August 24, 2020

“በገሃነም ውስጥ በጣም የሚያቃጥለው ቦታ የተያዘላቸው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሞራል ውድቀት
በሚታይበት ወቅት ድምጻቸውን የማያሰሙና በግልጽ የሚታይ ወንጀልን ለማይኮንኑ ሰዎች ብቻ ነው!“ Dante
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ነሐሴ 24፣ 2020
መግቢያ
ከሃጫሉ መገደል ጋር በተያያዘ በአገራችን ምድር የተከሰተው እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሁኔታ አብዛኛዎቻችንን አሳዝኖናል፤ አስቆጥቶናልም። የብዙ መቶ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደልና መታረድ፣ እንደሻሸመኔና ዝዋይ የመሳሰሉ የበለጸጉ ከተማዎች መውደምና፣ የብዙ ሰዎችም ንብረት መፈራረስና፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የቤተክርስቲያናት መውደምና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልክ መገደል አገራችን ወዴት እያመራች ነው? የህዝባችንስ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆናል? እያልን ብዙዎቻችን እየጠየቅን ነው። ማዕከላዊ መንግስትና የክልል አስተዳዳሪዎች ባሉበት አገር ይህ ሁሉ ሰው እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሲገደልና፣ ለብዙ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል የሰጡና የሚሰጡ የብዙ ባለሀብታሞች ሱቆችና ሆቴልቤቶች፣ እንዲሁም ደግሞ ፋብሪካዎችና መኖሪያ ቤቶች ሲወድሙ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ ሰዎች የት እንደነበሩና ተግባራቸውም ምን እንደሆነ ለማወቅ የተቸገርን ጥቂቶች አይደለንም።
በብዙ አገሮች ተቀባይነት ያጡ አገዛዞች ወርደው በአዳዲስ አገዛዞች ቢተኩም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ትርምስ የታየባትና አቅጣጫውም የጠፋበት እንደኛ አገር ያለ አይመስለኝም። የዛሬው ዐይነት እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ እንዲፈጠርና አገራችንም ድምጥማጧ እንዲጠፋ በእነ አቶ መለሰና የኋላ ኋላ ደግሞ በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው የህወሃት አገዛዝ የጥፋት የቤት ስራ እንደሰራ የማይታበል ሀቅ ነው። የህወሃት የመጨረሻው ዓላማና ውስጣዊ ፍላጎት ግልጽ ነበር። በድርጅቱ የበላይነት ስር የምትገዛና የምትበዘበዝ፣ ይህ የማያዋጣ ከሆነ ደግሞ ከረጅም ጊዜ አንፃር ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ፋሺሽታዊ አገዛዝ መመስረትና ከዚያ ሆኖ በተለያዩ ዘዴዎች አገርን ማተረማመስ ነበር። ህወሃት በመጠኑም ቢሆን ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ከገባ በኋላ ጥሎ የሄደው አስከፊ ሁኔታ በዚህ መልክ ሊከሰት ይችላል ብሎ ያሰበ ሰው ያለ አይመስለኝም። በተለይም ደግሞ በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ በአገሪቱ ውስጥ ሰላምን የማስፈንና ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመምራት ችሎታ ይኖረዋል ብለን የገመትን ጥቂቶች አልነበርንም። ይሁንና ሁለት ዐመት ባልሞላ ጊዜና ከዚያም በኋላ „በሳቂተኛውና በሊበራሉ“ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ዘመን ከሰላም ይልቅ ከፍተኛ አለመረጋጋት፣ ካለመገደልና ካለመሳዳድ ይልቅ መገደልና ስንትና ስንት ዘመናት የፈራ ሀብት የሚወድምበት ጊዜ በማየታችን ለአንዳንዶቻችን ይህ ዐይነቱ በህዝባችን ላይ የሚወርደው ግፍ እንደ ቅዥት ሆኖ የሚታየን ነው የሚመስለን እንጂ በዕውንስ በዚያች የክርስቲያኖችና በእስላሞች አገር እንደዚህ ዐይነት ውርጅብኝ የሚወርድ አይመስለንም ነበር። ከቅዠታችን ባነን በአገራችን ምድር የተፈጸመውን አጸያፊና አሰቃቂ ድርጊት ዕውን ሆኖ ሲታየን የመንግስትን ሚናና ተልዕኮዉን እንድንጠይቅ ተገደናል። መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? የህዝብ አለኝታ ወይንስ ህዝቡንና ለህዝብ ጠበቃ የቆሙትን የሚከታተል? አገር ስትፈራርስ ዝም ብሎ የሚመለከትና አፍራሾችን የሚማጸን፣ ወይንም ድርጊቱ በሁሉም የተፈጸመ በማስመስል „እኛ ኢትዮጵያውያኖች ኃይላችንን ለጥፋት ከማዋል ይልቅ በመግባባት ለግንባታ ብናውለው ይሻላል“ ብሎ ማሾፍ፣ ይህ ዐይነቱ አባባልና የፖለቲካ አካሄድ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና በውጭ ኃይሎች የተደገሰልንን መጠፋፋትና እንዲያም ሲል መከፋፈል በቂጡ ካለማጤን የተነሳ ነው።
