24 ነሐሴ 2020, 07:03 EAT

በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ቀን ተቆርጦለታል። ክልላዊ ምርጫው ጳጉሜ 4 እንደሚካሄድ የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። መራጮችም ከአርብ ጀምሮ የድምጽ መስጫ ካርድ መውሰድ ጀምረዋል።
በቅርቡም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫው መካሄድ እንደሌለበትና ምርጫውን ለማስቆም የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነትን እንደሚጠይቅ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባርን በሚደነግግበት አንቀጽ 62.9 ላይ “ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ-መንግሥት በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል” ይላል።
- መንግሥትንና ህወሓትን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት እንዲያሸማግሉ ክራይስስ ግሩፕ ሐሳብ አቀረበ
- በትግራይ በምርጫ ሥርዓትና በምክር ቤት መቀመጫ ብዛቱ ላይ ለውጥ ተደረገ
ለመሆኑ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ ተፈጻሚ የሚሆነው እንዴት ነው? በትግራይ ክልላዊ ምርጫ በመካሄዱ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል?
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የቀድሞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና ምክትል ፕሬዝደንት አቶ በሪሁ ተወልደብርሃን፣ በኔዘርላንድስ የአስተዳደርና ዲሞክራሲ አማካሪ አደም ካሴ (ዶ/ር) እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና የሰብዓዊ መብቶች መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ምን ማለት ነው?
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62.9 መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት በአንድ ክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ የሚያዘው ክልሉ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ጥሏል ብሎ ሲያምን ነው።
አቶ በሪሁ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ የሚባለው፤ “ከመደበኛው ሥርዓት ኢ-መደበኛው ሥርዓት ገዢ በሚሆንበት ጊዜ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ነው” ቢባል በርካቶችን ሊያስማማ እንደሚችል ይናገራሉ።
ሲሳይ መንግሥቴም (ዶ/ር) በመደበኛው የሕግ አስከባሪ አካል ሕግና ሥርዓትን ማስከበርና መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሲወድቅ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ሊያስብል ይችላል ብለዋል።
አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሕገ-መንግሥቱ መሰሶ የሚባሉ ነጥቦችን የሚያዛባ ሁኔታ ከተፈጠረ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ተከሰተ ሊባል እንደሚችል ያስረዳሉ። አክለውም “ሁሉም የሕገ-መንግሥት ጥሰቶች ግን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላሉ ማለት ግን አይደለም” ይላሉ።
አቶ በሪሁ ‘ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተጣሰ’ እና ‘ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ’ በሚሉት አገላለጾች መካከል ልዩነት መኖሩን ይጠቁማሉ።
“ሕገ-መንግሥታዊ ጥሰት ማለት ማናቸውም የጸረ-ሕገ መንግሥት ሂደቶችና ተግባራት ሲሆኑ፤ ሕገ-መንግሥቱ አደጋ ላይ ወድቋል የሚባለው ግን ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማት በራሳቸው ውድቀት ሲያጋጥማቸው ነው” ይላሉ።

እንደምሳሌም ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚው እና የዳኝነት አካላት በአንዳች ምክንያት ከተልዕኮ ውጪ ከሆኑ ሕገ-ምንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ያስብላል ሲሉ አቶ በሪሁ ያስረዳሉ።
የትግራይ ክልል፤ ምርጫ በማድረጉ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል?
