“ተበደልኩ ባዩም በዳዩም የሚምለው በመከረኛው ሕገ መንግሥት ነው”ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ – ለሲራራ
–
ሲራራ፡- ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የተሻለ ይሆናል፤ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ፉክክር ይኖራል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ አሁን የሚታየው ሁኔታ ግን እምብዛም ከድሮው የተሻለ አልሆነም፡፡ በእርስዎ ግምገማ ፈቀቅ ያላልንበት ምክንያት ምንድን ነው?
–

ፕሮፌሰር በየነ፡- በግልጽ እንደሚታየው በሚያሳዝን መልኩ የፖለቲካው ምኅዳር ደፍርሷል፡፡ ቀድመን ስንመክር የነበረው አሁን የተፈጠረው ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጠር ነበር፡፡ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ ዓመታት ምን ያህል ስለ ጠንካራ እና አሳታፊ ሥርዓት ግንባታ ስንጮህ እንደኖርን ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች እንዲለወጡና እንዲሻሻሉ፣ አርቆ አሳቢና አስተዋይ በመሆን መራመድ እንደሚገባ፣ የዚህች አገር ችግር ብዙ በመሆኑ የሁሉም ዜጎችና የፖለቲካ ኀይሎች ተሳትፎ አስፈላጊ እንደሆነ፣ ለዚያ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና እየዳበረ የሚሄድ መሆን እንዳለበት ስናሳስብ ነው የኖርነው፡፡ ብዙ ጩኸናል፡፡ የሚሰማ አልተገኘም፡፡ ባለመስማታቸውም ዛሬ እነሱም አገሪቱም እዚህ ደርሳለች፡፡
–
ትናንትና በአንድ ድርጅትና መንግሥት ውስጥ ሆነው የፖለቲካ ምኅዳሩን አንቀው አላላውስ ያሉን ሰዎች ዛሬ እርስ በርሳቸውም የሚስማሙ አልሆኑም፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ መካረር ውስጥ ገብተዋል፡፡ አሁን የሚታየው የፖለቲካ መካረር ትልቅ አገራዊ እና ሕዝባዊ ኀላፊነት ያላቸው አካላት መካከል መሆኑ ደግሞ ነገሩን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ አሁን በሚታየው የፖለቲካ ጡዘት ውስጥ ሥልጣን ያልያዙት ብቻ ሳይሆኑ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላትም ጭምር ተሳታፊ ሆነው ነው የምናያቸው፡፡ ሁኔታውን አደገኛ የሚያደርገውም እሱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊት አገርንም ሕዝብንም ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ ይችል ይሆናል እንጂ ማንንም የሚጠቅም አይደለም፡፡
–
አገርን በእልህ እና በቂም በቀል መምራት አይቻልም፡፡ ስሜታዊነት፣ አለማስተዋልና አርቆ አለማየት ሰፍኗል፡፡ ይህ ግን ጨርሶ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በዚህ ሰዓት በሁሉም ወገን መስከን እና ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል፤ ለጊዜው መፍታት ያልተቻሉትን ደግሞ በይደር ማቆየት መለመድ አለበት እያልን ምክራችንን ስንሰጥ ነው የቆየነው፡፡ አሁን ያለንበት የፖለቲካ ውጥረት አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ እንኳን አዳዲስ ችግር ተደራርቦባት ድሮውንም ቢሆን ብዙ ውዝፍ ችግርና ዕዳ ያለባት አገር ናት፡፡
–
በነገሠው የስሜትና የእልህ ፖለቲካ ምክንያት መከሰት ያልነበረባቸው ቀድመን ልናስወግዳቸው የሚገቡ ችግሮች እየተከሰቱብን ብዙ የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት መጥፋት እያስተናገድን ነው ያለነው፡፡ አሁንም በተለያዩ አካላት መካከል እልህ መጋባቶች በስፋት ይታያሉ፡፡ በመንግሥትና መንግሥትን በሚቃወሙ ሥልጣን ያልያዙ አካላት ብቻ ሳይሆን በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥታት መሀከል ያለው ግንኙነት እጅግ የተበላሸና ዜጎችን ፍርሃት ውስጥ የከተተ ነገር ነው፡፡ ሁሉም በሕገ መንግሥቱ ይምላል፣ ይገዘታል፡፡ ተበደልኩ ባዩም በዳዩም የሚምሉት በዚህ መከረኛ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥትን የተለያዩ አካላት እንደፈለጉ እየተረጎሙት ነው ያሉት፡፡ በዚህ ሁሉ ቀውስ የሚጎዳው የሕዝብ እና የአገር ጥቅም ነው፡፡
–
ሲራራ፡- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አገሪቱ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ልትገባ ነው በሚል እምነት በለውጡ ላይ ትልቅ ተስፋ ጥለው ነበር፡፡ ለውጡ በሚፈለገው ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን አስፍኖ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚያዋልድ መልኩ እንዳይሄድ ያደረገው ምንድን ነው ይላሉ?
–
ፕሮፌሰር በየነ፡- ይህ ለውጥ እንዲሁ በአንድ ጊዜ የመጣ ወይም በተወሰኑ ሰዎች ትግል የተገኘ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ብዙ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችም ጭምር ይህን ሐቅ ሲስቱት እናያለን፡፡ ለውጡ ለረዥም ዓመታት የተደረጉት ትግሎች ድምር ውጤት ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ በርካቶች ሕይወታቸውን ገብረዋል፣ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አሉ፣ የተሰደዱም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ለውጡ የሕዝቡ የረዥም ጊዜ የትግል ውጤት መሆኑ በደንብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ በውጭም በአገር ውስጥም ያላቋረጠ ትግል አድርጓል፡፡ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ የሕዝቡ ትግልና መስዋዕትነት ወደጎን ተገፍቶ አንዳንድ አካላት የለውጡ ፊታውራሪ ነን በሚል የትግል ውጤት ሽሚያ ውስጥ ሲገቡ ታዝበናል፡፡ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ የሚለው ሽኩቻም አሁን ለምንገኝበት ምስቅልቅል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ግልጽ ነው፡፡
–
እንግዲህ እንደተባለው በዚህ ለውጥ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ አሁንም ያ ተስፋ ተሟጥጧል ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም ሕዝቡ ከመንግሥትና ከሌሎች የፖለቲካ ኀይሎች ብዙ ይጠብቃል፡፡ ሆኖም እንዳልኩት የመንግሥት ሥልጣን በያዙትም ከዚያ ውጪ ባሉት አንዳንድ የፖለቲካ ኀይሎችም አካባቢ እጅግ አስቀያሚ የሆነ ሽኩቻ፣ ቂም በቀል፣ ስሜታዊነትና አርቆ አለማየት ለውጡን እየፈተነው ነው፡፡ መፍትሔው ከፍ ብየ እንደገለጽኩት መስከን ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ሲባል ቆም ብሎ ወደራስ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሀከል የሚደረጉት ውይይቶችም መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በተመሠረተ ሐቀኛ ውይይትና ድርድር ነው የዚህችን አገር ችግር መፍታት የሚቻለው፡፡
ሲራራ፡- ባለፉት ጥቂት ወራት በፓርቲዎች መሀከል ያለውን የፖለቲካ መካረር ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቢቆዩም ጥረቱ በታሰበው ልክ ውጤት አላመጣም፡፡ በዚህ ሁኔታ የአገር ሽማግሌዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጥረት የፖለቲካ አለመግባባቱን ሊፈታው ይችላል? ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭስ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡-
የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሲቪክ ማኅበራት ጥረት አላደረጉም ማለት አይቻልም፡፡ የተለያየ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ጥረታቸውን የሚሰማ አካል ባለማግኘታቸው ውጤት ማምጣት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም አሁን የሚታየውን ጥፋት የሚያደርሰው አካል የሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ሐሳብና አስተያየት ለመስማት ፍቃደኛ እየሆነ አይደለም፡፡ ችግሩ የሚፈታው መደማመጥ ሲኖር፣ ባህላዊ ተቋማትን ለማክበር የተዘጋጀ ሥነ ልቡና ሲኖር ነው፡፡ ሽምግልናን እንደ የዋህነት የሚያይ ደረቅ ፖለቲከኛ ነው ያለው፡፡ ለነገሩ በዚህች አገር እጅግ የተከበረና ዕንቁ የነበረው ይህ ባህል በኢሕአዴግ ዘመን መልኩ እንዲጠፋ ብዙ ተሠርቷል፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የነበራቸው ሞገስ እንዲገፈፍ ያደረገው ሥርዓቱ ነው፡፡በዚህ ጊዜ የአቅም መለኪያ ጥይት ማስጮህ እየሆነ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የማይችሉ ቡድኖች የሞራል አቅም ነው ያላቸው፡፡ ይህን የሞራል አቅም ከማያከብር ፖለቲከኛ ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ሰላም መፍጠር የሚቻለው? ለዚህ እኮ ቀድሞ የነበረው ግብረገብነት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የምናየው እንስሳት እንኳን የማያደርጉትን ተግባር ነው፡፡ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰው ከእንስሳት በታች ሲሆን ነው እየተመለከትን ያለነው፡፡ እነዚህን አካላት ቁጭ ብሎ ከመመልከት ውጪ እነዚህ ገለልተኛ አካላት ምን ሊያደርጓቸው ይችላሉ? እነዚህ ቡድኖች ያገኙትን ለማቃጠል ክብሪት እና ጭድ ይዘው ነው የሚዞሩት፡፡ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም እኮ ሲደበደቡና ጥቃት ሲደርስባቸው ታዝበናል፡፡አሁን ያለው የቡድን ጽንፈኝነት ለገላጋይም የሚመች አልሆነም፡፡ በዚህ ሁኔታ እርቀ ሰላም ቢባል የአገር ሽማግሌ ቢባል መጀመሪያ የሚሰማ አካል ሲገኝ ነው ውጤቱን መለካት የምንችለው፡፡ አሁን እንደምናየው የሰው ንብረት ሲወድም እና ሕይወት ሲጠፋ መንግሥት ሳንጃውን እና የፍትሕ ሚዛኑን ይዞ ነው መውጣት ያለበት፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት ከአገር ሽማግሌዎች አቅም በላይ የሆነ ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ወይም ለዚያ ሳይወግን ገለልተኛ ሆኖ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ይገባዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ የዜጎችን መብት ማስከበር ይገባዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኀላፊነቱ እየተወጣ አይደለም፡
፡ሲራራ፡- በፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኝነት ላይ የሚነሳው ጥያቄም አሁንም ከለውጥ በኋላ እንደቀጠለ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ፍትሕን ማረጋገጥ እና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መተማመንን መፍጠር የሚቻለው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- የፍትሕ ሥርዓቱ የአገሪቱን እና የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ሥራው ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ከደሃው ማኅበረሰብ በሚሰበሰበው ግብር ዩኒፎርም ለለበሰው ወታደር እና ካባ ለሚለብሰው ዳኛ ደሞዝ የሚከፈለው፡፡ እኔ በግሌ የፍትሕ ሥርዓቱ ባለሟሎች ሕዝብ ሲጠቃና ሲጎዳ ቆመው አይተዋል ነው የምለው፡፡ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የነበሩ ሰዎችን ስናነጋግር የሚሰጡን መልስም እሱ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም ሁኔታዎቹ ከአቅም በላይ ሆነው አይቻለሁ፡፡ ከሻሸመኔ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ኀይል ተቀምጦ ነው ያ ሁሉ ጉዳት የደረሰው፡፡ነገር ግን አሁንም ቢሆን በልዩ ኀይሉ መፍረድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ልዩ ኀይሉ ካልታዘዘ እርምጃ መውሰድ አይችልም፡፡ ትዕዛዝ ከየት ነው የሚመጣው? ከተባለ ከላይ ካሉ ባለሥልጣናት ነው፡፡ ጉዳት ሲደርስ ትዕዛዝ ቶሎ ባለመምጣቱ ነው ልዩ ኀይሉ በቅርብ ርቀት ባለበት ሁኔታ ያ ሁሉ ጉዳት የደረሰው፡፡ ይህ የሚያሳየው በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያልተቀናጀ ተግባር መኖሩን ነው፡፡ ምን ዓይነት ጥቃት ለመሰንዘር እንደታሰበ ቀድሞ የማያውቅ የደኅንነት ተቋም ጥቅሙ ምንድን ነው? መኖሩስ ምን ዋጋ አለው? የመንግሥት ባለሥልጣኑ፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ፣ ልዩ ኀይሉ ሲቀናጅ ነው የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር የሚቻለው፡፡ ባለፉት ሳምንታት ያየነው በተቋማት መሀከል ያለው ቅንጅት ምን እንደሚመስል ነው፡፡ በእርግጥ በብዙ ቦታዎች፣ በተለይም የታችኛዎቹ የመንግሥት መዋቅሮች የሚጠበቅባቸውን ተግባራት መወጣት ካቆሙ ቆይተዋል፤ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎችማ መንግሥታዊ መዋቅሩ ፈርሷልም ማለት ይቻላል፡፡ – ሲራራ