በተለይም የአለፈውን የሁለት ዐመቱን የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል በዶ/ር አቢይ የሚመራው አገዛዝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እኛ ነን የኦሮሞን ብሄረሰብ „ጥቅምና ፍላጎት የበለጠ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው“ ብለው በአክራሪነት ድምጻቸውን የሚያሰሙትንና የሚያደነቁሩንን፣ በሳይንስና በአንዳች ፍልስፍና ላይ ያልተመሰረተውን ከትግል ይልቅ የጥፋት ስልታቸውንና አካሄዳቸውን ስንመለከት እንደ ዕውነቱ ከሆነ ሁለቱም ኃይሎች የመንግስትን መሰረታዊ ተልዕኮና የፖለቲካ ትርጉም፣ እንዲሁም ደግሞ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ የተረዱ አይመስሉም። የሁለቱም አስተሳሰብና አካሄድ የኦሮሞን ብሄረሰብ „ጥቅምና የበላይነት“ በማስጠበቅ ላይ ያተኮረ እንጂ በዚያች ምድር ላይ በትክክል ቁጥሩ የማይታወቀውን በንጹህ መልኩ ሳይሆን በቅይጥ የሚገኘውን ከኦሮሞ ብሄረሰብ የሚበልጥ ወደ ዘጠና ሚሊዮን የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ እንደሚኖር የተረዱ አይመስልም። ከዘጠና ሚሊዮን በላይ የሚበልጠውም ኢትዮጵያዊ ልክ ኦሮሞ ነኝ እንደሚለው ኢትዮጵያዊ ሰላምን፣ ዲሞክራሲንና ብልጽግናን እንደሚመኝና ተግባራዊም እንዲሆንለት እንደሚፈልግ ግልጽ የሆነላቸው አይመስልም። ይህ ዐይነቱ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ታሪክ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የዲሞክራሲን ትርጉምና ዕውነተኛ ነፃነት ምን ማለት እንደሆነ ያላገናዘበ የአገዛዝ ስልትና የጽንፈኞች ጩኸት የመጨረሻ መጨረሻ ወደዚህ ዐይነቱ መረን የለቀቀና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊከተን በቅቷል። በተለይም ደግሞ የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አላት በምትባል አገር፣ ከአንዴም ሁለቴም የውጭ ጠላትን መክታ የመለሰች አገርና፣ ከአፄ ምኒልክ በኋላ የተካሄደው የዘመናዊነት ፖለቲካና የባህል ለውጥ በተካሄደበትና በኖርንበት አገር እንደዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ድርጊትና አገርን ለማፈራረስ መሯሯጥ በጣም ያናድዳል፤ የእነዚህ ጽንፈኞችና መንግስት የሚባለውም ተልዕኮ ምን እንደሆነ በቅጡ መረዳት ያስቸግራል። ማለት የሚቻለው ግን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር እንደ አገራችን ፖለቲከኞች ነን ባዮችና ለስልጣን እንታገላለን የሚሉ ጽንፈኛ ኃይሎች የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማሟላት እሽቅድምድሞሽ የሚደረግበት ሌላ አገር የለም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከአርባ ዐመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር በፖለቲካ ስም የተካሄደውን አሳፋሪ ድርጊትና አገር አፍራሽ ፖለቲካ በምንመረምርበት ጊዜ እንዲዚህ ዐይነቱ ድርጊት ሊመነጭ ወይም ሊፈጸም የሚችለው ትናንሽ ጭንቅላት ባላቸው ወይም አዕምሮአቸው ካልበሰሉ ሰዎች ብቻ ነው። የሚያሳዝነውም በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የሚነግዱ ትናንሽ ጭንቅላቶች ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደ አሸን መፍለቃቸውና የውጭ ኃይሎች መጫወቻ መሆናቸው ነው።
ያም ተባለ ይህ በዛሬው ወቅት ሁላችንም ግራ ተጋብተን እንገኛለን። ግራ የተጋባነውን ያህል በሁለት ጎራ ወይም ከዚያ በላይ በመከፋፈል እንደገና ስንፋለጥ እንታያለን። ይኸውም ዶ/ር አቢይን እንደሙሴ በሚመለከቱና፣ በሌላው ወገን ደግሞ ሰውየው ሌላ ተልዕኮ ያላቸው፣ በመሰረቱ የኦሮሞን ብሄረሰብ ጥቅም የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ እየሳቁ ሳያውቁት የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚሉ ግራ የተጋቡ መሪ ናቸው በሚሉት መሀከል። ከዚህ ውስጥ እጅግ አደገኛ የሆነው አስተሳሰብ ዶ/ር አቢይን እንደሙሴ ማየትና ማምለኩ ነው። ይህ ዐይነቱ ከፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው እጅግ አደገኛ አስተሳሰብና በራስ አለመተማመን በአብዮቱ ዘመን ወዴት እንዳመራን በግልጽ ይታወቃል። የኋላ ኋላም ደግሞ እ.ኢ.አ በ1997 ዓ.