አቶ በሪሁ ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸው “አይጥልም” የሚል ነው።
በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመንግሥት ሰልጣን የሚመነጨው በምርጫ ከመሆኑ አንጻር፤ “ምርጫ አደርጋለሁ ማለት ሕገ-መንግሥቱን ማክበር ነው። ስለዚህ ምርጫ ማካሄድ ለሕገ-መንግሥቱ አደጋ ሳይሆን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲከበርና ስር እንዲሰድ የሚያደርግ ተግባር ነው” ይላሉ አቶ በሪሁ።
“በእኔ እምነት ምርጫ ማካሄድ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር ከመሆኑ በስተቀር፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አይደለም።”
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉ የሚያደርገው ክልላዊ ምርጫ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል ማለቱ ስህተት ነው ሲሉም ይሞግታሉ።
“በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13 ላይ በማንኛው ደረጃ የሚገኙ የፌደራል እና የክልል የሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች ድንጋጌዎችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ግዴታ አለባቸው ይላል። የትግራይ ክልልም እያደረገ ያለው ይሄን ነው። ስለዚህ ለትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድ ግዴታው እንጂ ውዴታ አይደለም” ይላሉ አቶ በሪሁ።
‘ክልላዊ ምርጫው መካሄዱ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል’
ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በአቶ በሪሁ ሃሳብ አይስማሙም። ዶ/ር ሲሳይ የትግራይ ክልል የሚያካሂደው ምርጫ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ።
የክልሎች ሥልጣን የሚመነጫው ከሕገ-መንግሥቱ እንደሆነ የሚያስረዱት ሲሳይ (ዶ/ር)፤ አንቀጽ 50.8 የፌደራል መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በሕገ-መንግሥቱ መወሰኑንና ሕገ-መንግሥቱ የፌደራል መንግሥትና ክልሎች አንዳቸው የአንዳቸውን ሥልጣን ያከብራሉ ማለቱን ያስታውሳሉ።
ከዚያም ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102ን ጨምሮ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሕጎችን የማውጣትና የማስተዳደር እንዲሁም የምርጫ ቦርድ አባላት ሹመትን በተመለከተ ስልጣን የሰጠው ለፌደራል መንግሥቱ ነው ይላሉ።
የክልል ሥልጣንና ተግባር የተደነገገበትን አንቀጽ 52 ስንመለከትም ምርጫ ለማካሄድ ወይም የምርጫ አካል ለማቋቋም ለክልሎች የተሰጠ ስልጣን አለመኖሩን እንረዳለን ይላሉ ሲሳይ (ዶ/ር)።
“ስለዚህ የፌደራሉን መንግሥት ስልጣን የሚጋፋ የትኛውም እንቅስቃሴ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ይከታል” የሚሉት ሲሳይ (ዶ/ር)፤ “ክልሎች የፌደራሉን መንግሥት ስልጣን ከተጋፉ በክልሎች መካከል የሚኖረውን ግነኙነት አደጋ ውስጥ ይከታል። ከዚያም አልፎ የሕዝቦችን አንድነት የሚያላላና የግዛት አንድነትን ጥያቄ ውስጥ ይከታል። ስለዚህ የትግራይ ክልል ከምርጫ ጋር ተያይዞ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕገ-ወጥና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲሉ ሲሳይ (ዶ/ር) ይሞግታሉ።
አደም ካሴ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ከሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ሃሳብ ጋር ይስማማሉ።
አደም (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት በምርጫ የተወሰነ ነው ይላሉ። ከሕገ-መንግሥቱ ዋና ምሶሶዎች መካከል አንዱ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ነጥቦች እንደመሆናቸው መጠን የፌደራል መንግሥቱን የምርጫ ሥርዓትን ወደጎን የሚተው ከሆነ ፌደራላዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ሊጥል ይቻላል ይላሉ።
አደም (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቁ ምስል ምርጫ የማካሄድና ያለማካሄድ ጉዳይ ሳይሆን፤ “ክልሎችና የፌደራል መንግሥት አንዳቸው የአንዳቸውን ሥልጣን አክብረዋል ወይ የሚለው ነው።”
“ከሞራላዊ እሳቤ አንጻር የትግራይ ክልል እኮ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ በማለት ነው ምርጫ እካሂዳለሁ የሚሉት። ይሁን እንጂ መመልከት ያለብን ይህ እርምጃ በፌደራልና በክልል መካከል ያለውን የስልጣን ክፍፍል ይጥሳል ወይስ አይጥስም? የሚለው ነው። ስልጣኑ የፌደራል መንግሥት ነው እየተባለ ክልሉ ይህን ስልጣን መጠቀሙ ነው አደጋው” ይላሉ።
ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ የሚወስነው ማነው?
