August 23, 2020

አዲስ ዘመን – ሕገ መንግሥቱ በውስጡ ብዙ ጠቃሚ ድንጋጌዎችን የያዘ ቢሆንም አፈጻጸሙ የተለካውና የተሰፋው ግን በህወሓት ጥብቆ ልክ እንደነበር የኦህዴድ ነባር ታጋይ አቶ ኤልያስ ጉዮ አስታወቁ። ለውጡ የሞግዚት የውክልና የአሃዳዊነት አስተዳደር ሂደቱ እንዲነሳ ማድረጉን አመለከቱ፡፡

አቶ ኤልያስ ጉዮ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሕገ መንግሥቱ ጥሩ የሚባሉ ነገሮችን ይዞ የመጣ ቢሆንም አፈጻጸሙ የተለካው እና የተሰፋው በህወሓት ጥብቆ ልክ እንደነበር አስታውቀዋል። በክልሎች ጉዳይ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ ያለፉት 27 ዓመታት የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭና አዛዥነት የነገሰበት እንደነበር አመለከቱ፡፡

Image may contain: 1 person, suit

በ1980ዎቹ ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ኤልያስ፣ በወቅቱ እሳቸውም ሆኑ እሳቸው የወከሉት የፖለቲካ ድርጅት (ኦህዴድ) የሚወስናቸውን ውሳኔዎች በቅርበት የሚመለከቱ የህወሓት ሰዎች ይመደብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የፓርቲው አመራሮች ሕዝቡ የሚፈልገውን መወሰን እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ገኖ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩት አራት ፓርቲዎች (ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴን ) እንደነበሩ አስታሰው፣ ከላይ ግን መመሪያ የሚሰጠውና ሰው መድቦ የሚያዘው ህወሓት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ለምሳሌ ለኦሮሚያ ተመድበው ከነበሩት መካከል አብርሃም ማንጁስ እና ሰለሞን ጢሞ የሚጠቀሱ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ይህ እውነታ የፌዴራል ሥርዓቱ እንደ ሌሎቹ የሕገ መንግሥት ላይ ጽሑፎች በአግባቡ ያልተፈጸሙ፤ የሕዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ያላረጋገጠ፤ ይልቁንም የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭና አዛዥነት የነገሰበት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ይህንን የህወሓት ፈላጭ ቆራጭነት ገና ከጠዋቱ ጀምሮ የሚታገል ኃይል እንደነበር ጠቁመው፣ አንድ ቀንም ትግሉ ተቋርጦ እንደማያውቅ አመልክተዋል። በዚህ የተነሳም ብዙ አመራሮች በየወቅቱ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ጠቁመዋል። በተለይ ሲቪል የነበሩና አይሆንም ሲሉ የነበሩ የክልሉ ኃላፊዎችን ከኃላፊነት በማንሳት፣ ከድርጅት በማባረርና ከሥራ በማፈናቀል ብሎም ከአገር በማስወጣት መወገዳቸውን አመልክተዋል።

«ከመከላከያ ከማል ገልቹ ለምንድን ነው ከሀገር የወጡት ብለን ከጠየቅን፤ በአግባቡ መስራትና መንቀሳቀስ ስላላስቻሏቸው ነው፡፡ እነ ጄኔራል ባጫ እና እነ ጄኔራል ጌታቸው እንዲሁም እነ ጄኔራል አበባው ታደሰ ጡረታ እንዲወጡ የተደረገውም ስላረጁ ወይም ዕድሜያቸው መስራት ስላላስቻላቸው አይደለም» ብለዋል፡፡

በዚህ መልኩ በደረሰ መገፋት ትግሉ መታየት ሳይችል ቀረ እንጂ በወቅቱም ዝምታ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በተደረገ ብርቱ ትግል በአርሶአደሩ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ በርካታ ችግሮችን መከላከል መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ህወሓት ይህን ተግባር የፈጸመችው በኦህዴድ ወይም በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች እንደነበር ጠቁመው፣ «በትግራይ ታጋዮች ላይም በተመሳሳይ መልኩ ይፈፀም እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ይሄን ነገር አይሆንም የሚሉት ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን፤ በእኛ ላይ እንደዛ ሲደረግ መሆን የለበትም የሚሉ የህወሓት ታጋዮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዚያን ወቅት የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ገብሩ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

«አንድ ቀላል ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ ፊንፊኔ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ላይ እንጂ ወደጎን አታድግም፤ ተጠንቶ በአካባቢው ያለውን የኦሮሞ አርሶአደር የእርሱ መብት እስካልተጠበቀ ድረስ ምንም ዓይነት አርሶአደሩን የሚያፈናቅል ሥራ አንሰራም የሚል ውሳኔ እንደ ምክር ቤት ወስነን ነበር፡፡ ይህችን ውሳኔ የወሰንን ዕለት እነዚህ ያልኩህ እንደ ሞግዚት እኛን ከሚከታተሉና ከሚያስተዳድሩት ሰዎች አንዱ «ባጋጣሚ ነው እዚህ ያላችሁት፤ ከዚህ ስትባረሩ ሥራ ላይ እናውለዋለን» ሲል ለሁሉም እንደነገራቸው አመልክተዋል፡፡