ም ምርጫው ከከሽፈ ወይም ውጤቱ በእነ መለስ ዜናዊ ከተነጠቀ በኋላ ታጋይ ይመስል ድምጹን አጉልቶ ያሰማ የነበረው ግንቦት ሰባት በመባል የሚታወቀው ድርጅትና መሪዎቹ ልክ እንደ አምላክ የሚታዩበት ወቅት ነበር። የእነሱን የተሳሳተ ሃሳብ፣ ሳይንስና ቲዎሪ አልባ የትግል ስትራቴጂያቸውን የሚቃወም ሁሉ ስድብና ማስፈራሪያ ይወርድበት ነበር። ይህ ዐይነቱ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ እስካሁንም ድረስ አለቅ ብሎን አንድን ግለሰብ አምላኪና፣ የኢትዮጵያንም ህዝብ ነፃ ሊያወጡት የሚችሉት ዶ/ር አቢይ ብቻ እንደሆኑና፣ ከደሙም ንጹህ እንደሆኑ አድርገን የምንቆጥር ጥቂቶች አይደለንም። በተለይም ደግሞ ተማርን የሚሉና የዶ/ር ዲጊሪ የጨበጡ ሰውየውን አምላኪ ሆነው ስናገኛቸው ጤና መሆናቸውን እንድንጠራጠር ተገደናል። ጥፋተኛው እሳቸው ሳይሆኑ እነጀዋርና በጸጥታው ውስጥም ሆነ በፖሊስ ውስጥ ተሰግስገው የገቡ ኦነጎችና ቄሮዎች ናቸው በማለት ነገሩን አቃለውና አድበስብሰው ለማለፍ ይሞክራሉ። ከዚህ በላይ በጣም አንጀትን የሚያቃጥለው ነገር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ቲአትር ሲሰሩ ስንመለከት ነው። ሰው እንደዚያ አረመኔ በሆነ መልክ ሲገደልና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ተከታዮች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉና ቤተክርስቲያናትም ሲወድሙ ከማዘንና ይህ ዐይነቱ አሰቃቂ ድርጊት እንዳይደገም በፍጥነት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሲስቁና ሲዝናኑ ወይም ችግኝ ለመትከል ደፋ ቀና ሲሉ ስንመለከት የሰውየውን የአዕምሮ ጤንንት ጉዳይ እንድንጠራጠር ተገደናል። ሰሞኑን ሊባኖን በተፈጠረው እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ የብዙ ሰዎች መሞትን አስመልክቶ የአገራችን መሪ የሆኑት ዶ/ር አቢይ አገራችን ውስጥ በተፈጸመው ድርጊት ሳይጸጸቱና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን ሰዎችና የወደሙ ከተማዎችን ሳያጽናኑና ሳይጎበኙ ለሊባኖን ህዝብ ሲቆረቆሩና የተሰማቸውን ሃዘን ሲገልጹ-አይግለጹ ማለቴ አይደለም- ሸሻመኔና ዝዋይ እንዲሁም ሌሎች ከተማዎች በሚኖረው የአማራው ብሄረሰብና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ በሆነው ህዝብ ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ የሰጡት መግለጫ የለም። የእኔም ሆነ የአንዳንድ ኢትዮጵያዉያን ጥያቄዎች ለመሆኑ ሰውየው በደንብ ማሰብ ይችላሉ ወይ? በልባቸው ውስጥ ርህራሄ የሚባል ነገር አለ ወይ? እንደዚህ ዐይነት እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጠር የአንድ አገር መሪ ሚና ዝም ብሎ ማየት ነው? ወይስ ቆራጥና ፈጣን እርምጃ መውሰድ? የሚሉቱን ጥያቄዎች እንድናነሳ ተገደናል። እሳቸው ስልጣን ከጨበጡ ጀምሮ የማን አለብኝነት ስሜት የተሰማቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ነን የሚሉ ፖሊሶችና የጸጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ በንጹህ ዜጎች ላይ፣ በተለይም ወጣት ልጆችን ሲገድሉ ምንም ዐይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም። እንደዚሁም ለገጣፎና ቡራዩ ዜጎች ከቤታቸው እንዲወጡ ሲደርግና ቤታቸውም ሲፈርስና ሜዳ ላይ ሲጣሉም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ የወሰደው ምንም ዐይነት እርምጃ የለም። ይባስ ብሎ በዚህ ዐይነት የወንጀል ድርጊት ላይ የተካፈሉትንና አመራር የሰጡትን የተሻለ ሹመት እንደሰጧቸው ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ፣ እያዩና እየሰሙ፣ እንዳላዩና እንዳልሰሙ ዝም ብሎ ማለፍ ወይም ድምጽን አለማሰማት ለጸጥታና ለፖሊስ ኃይሎች፣ ለእነጀዋርና ለኦነግ፣ እንዲሁም ለሌሎች የኦሮሞ ጽንፈኛ ኃይሎች የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። ባጭሩ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ ሻሸመኔና ዘዋይ እንዲሁም ሌሎች የኦሮሞ ክልል ቦታዎች በንጹህ ዜጎች ላይ የተፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊቶች ዝም ብለው የተፈጸሙ ሳይሆን በዕቅድ የተካሄዱ ለመሆናቸው የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ድርጊቱ ለምን በዚህ መልክ መከሰት እንደቻለና መንስኤውም ምን እንደሆን ጠጋ ብለን እንመልከት።
የህወሃት አገርን የማውደም የቤት ስራና ውጤቱ!
በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ዕምነት፣ በተለይም ማርክሲዝምን ሌኒንዝምን ሆነ ኮሙኒዝምን ለሚጠሉት ከ28 ዓመት ጀምሮ ጎልቶ የወጣው የብሄረሰብ ጥያቄና የህውሃትም ሆነ ዛሬ ደግሞ የኦዴፓ ወይም „የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ“ አገዛዝ መስፈንና ማንነት ዋናው መነሾው የተማሪው እንቅስቃሴ ያነሳው የብሄረሰብ ጥያቄ ነው የሚል ነው። በተለይም በእነ ዋለልኝ መኮንን ተጋኖ የቀረበው ኢትዮጵያ „የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት“ የሚለው ትረካ የብሄረሰብን አርማ አንሰተው ለሚታገሉ ወይም ገና በመጀመር ላይ ለነበሩ እንደመነሻ ሊሆናቸው እንደበቃና፣ የኋላ ኋላ እንዳየነው ለክልል ፖለቲካና ለወያኔ ፋሺሽታዊ አገዛዝ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይነግሩናል። ይህ ዐይነቱ አባባል ምናልባት ትንሽ ዕውነት ሊኖረው ይችል ይሆናል። በእርግጥም በተለይም የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ መሪዎች ነን በሚሉ ጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ ወደ ዛሬው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ለመክተት እንደቻለ የማይታበል ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ግን የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ ኤሊቶች የተማሩ ከሆነና፣ የተለያዩ መጽሀፍም እስካነበቡም ድረስ በተማሪው ማህበር መሪዎች ይናፈስ የነበረውን የብሄረሰብ ጥያቄ ለምን እንደ ዕውነት አድርገው ሊወስዱት ቻሉ? ለምን ለማወዳደርና፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ በትክክልኛ የምርምር ዘዴ በማጥናት ሚዛናዊና ትክክለኛ የሆነ ፍርድ ለመስጠት አልቻሉም? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ጉዳይ ነው።
በእኔ ጥናት መሰረት ይህን ዐይነቱን ውንጀላ የሚያነሱ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት፣ በተለይም ደግሞ የዩኒበርሲቲው የትምህርት ከሪኩለም ማን እንደቀረጸውና እንዴትስ እንደታቀደ በደንብ ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይመስለኝም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲና የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ፣ በተለይም የአሜሪካና የእንግሊዝ ጣልቃ-ገብ ፖሊሲና፣ አፄ ኃይለስላሴ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር የነበራቸው የቀረበ ግኑኝነት ለዛሬው አደጋ እንዳጋለጠን በፍጹም ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይመስለኝም። በአብዛኛዎቹ ዕምነት የብሄረሰብ ጥያቄ የተጸነሰው በተማሪው ማህበር መሪዎች ሲሆን፣ በአብዮቱም ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ለደረሰው ውጥንቅጥ ሁኔታና የወንድማማቾች ደም መፋሰስ ሁሉ ተጠያቂው በግራ ስም የሚታማው የተማሪው እንቅስቃሴ ነው የሚል ነው። እንደዚህ ብለን የምንገምትና የምናምን ከሆነ ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተዋቀርውን የዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታ በፍጹም አልገባንም ማለት ነው። በዚህም አማካይነት ከቬትናም ጀምሮ እስከ ካምቦጃ ድረስ፣ አንጎላና ሞዛምቢክ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ አገዛዝና፣ በ1950ዎቹ ዓመታት በኢራን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የሙሀመድ ሞሳዴግህ አገዛዝ በኩዴታ እንዲወርድ ከተደረገና ሻህ ስልጣን ላይ እንዲወጣ መደረጉ፣ ከዚያ በኋላ በአፍጋኒስታንና በኢራክ፣ በሶሪያና በሊቢያ በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጣልቃ-ገብነትና ግብዝነት የደረሰውን የታሪክ ውድመትና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት መነሾዋቸው ምን እንደሆን አልገባንም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር በነፃነት ስም አሳቦ የተለያዩ ብሄረሰብ እንቅስቃሴዎች መፈጠር ካለ አሜሪካንና እንግሊዝ፣ እንዲሁም ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮችና የአረብ አገሮች እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችን ከማከረባበትና ጥሬ-ሀብታቸውን ከመቆጣጠር ውጭ ተነጥሎ በፍጹም ሊታይ አይችልም።