ሲሳይ (ዶ/ር) ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ የሚወስነው “የሕገ-መንግሥቱ የበላይ ጠባቂ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው” ይላሉ።
በተመሳሳይ አደም (ዶ/ር) በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ የሚወስነውም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚያዛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ይናገራሉ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔር ብሔረሰቦች ጭምቅ ስብስብ በመሆኑ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ያንጸባርቃል በመባሉ ይህ ኃላፊነት እንደተሰጠው አደም ካሴ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንድ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጥሷል ብሎ ወስኖ፤ እራሱ መልሶ የፌደራል መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ መወሰኑ ፍትሃዊ ያደርገዋል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አሁን ያለው የሕገ-መንግሥት ሥርዓት እንደ አገር ያዋጣናል አያዋጣንም የሚለው ሌላ ክርክር የሚያስነሳ ነው። አሁን ያለውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንቀበላለን እስከተባለ ድረስ ግን ይህን ብቻ ነጥሎ አንቀበልም ማለት አይቻልም” ይላሉ።
“እውነት ነው የሚተረጉመውም የሚያዘውም አንድ አካል ነው። አቤት ማለት አይቻልም። ይህ መሠረታዊ የሆነ የአወቃቀር ችግር ነው። ይህን መለወጥ ሊኖርብን ይችላል። እስካልተለወጠና በሥርዓቱ እስካመንን ድረስ ግን ለሕገ-ምንግሥቱ ከመገዛት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም” ይላሉ አደም (ዶ/ር)።
ጣልቃ ይገባል ማለት ምን ማለት ?
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በተደነገገበት የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62.9 ላይ ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ-መንግሥት በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል ይላል። ለመሆኑ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ይገባል ሲባል ምን ማለት ነው?
ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) የፌደራል መንግሥት በክልል ጉዳይ ጣልቃ የሚገባው “እንደየ ችግሩ መጠን እና ስፋት ይለያያል” ይላሉ።
የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ ሊገባ የሚችልበትን መንገድ ሲያስረዱም፤ “ሕገ-መንግሥዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ሊያስቆም በሚችል መልኩ ከድርድር እስከ የኃይል እርምጃ ሊደርስ ይችላል” ይላሉ።
እንደምሳሌም የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት አብዲ ሞሐመድ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌሎች ወንጀሎች በተጠርጠሩበት ጊዜ የፌደራሉ መንግሥቱ ከጅግጅጋ በቁጥጥር ሥር ያዋለበትን ሁኔታ ያነሳሉ።
አደም ካሴ (ዶ/ር) በፌደሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ መሠረት የፌደራል መንግሥት በክልል ጉዳይ በተለያየ መልኩ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ይጠቁማሉ። የፌደራሉ መንግሥት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጠውን ትዕዛዝ የመፈጸም ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለበትም ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ ይላሉ አደም (ዶ/ር)፤ “ይሁን እንጂ አንድ ማስታወስ ያለብን ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን አለው ማለት የግድ ስልጣኑን መጠቀም አለበት ማለት አይደለም።”
አደም (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት የዳበረ ቢሆን ኖሮ መሰል በክልልና በፌደራል መንግሥት መካከል የስልጣን ግጭት በተደጋጋሚ ባጋጠመ ነበር። ነገር ግን ይህ አለመግባባት ወደ ኃይል የሚያመራ አይሆንም ነበር ይላል።
ለቀድሞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና ምክትል ፕሬዝደንት አቶ በሪሁ ተወልደብርሃን ግን “የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫው ጉዳይ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ አዛለሁ ማለቱ ትክክል አይደለም፤ ስልጣኑም የለውም” ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም አቶ በሪሁ አዋጅ ቁጥር 359/1995 የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሕጋዊ ሥርዓት ተክሏል ይላሉ።
ሕገ-መንግሥቱም ቢሆን የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ የሚችለው በሁለት ምክንያቶች እንሆነ አስቀምጧል ይላሉ። እነሱም፡
አንቀጽ 51.14 ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ የፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊትን ያሰማራል ይላል።
55.16 ደግሞ በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማስቆም ሳይችል ሲቀር፤ በራሱ አነሳሽነትን ያለ ክልሉ ፍቃድ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ለፌዴሬረሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፤ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመሪያ ይሰጣል ይላል።
ከዚህ ቀደም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አጋጥሞ ነበር?
ሲሳይ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም አንድ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ጣለ የተባለበትን አጋጣሚ እንደማያስታውሱ ተናግረው፤ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድን ወደ ስልጣን የመጣው የሕዝብ ተቃውሞ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ጥሏል ተብሎ በአገሪቱ በተደጋጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንደነበረ አስታውሰዋል።