August 22, 2020 – Konjit Sitotaw
ባልደራስ የዛሬው የተወሰኑ ፓርቲዎች የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ አግላይ ነው ሲል ቅሬታ አቀረበ
–
ሁሉን አቀፍ ያልሆነ የብሄራዊ መግባባት መድረክ ብሄራዊ መግባባትን አያመጣም! – ባልደራስ
–

በአሁኑ ሰዓት በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ የተወሰኑ ፓርቲዎች ውይይት እያደረጉ እንደሆነ እያየን ነው። የሃገራችን ሰው በአንድ እጅ አይጨበጨብም ይላል። ብሄራዊ መግባባት የሚመጣው እኮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ለሂቃን ሲሳተፉበት ነው።
–
በጋራ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መምከር ስንችል፣ በንጹህ ልቦና ሃገርን አስቀድመን በሰከነ መንፈስና በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገራ ውይይት ሲደረግ ነው ብሄራዊ መግባባት የሚመጣው:: በጋራ የጋራ አጀንዳ ቀርጸን ሃቀኛና ግልጽ ውይይት ሲደረግ ነው ብሄራዊ መግባባት የሚመጣው።
–
በዶክተር አብይ የሚመራው መንግሰት ሁለት ነገሮችን አጥብቆ ሲርቅ እናያለን። አንደኛው ነገር መነሳት የሚገባቸውን ብሄራዊ አጀንዳዎች በብዙ ርቀት ሲርቅ ይታያል። ይፈራቸዋል። ወሳኝ የብሄራዊ መግባባት አጀንዳዎችን ረገጥ አድርጎ ለመወያያት አይደፍርም። ሁለተኛው የሚፈራው ነገር ደግሞ ኣካታች የሆነ ጉባኤ ማድረግን ነው።
–
ጠያቂ የሆኑና ሃቀኛ የሆኑ አጀንዳዎችን ማንሳት የሚፈልጉ ፓርቲዎችን ከዚህ ጉባኤ ያገላሉ። አግላይ የሆነና ለለውጥ ያልቆረጠ የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ ሃገራዊ መግባባትን አያመጣም ብቻ ሳይሆን የብሄራዊ መግባባት ሃሳብን የሚያረክስ ነው። ባልደራስ ሁል ጊዜም ለሃቀኛና ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ መግባባት ይሰራል። ሃገራችን ወደ ሃቀኛ ብሄራዊ መግባባት እንድታመራም ይጥራል።