ወደ ተጨባጩ ሁኔታ ሳንመጣ ህወሃት የሚባለው በእነ መለሰ ይመራ የነበረው ድርጅት ጥንስሱ የተጣለው እንግሊዝ ኤርትራን በሞግዚትነት በምታስተዳድርበት ዘመንና በአፄ ኃይለስላሴው መንግስት ላይ ከፍተኛ ተፅዕና በነበራት ዘመን ነበር። በዚያን ጊዜ የንቅናቄው ስም ወያኔ በመባል ይታወቃል። ኋላ ላይ መለስ የጅኔራል ዊንጌት ተማሪ በነበረበት ወቅት በጎሳ ፖለቲካ ላይ እንዲያተኩር በእንግሊዙ የስለላ ድርጅት እንደተመለመለ የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ዩኒቨርሲቲም ከገባ በኋላ ይህንን አቋሙን አጥብቆ በማንሳት ክርክር ያደርግ እንደነበርና ከአፉ በሚወጣው አግባብ ያልነበረው አባባል አንዱ ሊደበድብው ሲል በሌላ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ እንደዳነ አብረውት ከተማሩ ለመስማት ችያለሁ። ከመለስ ሌላ የግራ ስምን አንግበው የሚታገሉና አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ኤሊቶችና ከአማራውም በእንግሊዝ የስለላ ድርጅት የተመለመሉትና የብጥበጣ ፖለቲካ እንዲያካሂዱ የተደረገው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ነበር። በተለይም አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ሁኔታው ያላማራቸው አሜሪካና እንግሊዝ፣ እንዲሁም አንዳዶንዶች የምዕራብ አውሮፓ መንግስታትና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ድርጅት(NATO) እራሱ እነዚህን የመሳሰሉ አገርን አተረማማሽ ኃይሎች በገንዘብም ሆነ በመሳሪያ በመደጎምና በማስታጠቅ የአገራችን ፖለቲካ መስመሩን እንዲስት ለማድረግ በቅተዋል። ባጭሩ መለሰና ድርጅቱ ህወሃት፣ እንዲሁም ሌሎች የትግሬ ፕሮጀክትና የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ሳይሆኑ የውጭ ኃይሎች አገርን የማዳከምና ለዘለዓለም ደሃ ሆነው እንዲቀሩ የሚያደርግ ስትራቴጂ ፕሮጀክቶች ናቸው ማለት ይቻላል። እንደዚሁም ከጣሊያን ወረራና መሸነፍ በኋላ እንግሊዝ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ በነበረባት ወቅትና ኤርትራንም በሞግዚትነት በምታስተዳድርበት ዘመን ጀበሃ የተባለውን ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል እንዳደራጀት ይታወቃል። ከዚያም በኋላ ሻቢያም ሆነ „የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅትና“ በማርክሲስዝምና ሌኒንዝም ስም ይምሉ የነበሩ አንዳንድ ድርጅቶችና ኢድህ ራሱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የእንግሊዝ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ በግልጽ ይታወቃል። የተለያየ ስም ይዘው አገራቸንን ይወጉና ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆነው የሚያዳክሙ ከየት በሚያገኙት ገንዘብ ነው የሚንቀሳቀሱት፣ የሚኖሩትና መሳሪያም ይገዙ የነበረው? ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። ስራ እየሰሩ ደግሞ የጦር ትግል ማካሄድ እንደማይቻል ይታወቃል፤ ከአባላት ወይም ከደጋፊዎቻቸው ብቻ በሚገኝ ገንዝብ መሳሪያ ለመግዛትና፣ ከአንድ አውሮፓ ከተማ ወደ ሌላ፣ ከአሜሪካ ወደ ተለያዩ አረብ አገሮች ለመመላለስና በየሆቴልቤቶች ለማረፍ የሚያስችል ተከታታይ የሆነ የገንዘብ ምንጭ መኖር አለበት። ስለዚህም ምንጫቸው አንድ ብቻ ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮችና እንዲሁም የአረብ አገሮች በነፃነት ስም ለሚታገሉትንና አገራችንን ለሚያዳክሙትና ለመበታተን ለሚፈልጉት ዋናዎቹ የገንዘብ ምንጮች ነበሩ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከዚህ ውጭ ማሰብ ኢትዮጵያ ራሷን እንዳትችል ማድረግ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳትሆን መሰናክል መፍጠር፣ እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ እንዳትቀጥል እንደማድረግ ይቆጠራል። ለማንኛውም በእኔ ቲሲስ የምንስማማ ከሆነ በመለስ ዜናዊ መሪነት ህውሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን ፖሊሲ እንመልከት።