ሌላ ጊዜ እንደ ሕዝብ ብዛታችን ቦታ ይኑረን ከሚል መነሻ፤ ኦሮሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን፣ አማራው ደግሞ ፕሬዚዳንት ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለምን አይደረግም፤ ለምንስ እንደ ሕዝብ ብዛታችን የሥልጣን እርከኖች አይደለደሉም የሚል ጥያቄ አነሳን፡፡ ይሄ ሃሳብና ጥያቄ ሲቀርብ በዚያን ጊዜ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር «አሁን እናንተ ናችሁ እንዲህ የምታነሱት እንጂ የትኛው የኦሮሞ አርሶ አደር ነው ፕሬዚዳንት ሥልጣን የለውም የሚለው? እንደውም ንጉስ ተሾመልን ነው የሚሉት፤ ተዉት ባካችሁ!» ነበር ያሉን፡፡

ዶክተር ነጋሶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን «ንግግርዎት የመንግስቱ ኃይለማርያምን ንግግር መሰለ» እያለ ሲሞግት፤ ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በላይ በወቅቱ ኦህዴድ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው የጎዱት፡፡ እነ ገነት ዘውዴ መለስን እንዴት እንዲህ ይናገረዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዴት መንግስቱ ኃይለማርያምን መሰልክ ትለዋለህ ብለው ሲያለቅሱ፣ ኦህዴድ ውስጥ የነበሩትም ናቸው መለስን እንዴት እንዲህ ትለዋለህ ሲሉ የነበሩት፡፡

«በዚያ የተነሳ ዶክተር ነጋሶን ማግኘት የሚገባውን ጥቅማጥቅም ነጥቀውት፤ መኪና ነጥቀውት፤ ለቤት የሚከፈለውን ኪራይ ከመከልከል አልፈውም ቤት እንኳን እንዳይታደስለት ተደርጎ ጣሪያው እስኪያፈስ ድረስ ነው እንዲሰቃይ የተደረገው፡፡ ይሄን ሲያደርጉ የነበሩ የህወሓት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ የኦሮሞ ልጆችም ናቸው» ብለዋል፡፡

ለውጥ ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም ለክልሎች ይዞ የመጣው ትልልቅ ነገሮች እንዳሉ አመልክተው፣ አንደኛ ሞግዚትነት ተነሳ፡፡ የሞግዚት አስተዳደሩ ወይም በውክልና የአሃዳዊነት አስተዳደር ሂደቱ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ፌዴራሊዝም አለ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ፓርቲ የበላይነትና ቁጥጥር ስር የነበረ የአሃዳዊነት አስተዳደር ነበር ሰፍኖ የቆየው፡፡ እናም በለውጡ ያ አሃዳዊነት ተነሳልን፡፡ ይሄ ለኦሮሚያ ክልልም፤ ለሌሎች ክልሎችም መሆኑን አስታውቀዋል፡

፡–

ሁለተኛ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እኩል ተሳታፊነትን አረጋግጧል፡፡ እንዲያውም እኛ በአሃዳዊነትም ቢሆን የምንተዳደር አራቱ ድርጅቶች ወይም ክልሎች እንሻል ነበረ እንጂ፤ መልዕክት ብቻ የሚደርሳቸው ክልሎች ነበሩ፡፡ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መልዕክት ብቻ ነበረ የሚደርሳቸው፡፡

ምንም ነገር የማያውቁትንና በአራቱ ድርጅቶች የተወሰነውን ደብዳቤ ነው የሚላክላቸውና ይሄንን አድርጉ የሚባሉት ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ያ አይደለም የሚሆነው፡፡ እነሱም መንግሥት ውስጥ ገብተው እየሰሩ፤ በፓርቲ ውስጥም ድርሻ ኖሯቸው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ገብተው ተሳታፊ ሆነውና ሀሳብም ሰጥተው ብሎም ተከራክረውበት ያመኑበትን ነገር በክልላቸው ሄደው ይተገብራሉ፡፡ ይሄም አንድ ትልቅ ነገር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ለውጥ ብዙ ሰዎች ነፃ እንዲወጡ የተደረገበት ሂደት ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች እኮ የኦሮሚያ ክልል ነበር የሚባሉት፡፡ በለውጡ እኮ ይሄንን በር ከፍቷል፤ ብዙ ባላምንበትም፡፡ ይሄን የምለው ግን ለምን ተለቀቁ ብዬ አይደለም፤ ታይቶ እየተለየ በፋታ ቢለቀቁ ጥሩ ነው ለማለት እንጂ፡፡ በአገር ውስጥ ማረሚያ ቤቶች የተዘጋባቸው ብቻ ሳይሆን፤ የአገር ውስጥ መግቢያ በር የተዘጋባቸውም ናቸው በሩ ተከፍቶላቸው በኤርፖርት እንዲገቡ የተደረገው፡፡ በሕይወትህ ኢትዮጵያን አትረግጣትም የተባለ ሰው ሳይቀር ነው ያለምንም ችግር በኤርፖርት በክብር የገባው ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን