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነች፣የተለያዩ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት ማዕከል፣የሀገራችን የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ማዕከልነትን አካታ የያዘች፤ እንዲሁም የዘመናዊ ኢትዮጵያ አባት የሆኑት የአድዋ ጀግና ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ የቆረቆሯት፤ የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነች አለማቀፍ ከተማ ናት፡፡ በተሳሳተ እና በተንኮል የፖለቲካ ግንዛቤ የልዩ ጥቅም አካፋይ እና ሰጪ እንድትሆን በህገ መንግስቱ የተሰነቀረባት የኦህዴድ ጡት አባት በነበረው ህወሀትና ኦነግ ነበር፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የታገሉት የተረኝነት አካሄድ፣ ኦህዴድ/ብልጽጋና መልሰው ለማንበር የሚያደርጉትን ጉዞ፣ ትግላችን ከበፊቱ በባሰ አንባገነን እና ለህዝቦች ተቻችሎ እና አብሮ መኖር ደንታ የሌለው ስርዓት እንደገጠመን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው፡፡–በአዲስ አበባ የተከፈተው ተራ የግለሰቦች ተረኝነት ስሜት ብቻ ሳይሆን ‹‹ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው›› የሚል አስተሳሰብ እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ መሬትን በወረራ መልክ ሲከፋፈሉ፣ የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ከኑሮው ላይ ቆጥቦ ያስገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት ተሰርቆ በተረኝነት ለኦህዴድ/ብልጽግና የፓርቲው አባላት ሲያድሉ፣ በተዘዋዋሪ ፍንድ ለከተማዋ ነዋሪ ወጣቶች የሚሰጠውን ብድር ከልክሎ ‹‹ቄሮ›› በሚል ለሽብር ተግባር ላዘጋጁት መንጋ ሲያድሉ በጥብቅ ተቃውመናቸዋል፣ ዋጋም ከፍለንበታል፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ ሲጋለጥባቸውና አልሳካልቸው ሲል አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት የከተማውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ፋይዳ ማጥፋት ቀጣዩ አማራጭ ሴራቸው እንደሆነ ከወዲሁ አስገንዝበውናል፡፡ ጥፋትን እንጂ ልማትን የማይችለው ኦህዴድ/ብልጽግና፣ በሁሉም ኢትዮጵያኖች ድካምና ኃብት የተገነባችውን አዲስ አበባ፣ የበለጠ ገናና ከተማ ከማድረግ ፈንታ ለማስመሰል ባልዘለለ ለማሽመድመድ ማቀዱ፣ ያለበትን የዝቅተኝነት እና ተሸናፊነት ስነ ልቦና ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ በምንም ሁኔታ የአንድ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በሌሎች ብሔረሰቦች መቃብር ሊገነባ አይገባም ብሎ አበክሮ ያምናል፡፡–የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን በራሱ፣ ክልል እስከመሆን የማስተዳደር ህጋዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና ታሪካዊ መብት ባለቤት ነው፡፡ ለዚህ ህዝባዊ ጥያቄ መልስ ደግሞ ከማንም ጫማ ስር ወድቀን እና ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ተመላልሰን የምናስከብረው ሳይሆን፣ በህዝብ ትግል ገዢዎችን አስገድዶ የሚረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡ በልመና የሚገኝ መብት እንደሌለ የሰው ልጅ ታሪክ ጉዞ ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ አንጻር ትግላችን፣ አንዱ ጨቋኝ ሄዶ፣ ሌላኛው ተረኛ በመምጣቱ የሚመለስ ሳይሆን ህዝባችንን የሥልጣን ባለቤት በማድረግ፣ የሚፈልገውን በምርጫ ካርዱ እንዲመርጥ ስናደርገው ብቻ የሚመለስ እንደሆነ እንረዳለን፡፡በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የዴሞግራፊ ለውጡን 37 ከመቶ ማድረሳቸውንና “ዝም ብላችሁ ጠብቁን ከጥቂት ግዜ በኃላ የእኛ እናደርገዋለን” የሚለው የዘር ማጥፋት ንግግር፣ የኦህዴድ/ብልጽግና መሪዎችን መዳረሻ ፍንትው አድርጎልናል፡፡ ከዚህ ቀደም፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሀብትን ህወሀት ሲመዘብርና የግዛት ማስፋፋት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ለሚያስታውስ፣ የዛሬዎቹ ተረኞች ዓላማ በይበልጥ የሚያሳስብ ይሆናል፡፡ ክልሉ የአባይ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ የሚገኝበት አካባቢ መሆኑንና በተፈጥሮ ሀብቱ እጅግ የበለጸገ መሆኑ ደግሞ የሰዎቹ ያልጠግብ ባይነት በእጅጉ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ማንነታቸው እየተመረጠ የሚፈጸምባቸው ግድያ፣ዝርፍያና ማፈናቀል በኦህዴድ/ብልጽግና የተመራ መሆኑን ፍንትው ያለ ምስል እንዲኖረን ያደርጋል፡፡–ሐረር፣ በሀገራችን ረጅም ታሪክ፣ባህልና ማንነት ያለው ህዝብ መኖሪያ ከተማ ነበረች፡፡ የትልልቅ ኢስላማዊ ትምህርት ቤቶች ማዕከል በመሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍል ተማሪዎችን እና ጎብኚዎችን ትቀበል የነበረችው ታሪካዊ ከተማ፣ ዛሬ ቁልቁል ወርዳ ውሃና መሠረታዊ ፍጆታ ማግኘት የህዝቡ ቀን ተቀን ፈተና ሆኗል፡፡ ይህች ስለስልጣኔዋ ብዙ የስነ ጥበብ ሰዎች የተቀኙላት እና የውጭ ጸሃፍት ታሪኳን እንዲያስቀሩ ያስገደደች ከተማ፣ በ50፣50፣0 ቀመር ምክንያት ምስራቃዊ የመክሸፍ ምልክት ሆናለች፡፡ ለውጡ መጣ ከተባለ ጀምሮ በሚደርስባቸው ሊገለጽ የማይችል በደል ውስጥም ሆነው፣ መብታቸውን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን የክልሉን ነዋሪዎች ወኔ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ያደንቃል፡፡–ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁ በራስ ገዝነት ትተዳደር የነበረች የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈርጥ ከተማ የነበረች ሲሆን 40፣40፣20 የሚባል አፓርታይዳዊ ስርዓት ከተዘረጋባት በኃላ እንኳን የአባቶቿን ወርቃማ ዘመን ልታስመልስ ይቅርና፣ ልጆቿ በሰላም ወጥተው የማይገቡባት ምድር ሆናለች፡፡ ነዋሪው ህዝብ መሪዎቹን መምረጥ ትቶ ማንነት ተቆጥሮ እንዲመረጥበት ተሰፍታለች፡፡ ለፍቶ አዳሪ የባጃጅ ሹፌር፣ የ20 እና 30 ሺ ብር ቅጣት እየተጣለባት፣ ወደ ጋማ ከብት ትራንስፖርት ስርዓት እንድትመለስ ለማድረግ ገዢው ፓርቲ እየሰራ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል ለተፈጸመ ድርጊት፣ ልጆቿች ፍርድ ቤት ሳያውቃቸው እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ወንድሞቻቸን ላይ ከህግ ውጪ በገዢዎች የሚደርሰውን በደል ባልደራስ በጽኑ ይቃወማል፡፡ ለምስራቁ ኢትዮጵያ ሰቆቃ፣ ከነሽመልስ የጥላቻ እርምጃ በስተቀር፣ ማንም ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል እንረዳለን፡፡–ከ800 ሺ የሚበልጥ የጌድዎ ህዝብ በለውጡ ሰሞን እንዲፈናቀል መደረጉ ይታወሳል፡፡ ያ ተግባር እንዳይሰማ መሸሸጉ አልበቃ ብሎ ለህዝቡም አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራ አልተከናወነም፡፡ ባልደራስ በጌድዎ ህዝብ ላይ ጽንፈኞች ያደረሱትን በደል ሲያስታውስ በእጅጉ ያዝናል፡፡ አላማውም ጌዲዮን ከደቡቡ ክልል ገንጥሎ በኦሮሚያ ክልል ስር ለማድረግ መሆኑን ስለሚገነዘብ ይህን አላማ ባልደራስ አጥብቆ ይኮንናል፡፡–2. ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረበውን ጥያቄ እና የመንግስት የኃይል እርምጃ–በህገ-መንግስቱ መሰረት የክልልነት ጥያቄ ያነሱ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች እንዳሉ ይታወቃል፤ይህን ጥያቄ በህጋዊ መንገድ መፍታት ባለመቻሉ በተለይ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ወቅት የብዙ ዜጎች ህይወት የቀጠፈ፣ሀብት ንብረት ካወደመ በኃላ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መደረጉ እና ሲዳማ ክልል መሆኑ የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው፡፡ እንደ ሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ዞኖች ይገኛሉ፡፡ ይህን ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ በአግባቡ ለመፍታት ከመሞከር ፈንታ ጥግ ጥጉን ሲሽከረከር የከረመው ኦህዴድ/ብልጽግና የህዝብ ጥቅም ከማስከበር እና ጥያቄውን በአግባቡ ከመፍታት ይልቅ የኦህዴደ/ብልጽግናን የፖለቲካ የበላይነት ለተቀበሉ ዞኖች የክልልነት መብትን መስጠት፣ ይህን ላልተቀበሉ ደግሞ የክልልነት መብትን የመንፈግ አካሄድን በመከተል ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በቅርቡ ኦህዴድ/ብልጽግና የወላይታን ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ለማፈን በመከላከያ ሰራዊት ትጥቅ ካልያዙ ሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል ወደ 36 የሚጠጉ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ተደርጓል፡፡–የወላይታ ህዝብ ያነሳውን የክልልነት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሄደበት ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የህዝቡን ስልጡንነት ያሳየና የሚያስመሰግነው ነው፡፡ በኦሮሚያ ከተሞች ዜጎች ምንነታቸው እና ሀይማኖታቸው እየተመረጡ የዘር ፍጅት ሲፈጸምባቸው፣ ትዕዛዝ አልተሰጠኝም ብሎ ሲመለከት የነበረው የኦህዴድ/ብልጽግና የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት ‹‹ሕገ ወጥ ስብሰባ ሊያደርጉ ሲሉ›› ብሎ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ላይ የፈጸመው እስራት እና ተቃውሞአቸውን ያሰሙት ሰላማዊ ወንድሞቻችን ላይ መከላከያ ሰራዊቱ የፈጸመው እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ላለንበት አስከፊ ተረኛነትና አንባገነናዊ ስርዓት ማሳያ ሆኗል፡፡ ብዙ የተወራለት የኦህዴድ/ብልጽግና መከላከያ “ሪፎርም” ቀደም ሲል ከነበረው የገዢ ፓርቲ ፍላጎት አስፈፃሚነት በምን አይነት መንገድ እንደሚሻል በተግባር ሊያሳየን አልቻለም፡፡–ከዚህ በተቃራኒ የወላይታ ህዝብ መብቱን ለማስከበር ያሳየው ጽናት ለሌሎች ዞኖች ትምህርት፣ሰላማዊነቱም ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ባልደራስ እምነቱ ሲሆን ወደፊትም የወላይታ ህዝብ ላነሳው የክልልነት ጥያቄ በዝህ ቅቡልነት በሌለው ሕገ-መንግስት እስከተዳደርን ጊዜ ድረስ ባልደራስ ያለማወላወል ከመደገፉም በተጨማሪ ለሲዳማ እንደተደረገው ሕዝቡ የሪፈረንደም መብት ተሰጥቶት ጥያቄው በዚህ አግባብ እልባት እንዲያገኝ ይጠይቃል፡፡ በወላይታ ህዝብ ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ የወሰደው ርምጃ ፍጹም ተመጣጣኝ ያልሆነ እና ንጹሀን ሕጻናት ላይ ጭምር የተደረገ ግፍ በአስቸኳይ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ እና ትዕዛዝ የሰጡ ኃላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ባልደራስ በጽኑ የሚታገልበት ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል፡፡–የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ–የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፊደል ቀርፃ ትምህርት ያስፋፋች የታሪክ መዘክር በመሆን የኢትዮጵያ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲወራረስ ያደረገች የአገር ባለውለታ የሆነች ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ ናት፡፡ በዚህ ዘመን መንግስት እና ሀይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በቅጡ ያልተረዱ የኦህዴድ/ብልጽግና አመራሮች የሚያንጸባርቁት ስርዓት ያጣ እርምጃ የቤተ-ክርስቲያኑን ምዕመን ለስጋት ያደረገ እኩይ ተግባር ሆኗል፡፡ በቅርቡ ኦህዴድ/ብልጽግና ለከፍተኛ አመራሮቹ በሚሰጣቸው የስልጠና ሰነዶች ላይ ጭምር ሀይማኖቷ ለሀገር ዕድገት ጎታች እንደሆነች በገሀድ የተመለከተ መሆኑ፣ በእምነቱ እና በእምነቱ ተከታዮች ላይ ጥላቻን ያነገበ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በዚህ እና መሰል ማሳያዎች በተለይ ስርዓቱ ወደስልጣን ከመጣበት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ46 በላይ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ልብ ይሏል፡፡ በእምነቱ ተከታዮች ላይ በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ዘግናኝ ግድያዎች ሲፈጸሙ ተመልክተናል፡፡ ለዚህም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂዎቹ የስርዓቱ መሪዎች ቅጥ ያጣ፣ በጽንፈኛ ብሔረተኝነት ስሜት የተበከለ ንግግር እና ዳተኛ የህግ ማስከበር ሂደት እንደሆነ ማንም የሚገነዘበው ሀቅ ነው፡፡–የሀገራችንን ፖለቲካ ማረጋጋት የሚቻለው አሮጌና የተሳሳተ የጥላቻ የታሪክ ትርክት ላይ በማላዘን ሳይሆን ሌት ከቀን ለሥራ በሚታትር የፖለቲካ አመራር እና በሚያወጣቸው ጠንካራ የፖሊሲ አማራጮች ብቻ ነው፡፡ ሁሉን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ፖሊሲ የሌላቸው የፖለቲካ አመራሮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና “ነፍጠኛ” በሚል የቅጽል ስም የሚጠራዉን የአማራ ማህበረሰብ ለውድቀታቸው የጦስ ዶሮ ለማድረግ ተነስተዋል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ማንኛውም እምነት ከመንግስት ጋር ተለይቶ እና ነጻነቱ ተጠብቆለት መካሄድ እንደለበት ያምናል፡፡ በመንግስት የሚጠላም ሆነ በተለየ የሚመረጥ እምነትም ሆነ ማህበረሰብ ሊኖር አይገባም ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ቤተክርስቲያንቷን በተለየ የጥቃት ኢላማ በማድረግ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ የመንግስት እንዳላየ ማለፉ በእጅጉ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ዛሬ በሷ ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ነገ በሌሎች ላይም እንዳማይደገም ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡–አማርኛ ቋንቋን እና የአማራ ህዝብን በተመለከተ–አቶ ሽመልስ አብዲሳ አማርኛ ቋንቋ ቁልቁል እየወረደ፣ በተቃራኒው ደግሞ ኦሮምኛ ቋንቋ ሽቅብ እየተጓዘ እንደሆነ በንግግራቸው መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ የኦሮምኛ ቋንቋ በማደጉ አይኑ የሚቀላ ባይኖርም፣ አማርኛን ጥሎ ኦሮምኛን አንጠልጥሎ ለመሄድ ኦህዴድ/ብልጽግና የቀየሰው “የቋንቋ ፖሊሲ” ኢትዮጵያን ያፈራርሳት ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ቅዥት ነው፡፡ ብቸኛ የጥቁር ህዝቦችን ፊደል የሚጠቀም ቋንቋ በዚህ ደረጃ መጠላቱ፣ ድርጅታቸው ከራሳቸው ማንነት ጋር ጭምር የተጣሉ ድኩማኖች ስብስብ መሆኑን ከሚያሳይ በስተቀር ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፡፡–ሌሎች አገር በቀል ልሳኖች በስራ ቋንቋነት ጥቅም ላይ መዋላቸው ለህብረ ብሄር አገር ግንባታ ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ ሀገር በሌሎች ትልቅነት ውስጥ የራስን ትልቅነት በማከል እየተገነባ የሚሄድ የማያልቅ የትውልዶች ቅብብል ጉዞ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ ደግሞ ተወደደም ተጠላም ሀገሩን ድልድይ ሆኖ ያያያዘ ማጣበቂያ ነው፡፡ እሱን ለማላቀቅ መሞከር ሀገሩን ለማፍረስ እንደሚደረግ ጥረት ብቻ ሳይሆን የምንረዳው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ የላቸውም የሚለውን የዘረኞች አስተሳሰብ ፉርሽ መሆኑን የምናሳይበትን መብራት ለማጥፋት እንደመሞከር የሚቆጠር አድርገን ነው፡፡–የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የጥላቻ ንግግር ትልቅ ትኩረት ያደረገው የአማራ ህዝብ ላይ ነው፡፡ ትላንትም ገለን ቀብረነዋል ሲባል የነበረው ህዝብ፣ ዛሬም የዚህ ጥላቻ ሰለባ ለማድረግ የሚደረገው ሩጫ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ አቶ ሽመልስ የሚመሩት ክልል በሳቸው የሥልጣን ዘመን፣ የትናንት የአማራ መከራውን የሚያስንቅ የዘር ማጥፋት ፍጅት እየተፈጸመበት እንደሆነ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ እየዘገቡት ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር የአማራ ህዝብ ሞቶ ባቀናት ሀገሩ እና የአባቶቹ አጽመ ርስት በሆነው መሬት ላይ መጤ ነህ ውጣ መባሉ የዚያው ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔረተኞች የሚመሩበት የሃሰት የታሪክ ትርክት አካል መሆኑን ባልደራስ ይረዳል፡፡ እንደዚህ አይነት አካሄድ ማብቃት ካልቻለ፣ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ የአማራ ህዘብ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ለህልውናው የሚያደርገውን ትግል ባልደራስ ይደግፋል፡፡ የአማራ ህዝብ ትግል ውጤታማ ሊሆን የሚችለው አባቶች ባወረሱት አገራዊ ባንዲራ ስር፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የአገሪቱ እኩል ባለመብት ማድረግ ሲቻል እና በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት እውን ሲሆን ነው ብሎ ባልደራስ ያምናል፡፡–ኦህዴድ/ብልጽግና ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትህ የነገሰባት እና ዜጎች በአገራቸው የሚኮሩባት ለማድረግ በእጁ የገባውን የታሪክ አጋጣሚ በሚገባ ይጠቀምበት ዘንድ ምክሩን ለመለገስ ይፈልጋል፡፡ የሚከተለውና ከህወሐት የወረሰው የተረኝነት ፖለቲካ የማያዋጣና ፍጹም የማይጠቅም እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባል፡፡–ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በአገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደት መጨናገፍ ከኦህዴድ/ብልጽግና እኩል ሌሎች ህዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ይመለከታል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ አገር እየተገፉ ላሉት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለሚታረዱት አማራ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ፣ ወላይታ እና ሌሎች ህዝቦች የኦህዴድ/ብልጽግና አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ አይን ያወጣ የፖለቲካ ስህተት ሲሰራ እያዩ፣ ስህተቱን በግልጽ ማረም ሲገባ፣ በአጎብዳጅነት ለአገር አንድነት ጠንቅ የሆነ የተሳሳተ የመንግስት ፖሊሲን የማይተቹ የ “ተቃዋሚ” የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር እንደሆኑ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በመጨረሻም ኦህዴድ/ብልጽግና በአቶ ሽመልስ አብዲሳ በኩል የተናገረው ንግግር የኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲና በዚሁ ፓርቲ የሚመራው መንግስት ፖሊሲ ስለመሆኑ ባልደራስ ጥርጥር የለውም፡፡–ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተቋቋመበት ምክንያት ኢ-ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ የለውጥ መንግስት እየተባለ የሚጠራውን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የመቃወም ፍላጎት አንግቦ አይደለም፡፡ ፓርቲያችን የተቋቋመበት ምክንያት ብልጽግና የሚከተላቸው ፖሊሲዎች በተረኛነት ፖለቲካ የሚመሩ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት የሚያፋልሱ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት፣አማራጭ ፖሊሲዎቹን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአዲስ አበባ ሕዝብ አቅርቦ የከተማው ሕዝብ ከስጋት ተላቆ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ተጎናጽፎ እና የዜግነት መብቱን አስከብሮ ባልተከፋፈለ ልቦና የኑሮውን ሁኔታ ሊያሻሽል የሚችልበትን አካሄድ እንዲከተል ለማድረግ ነው፡፡–የኦህዴድ/ብልጽግና አካሄድ በተረኛነት ፖለቲካ የሚመራ ነው ስንል ከተጨባጭ መረጃ በመነሳት እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆንን ብቻ የምናነሳው ተቃውሞ አይደለም፡፡ ጠቅለል ካለው አገራዊ ጉዳይ ስንነሳ የኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ የሚከተለው የፖለቲካ አመለካከት ጽንፈኛ የሆኑ የኦሮሞ ብሔረተኞች ከሚያራምዱት የኦሮሙማነት አመለካከት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ኦህዴድ/ብልጽግና ልክ እንደ ኦነግ ኢትዮጵያን በገዳ ፖለቲካ መርህ መምራት የሚፈልግ፣ በአማርኛ ቋንቋ ኪሳራ የኦሮምኛ ቋንቋን ለማፋፋት የሚፈልግ፣ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ከተማ ሳትሆን የኦሮሚያ አካል እንደሆነች የሚያምንና ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህንን የፖለቲካ አላማውን ያለማወላወል በተግባር ላይ ሲያውል የቆየ የፖለቲካ ድርጅት ስለመሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን አስረጂዎች ማቅረብ ይቻላል፡-–1ኛ/ ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ ጊዜያት በድምሩ ወደ 43.000 የሚጠጉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በልማት ተነሺ ለሆኑ ኦሮሙማዎች በሚል ሽፋን “ለኦሮሞ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው” ማንነትን መመዘኛ ባደረገ መመሪያ መሰረት አከፋፍሏል፡፡ እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤት የሌላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቆጥበው የሰሯቸውና ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በእጣ እንረከባለን ብለው በጉጉት ሲጠባበቁ ከነበሩ አዲስ አበቤዎች የተነጠቁ ናቸው፡፡ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር በጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ምድር ቤቶችን አያካትትም፡፡ ቁጥራቸው የማይናቅ ምድር ቤቶች “የኦሮሞ አርሶ አደር ልጆች”ን አንድ ለአምስት በማደራጀት የተከፋፈሉ ናቸው፡፡–2ኛ/ በደርግ ጊዜም ሆነ በህወሐት ዘመን የአዲስ አበባ ስፋት ወደ 54.000 ሄከታር የሚጠጋ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት የኦሮሞ ወጣቶችን ተቃውሞ ቀሰቀሰ የተባለለትን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጥናት ለመከለስ በሚል ከከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር የተውጣጡ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው በሚከተለው የተረኝነት ፖለቲካ የተቃኘው ጥናት የአዲስ አበባን ከተማ ስፋት ቀደም ሲል ከነበረበት 54.000 ሄክታር ወደ 43.000 ሄክታር በመቀነስ፣ የማስፋፊያ ስራ ከሚከናወንባቸው 5 የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ማለትም ከየካ፣ ከቦሌ፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ከኮልፌ ቀራኒዮ፣ ከአቃቂ ክፍለ ከተሞች 30 ወረዳዎች ወደ ኦሮሚያ ለማካለል ታቅዶ፣ በነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ያሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በየጊዜው በአስተዳደሩ ትዕዛዝ በኃይል እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡–3ኛ/ የማስፋፊያ ልማት በማይካሄድባቸው የመሃል አዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ክፍትና ኪስ ቦታዎች ለገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች እየተሰጡ ነው፡፡ በሌላ በኩል የማስፋፊያ ልማት በሚካሄድባቸው ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ባዶ መሬቶች በወረዳ አስተዳዳሪዎች በተሰጠ ቀጭን የመስተዳድሩ ትዕዛዝ መሰረት “በኦሮሞ ወጣቶች” እና የገዢው ፓርቲ የወረዳ ካድሬዎች በስፋት እየተወረረ ይገኛል፡፡–4ኛ/ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስር ከሚገኙ የልማት መስሪያ ቤቶች ውስጥ አብዛኞቹ በኦህዴደ/ብልጽግና የተንሰራፋ አመራር ስር ወድቀዋል፡፡5ኛ/ አህዴድ/ብልጽግና በመሬት ወረራው አማካኝነት ቦታ እንዲያገኙ ለተደረጉ፣ ይሁንና ከሌላ የኦሮሚያ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ለተደረጉ የማህበረቡ አባላት መታወቂያ በስፋት የማደል እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው፡፡–6ኛ/ በአዲስ አበባ ቻርተር መሰረት የከተማው ከንቲባ በከተማው ሕዝብ ከተመረጡ ምክር ቤት መካከል መመረጥ ሲገባው፣ በኦሮሚያ የሞግዚት አስተዳደር መርሆነት የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው አዲስ አበባን በከንቲባነት ሲመራ ቆይቷል፡፡–7ኛ/ ምክር ቤቱም የተመረጠበትን የጊዜ ገደብ በተደጋጋሚ የጨረሰ ቢሆንም አለ ምርጫ በስልጣን ላይ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡እነዚህና ሌሎች ተጨማሪ ድርጊቶች በገሃድ ገዢው የኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ የተገበራቸው በተረኛነት መንፈስ እየተከናወኑ ያሉ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡–ለእነዚህ ኦህዴድ/ብልጽግና ለሚያራምዳቸው በተረኛነት መንፈስ ለተቃኙ ፖሊሲዎች ባልደራስ መፍትሄ ይሆናሉ ብሎ የሚያቀርባቸው የፖለቲካ እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡–1ኛ/ በአጭሩ ጊዜ አዲስ አበባ ከቻርተር ከተማነት ወደ ክልልነት እንድታድግ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡–2ኛ/ ለዘለቄታው አዲስ አበባ ከሞግዚት አስተዳደር ተላቃ የከተማው ነዋሪ ሕዝብ በመረጠው ፓርቲ ስር እንድትተዳደር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡–በአጠቃላይ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች መፍታት ሲያቅተውና መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣት ሲያቅተው ባለስልጣን ከአንዱ መ/ቤት ወደ ሌላው ሲያዛውር ይታያል፡፡ የአዲስ አበባ ችግር ከመነሻው መዋቅራዊ ከመሆኑም ባሻገር ታላቋን አዲስ አበባን የሚመሩ ከንቲባዎች የሚመጥኑ፣ ችግር ፈቺዎችና መልካም አስተዳደር የሚያመጡ መሆን አለባቸው፡፡ ትናንትና ከከንቲባነታቸው የተነሱት አቶ ታከለ ኡማ ሲሾሙ ህግን ተከትለው የመጡ አልነበሩም፡፡ የምክር ቤት አባል ሳይሆኑ የተሾሙ ከመሆናቸውም በላይ በቆዩበት የሥልጣን ዘመናቸው የአዲስ አበባን ችግር ሲያወሳስቡ የነበሩ ግለሰብ ናቸው፡፡ በኮንዲምኒየም አሰጣጥ ላይ የፈፀሙት ወንጀል፣ መሬት ወረራ እንዲስፋፋ የፈፀሙት ወንጀል፣ ህገ-ወጥ ግንባታ እንዲስፋፋ የፈፀሙት ወንጀል፣ የድሆችን ቤት በማፍረስ በተለይም በኮረና ሰዓት የፈፀሙት ወንጀል የሚያስጠይቃቸው ነው፡፡ እኚህ ሰው ዛሬ ወደ ሌላ ሹመት ተዛውረው ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ሥልጣኑን ተረክበዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ሌላ ግፍና ከፍተኛ ንቀት ነው፡፡ እኚህ ሴት ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በነበሩበት ሰዓት ያሳዩት በተረኝነት የተቃኘ አሰራር ሕገ-ወጥ እና በከፍተኛ ሁኔታ ትዝብት ላይ የጣላቸው ከመሆኑም ባሻገር በእውቀታቸውም ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ ለውጡ የጉልቻ መለዋወጥ ነው፡፡ ባልደራስ ትግሉን ይቀጥላል፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብም ከባልደራስ ጎን በመሆን ለመሰረታዊ ለውጥ እንዲነሳ እንጠይቃለን፡፡–ይህ የኦህዴድ/ብልጽግና ጉዞ የትላንቱ የህወሀት ሌላኛው ገጽታ በመሆኑ ሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ሊረባረብበት እንደሚገባ በማመን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ሙሉ ለሙሉ መጨናገፉን ለኢትዮጵያ ህዝብ በመግለጽ ትላንት የህወሀት አንባገነናዊ ስርዓትን ለመገርሰስ ያዋልነውን የተባበረ ክንዳችንን በማስተባበር ለሰላማዊ እና ህጋዊ ትግሉ እራሳችንን እንድናዘጋጅ እየጠየቀ፤ በቅርቡ ሀብት ንብረታቸውን በተፈጥሮ አደጋ ላጡ የአፋር ክልል ነዋሪዎች ሀዘኑን በመግለጽ ለድጋፍ እንድንረባረብ፤ ሰኔ 22ን ተከትሎ የዘር ማጥፋት ድርጊት ህይወታቸውን ላጡ እና ሀብት ንብረት ለወደመባቸው፣ በወላይታ ዞን መብታቸውን ለማስከበር ሲጠይቁ በመከላከያ ሰራዊት ህይወታቸው ለተቀጠፈና አካላቸውን ለጎደለ ንጹኀን ዜጎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች የስርዓቱ ስግብግብነት የፈጠራቸው የዜጎች ህልፈተ-ህይወት፣መፈናቀል እንዲሁም የኦህዴድ/ብልጽግና ተረኝነት ሴራን በማጋለጣቸው በግፍ በእስር ለሚገኙ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች በአጠቃላይ በሀገራችን የተንሰራፋውን መጥፎ መንፈስ ለማጥፋት እና መጪውን የትግል ወቅት ሰላማዊ ለማድረግ ፈጣሪያችን ሁላችንን እንዲረዳን እንደየቤተ-እምነታችን በጸሎት እና በጾም ለፈጣሪያችን እጃችንን እንድናነሳ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያን ህዝብ በእጅጉ ይማፀናል፡፡–በመጨረሻም በአንባገነኑ ኦህዴድ/ብልጽግና በግፍ የታሰሩ የድርጅታችን ከፍተኛ አመራሮች /አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ሌሎች የድርጅታችን አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ባላሰለሰ ሁኔታ በድርጅታችን እና አባላቶቻችን ላይ የሚያደርገውን ወከባ እና እንግልት በአስቸኳይ እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡–ድል ለዲሞክራሲ!!ነሐሴ 14/2012 ዓ.ምአዲስ አበባ ኢትዮጵያTel. 09 05 00 25 25 E.mail:- balderasethiopia@gmail.com www.balderasfordemocracy.com