ህወሃት በመለስ መሪነት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ተግባራዊ ያደረገው አፓርታይድን የሚመስል የክልል ፖለቲካ ነው። ይህ ዐይነቱ የክልል ፖለቲካ በጣሊያን ጊዜ የተነደፈ ቢሆንም ጊዜን ጠብቆ ተግባራዊ ለመደረግ የበቃው በእንግሊዝና በአሜሪካን ግፊትና ድጎማ ነው። ምክንያቱም አጭር ነው። አገራችን በፌዴራል ስም በጎሳ የምትካለል ከሆነ አርቲፊሻል የሆነ ማንነት(Identity) ይዳብራል። በየክልሉ የዋር ሎርድነት መንፈስ የሚኖራቸው ኃይሎች በመፈጠር ከረጅም ጊዜ አንፃር ልክ እንደ ዘመነ-መሳፍንት አገዛዝ እርስ በራሳቸው ይፋለማሉ። ጆርጅ ፍሪድማን የሚባለው አሜሪካዊው ቀንደኛ የጦር ስትራቴጂስትና የሶስተኛው ዓለም ጦርነት እንዲመጣ የሚማጸነው እንደሚነግረን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራቡ ዓለም የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ላይ በቀጥታ ጦርነት ማወጅ አያስፈልገውም። በእሱ ዕምነት ለነጩ ዓለም የቤት ስራ የሚሰሩለት የየአገሩን ሰዎች ማደራጀትና ማስታጠቅ ብቻ ይበቃል። እነሱ ለእኛ የቤት ስራ ይሰሩልናል። እርስ በራሳቸው ሲከሳከሱ እንዲገፉበትና አገራቸውን እንዲያፈራርሱ አስፈላጊውን ዕርዳታ እናደርግላቸዋለን። በዚህ መልክ በአንድ በኩል የጥሬ ሀብትን ይዘርፋሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የበላይነታቸውን እንደያዙ ይቆያሉ። በዚያውም መጠንም የድህነቱንና የልመናውና ዘመን ይራዘማሉ። ህዝቦች በስምምነት የሚኖሩባትና እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ አገር የሚገነቡባት መሆኑ ቀርቶ በጥርጣሬ ዐይን እየተያዩ የውጭውን ኃይል፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን አገር አፍራሽ ፖለቲካ ተግባራዊ ያደርጋሉ። አገራችንም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚፈጠሩባትና የሚመረቱባት አገር መሆኗ ቀርቶ ወደ ታዛዥነት ትለወጣለች። ህዝቦቿም ዕውነተኛ ነፃነታቸውን እንዳያገኙ ይደረጋሉ።
ካለፉት 28 ዐመታትና ከዚያም በላይ በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የሚካሄደው ውዝግብ ከላይ የተዘረዘረውን ሁኔታ ነው የሚያረጋግጥልን። እነ መለስና ግብረአበሮቹ የፈጠሯቸው የክልል አስተዳደርና የጎሳ ፖለቲካ የአገራችንን ውድቀትና መበታተን ለማፋጠን ችለዋል። አገራችን እንደ አገር በሁለት እግሮቿ እንዳትቆምና ህዝቡም እንደማህበረሰብ ውስጣዊ እሴቱን በማጠንከር ጠንካራ አገር እንዳይገነባ ለህይወቱና ለታሪካ ስራ በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ እንዲጠመድ ተደርጓል።የፖለቲካውን መድረክ የጎሳና የማንነት እንዲሁም የሃይማኖት ጥያቄዎች ይዘውታል። የአህዳዊነት ወይም የአንድነት ጥያቄ የነፍጠኞች አስተሳሰብ ነው በመባል ሰፊው ህዝብ ተሸማቅቆ እንዲኖር ተደርጓል። የአማራ ብሄረሰብና የአማርኛ ቋንቋ፣ እንዲሁም የእርቶዶክስ ሃይማኖት እንደዋና ጠላት በመታየት ግድያና መሳደድ ይደረግባቸዋል። የአንዳንድ ክልል ወጣት መሪዎችም ይህንን ስነ-ልቦናን የሚያሸማቅቅ ነገር በማራገብ ሳያውቁት የኢምፔሪያሊስቶችንና የህውሃትን የሴራ ፖለቲካ ተግባራዊ ያደርጋሉ። ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ዕውቀትም ስለሌላቸው ክልላቸው እንዲበዘበዝ ሀብትን ዘራፊና ሀብትን ወደ አገራቸው አውጭ ለሆኑ ኢንቬስተሮች በራቸውን ክፍት በማድረግ ዕውነተኛ የኢኮኖሚና የማህብረሰብአዊ ዕድገት እንዳይፈጠር በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከአገራዊ ስሜት ይልቅ ጎሳዊና ሃይማኖታዊ ስሜትን በማዳበር ህዝቡ በዚህ እርኩስ መንፈስ በመጠመድ እግዜአብሄር የሰጠውን የመፍጠር ኃይልና ተፈጥሮአዊ ሀብት እንዳይጠቀም ለመደረግ በቅቷል። ለድህነትና ለጉስቁልና ኑሮ ሰለባ በመሆን ግለሰብአዊ ነፃነት እንዳይኖረውና በራሱ እንዳይተማመን ተደርጓል። በዚህ መልክ አገሪቱ በቀላሉ በእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ስር በመውደቅ ኋላ-ቀርነትና ድህነት ዕጣዋ እንዲሆኑ ለመደረግ በቅቷል፤ ህዝቡም ለማያቋርጥ ጦርነት ተዳርጓል። ምናልባትም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣ መስሎ የሚታይ ከሆነ የውጭ ኃይሎች መጥተው እንዲሰፍኑ በመደረግ የባርነቱ ዘመን እንዲራዘም ይደረጋል። ባጭሩ ዓለምን በሚቆጣጠረው የነጭ ኦሊጋሪክ መደብና በዓለም አቀፍ ስም የተቋቋሙት ድርጅቶች ዋና ተግባርና ዓላማ የተወሳሰበና የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸውን የአገራችንን ኤሊቶች በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ አለመረጋጋት እንዲኖርና የጥሬ-ሀብትም እንዲዘረፍ ያደርጋሉ። በተለይም ቻይና ኃያልና ተፎካካሪ ኃይል ሆና ከወጣች ጀምሮ የተያዘው ዘመቻ አገራችንና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ወደ ጦርነት ቀጠና ውስጥ መክተት ነው። የቻይናን ግፊትና ጥሬ-ሀብትን ማግበስበስ ዝም ብለን ማየት የለብንም እያሉ በግልጽ እየተናገሩና መጽሀፍም እየጻፉ ነው። በፖለቲካ ስም ህዝባችንን ግራ የሚያጋባው ታጋይ ነኝ ባይ ይህንን ዐይነቱን የነጭ ኦሊጋርኪውን እርኩስ ስትራቴጂ ነው ያልገባው። ህዝባችን የዚህን ዐይነቱን እርኩስ ዕቅድና ውጤቱን ከረጅም ጊዜ አንስቶ እየቀመሰውና፣ በዛሬው ወቅት ከፍተኛው ቦታ ላይ የደረሰ ለመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ የተገባ አይደለም። በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ደግሞ ኢምፔሪያሊዝምና ተዋናዮቹ አንድን አገር ለማዳከምና ለመበታተን የሚችሉበት በቂ የገንዘብና የማታለያ መሳሪያዎች አሏቸው። አንድን አገር ለመበታተንና ባህሏንም ለማውደም የግዴታ በዋር ሎርዶች ብቻ አይመኩም። በተለያየ መስክ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያኖችንም በመመልመል በገንዘብና በተለያዩ ቁሳቁሶች በማታለል ከውስጥ የመቦርቦሩንና የመበታተኑንም ሂደት ያፋጥኑታል። ከዚህ ውስጥ የስለላው መዋቅርና የኔዎ-ሊበራሊ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አገርን የማዳከም ዐይነተኛ መሳሪያዎች ናቸው።
ከዚህ ስንነሳ የእነ መለስ ዜናዊን የኢኮኖሚ ፖሊሲም ስንመለከት ፖሊሲው ዋሺንግተን ረቆ የመጣና ተግባራዊ የሆነ ነው። ዋና ዓላማውም ህዝባዊ ሀብትን መፍጠርና አገሪቱን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ ሳይሆን፣ ዘራፊና (Predatory State) አዘራፊ መንግስት እንዲዳብር ማድረግ ነው። በዚህ መሰረት በአንድ በኩል የጸጥታውና የሚሊታሪው፣ እንዲሁም የፖሊሲው ኃይል ይጠናከራሉ። አዲሱን ዘራፊና አዘራፊ መንግስት የሚጠብቁና ለውጭ ኃይሎች የሚያሸረግድ ይሆናል። በዚህ ዐይነቱ የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ኤሊት በመካተት የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ይደረጋል። በሌል ወገን ደግሞ ሆቴልቤትችና መዝናኛ ቦታዎች እዚህና እዚያ በመቋቋም ታዳጊው ወጣት እንዲባልግ ይደረጋል። አዲስ ዐይነት የወሲብና የሴተኛ አዳሪነት ባህል በመስፋፋት አገሪቱ እንዳለች ትበወዛለች። አዲሱና ታዳጊው ወጣት ይህንን ዐይነቱን ከውጭ የመጣ አገርን አውዳሚ አስተሳሰብ ትክክል ነው ብሎ በመቀበል በዚያው ይገፋበታል። በህውሃት የአገዛዝ ዘመን አገራችን የሴተኛ አዳሪዎች መፈልፈያ የሆነችውና የብልግና ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋባት አገር ለመሆን የበቃችው በዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ተንኮል ግን ደግሞ ቀላል ስትራቴጂ ነው። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊቱ ሞራሉ በከፍተኛ ደረጃ ከመውደቁ የተነሳ እንደሴተኛ አዳሪዎች ለፈረንጆች የሚያሸረጉድ ሆኗል። ህውሃት ፈረንጆችን ጓደኛ ለማድረግና ተጠያቂም እንዳይሆን ልዩ ልዩ የመዝናኛ ቦታዎችን በመክፈት ማንኛውንም ወጪ ያደርግላቸው እንደነበር ግልጽ ነው። አገር ቤት ከመጡ በኋላ ተደስተው እንዲመለሱ የማያደርገው ጥረት አልነበረም። በተለይም በልደቱ ስም ላሊበላ የተሰራው ሆቴል ቤት ዋናው ተግባሩ ሎቢይስቶችን ማስተናገጃ ነበር። በተጨማሪም እንደነ ሼራተን የመሳሰሉት የቅብጠት ሆቴል ቤቶች ሰላዮችን ማስተናገጃና የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚሸረቡበት ቦታዎች ናቸው። በዚህ መልክ ህወሃት ከውጭ ኃይሎች ጋር በብዙ ሺህ ድሮች በመተሳሰርና የእነሱን ጥቅም በማስጠበቅ በከፍተኛ ደረጃ ባህልን ያወደመና ጠንካራ መንፈስ ያለው፣ ማሰብና መመራመር የሚችል የህብረተሰብ ኃይል ብቅ እንዳይል ያደረገ ነው። ጠንካራ የሆነ ምሁራዊ ኃይልና ለህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ግልጋሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት በሌሉበት አገር ደግሞ የውጭ ኃይሎች የፈለጉትን ነገር ማድረግ ይችላሉ። አገርን በሁሉም አቅጣጫ በማዳከም ታዳጊው ትውልድ የሚሄድበትን እንዳያውቅ፣ ለምን እንደሚኖርና ምንስ ማድረግ እንዳለበት ግንዛቤ እንዳይኖረው ይደረጋል። ባጭሩ ወያኔ የውጭ ኃይሎች ቅምጥ የሆነ ማፊያዊ ቡድን ነበር ማለት ይቻላል። በእነሱ እየተበወዘና እየተመከረ አገርን ለውድቀት የዳረገ ድርጅት ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት የድርጅቱ መስራቾች ጭንቅላት በተበላሸና በውሸት አስተሳሰብ የታነፀና ጥላቻን መመሪያው በማድረጉ ብቻ ነው።
ወደ ሌሎች መስኮችም ስንሄድ የምናየው ነገር አገሪቱ የቱን ያህል በሁሉም አቅጣጫ ለመዳከምና ለመፈራረስ እንደቻለች እንገነዘባለን። የኢምፔሪያሊስቶችም ዋናው ዓላማ ጥቁር ህዝብ ጥበባዊ በሆነ መልክ መኖር የለበትም። አማምረው በተሰሩ ከተማዎች ውስጥ የሚኖር ህዝብ የመፍጠር ኃይሉ ከፍ ያለ ስለሚሆንና መንፈሳዊ ተሃድሶም ስለሚያገኝ የከተማና የቤት አሰራርም መበላሽትና መዘበራረቅ አለባቸው። ለምሳሌ በአገራችን ምድር በተለይም አዲስ አበባ ጊዝ (GIZ) በመባል በሚታወቀው የጀርመን ተራድኦ ድርጅት አማካሪነትና ተቋራጭነት የተሰሩትን ትላልቅ ፎቅ የመኖሪያ ቤቶች ስንመለከት ለሰው ልጅ መኖሪያ ታስበው የተሰሩ አይደሉም። ማንኛውንም ስታንደርድ ያልጠበቁ የቤት አሰራሮች ናቸው በከተማይቱ የተስፋፉት። ይህንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ለዕርዳታው ሰጪ ድርጅት ይሰራ የነበረ ጀርመናዊ እንደነገረኝ ከሆነ አገሪቱን እንደተጫወቱባት ነው። ባጭሩ አገዛዙንና የኢትዮጵያን ህዝብ ተጫውተንባቸዋል ብሎ በመጸጸት ነው የነገረኝ። እንደዚሁም ለድርጅቱ ይሰራ የበረ አንድ ጀርመናዊ አርክቴክቸር ይህንን ጉዳይ አረጋግጦልኛል። በዚህ መልክ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን የውጭ ገበያን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል የተተከሉት የስኳር ፋብሪካዎች ዕቅድ አውጭው በኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥ ይሰራ የነበረና አሁን ጡረታ የወጣ ጀርመናዊና ጓደኞቹ እንደሆኑ እራሱ የኮሚሽኑ ኃላፊ ቃል በቃል ነግሮኛል። ባጭሩ በወያኔ አገዛዝ ዘመን አገራችን የፈረንጆችና የአረቦች መጫወቻ የሆነች አገር ነበረች፤ አሁንም ናት። ህዝባችንም የተናቀበትና ወጣቱና ወጣት ሴት ልጆች ለወሲብ ስራ የተጋለጡበት አገር ነች።
ባጭሩ ባለፉት 28 ዓመታት ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንመረምርበት ጊዜ ናኦሚ ክላይን „The Shock Docktrine“ ብላ በሚገባ የተነተነችውን ዐይነት ሁኔታ በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንደሆነ እንመለከታለን። የአብዛኛው ህዝብ ጭንቅላት ከሶሻሊስታዊ ወይም ባህላዊ አስተሳሰብ በመላቀቅ በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መተካት አለበት። አትኩሮው በሙሉ ገንዘብ ማግኘትና ፍጆታን ገዝቶ መጠቀም መሆን አለበት። በሌላ አነጋግር ባህሉንና ሞራላዊ እሴቱን አሽቀንጥሮ በመጣል በአሜሪካው የፍጆታ አጠቃቀም ባህል መተካት አለበት። በፖለቲካ ስም ስልጣንን የያዙት ኃይሎች ምንም ዐይነት ዕውቀት የሌላቸውና፣ ስልጣን ላይ እያሉም መንፈሳቸውን ለማዳበር ስልጠና ስለማይወስዱና የተለያዩ መጽሀፎችን ስለማያነቡና ትችታዊ አስተሳሰብን ለማዳበር ስላልቻሉ ከውጭ የሚመጣ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ አገሪቱን የቆሻሻ ባህል መጣያ ለማድረግ በቅተዋል ። በውስኪና በልዩ ልዩ ቅንጦሽ የመጠጥ ዐይነቶች ጭንቅላታቸው ስለተበላሸ በአገራችን ምድር ምን ምን ነገሮች ይደረጉ እንደነበር የመገንዘብ ኃይል አልነበራቸውም። ስለሆነም በተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ከፍተኛ ማህበራዊና ባህላዊ ቀውስ ሲፈጠር መልስ ለመስጠት አቅቷቸዋል። አሰልቺና ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ ውስብስብ በመሆንና በመከማቸት መላወሻ ለማጣት በቅተዋል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ህወሃት 27 ዓመት ያህል ከገዛ፣ ከበዘበዘና ካስበዘበዘ በኋላ በድሮው ፖለቲካ ስልቱ ሊቀጥል ስላልቻለ በአዳዲስ ኃይሎች፣ ግን ደግሞ የተሻለ ሃሳብ በሌላቸው መተካቱ የታሪክ ግዴታ ነው። ስለሆነም ስልጣን ከህውሃት እጅ ተላቆ የኦሮሞን የበላይነት ወደሚያረጋግጥ „የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ“ እጅ መሸጋገሩ ሎጂካዊና አገርን ለአንድም ለመጨረሻም ጊዜ መበታተኛ ስትራቴጂ እንጂ በኢትዮጵያ ምድር ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ጠንካራ አገር ለመገንባት፣ የጎለመሰና በከፍተኛ ዕውቀት የዳበረና ፈጣሪ የሚሆን ህብረተሰብአዊ ኃይል ለመፍጠር አይደለም።
በሌላ ወገን ግን በአንዳንድ ጋዜጠኞችና ተንታኞች ይናፈስ የነበረው ወሬ፣ በተለይም አቶ ለማ መገርሳ ህውሃትን ከስልጣን ለማስወገድ የተጫወቱት ሚናና ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ከሀቁ የራቀ ነው። ዶ/ር አቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ለመሆን የበቁት በአሜሪካንና በሳውዲ አረቢያ መንግስት ግፊት እንደነበር የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ ይናፈስ የነበረው ወሬ በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን የደርግን ወታደር ብቻውን ማሸነፍ በመቻሉ ነበር የሚል ነበር። ሀቁ ግን የደርግ አገዛዝ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በጦርነት የተጠመደ ነበር። ከሶማሌ ወረራ አንስቶ ከሻቢያ የደፈጣ ሰራዊት ጋር ይካሄድ የነበረው ጦርነት፣ ከውስጥ ደግሞ በቀይና በነጭ ሽብር ስም ይካሄድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በእራሱ በደርግም ሆነ በሚሊታሪውና በፀጥታው ውስጥ የነበሩ ለሲአይኤ (C.I.A) መረጃ የሚያቀብሉ ሰዎች፣ ወያኔ የሚመካባቸው የውስጥ አርበኞችም ጭምርና ቀስ በቀስም የወታደሩ በጦርነት ብዛት መስልቸትና መዳከም…ወዘተ. ለደርግ አገዛዝ መውደቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ወደነ አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አቢይ ስንመጣም ተመሳሳይ ሆኔታን እናያለን። የቲም ለማ ስልጣን ላይ መውጣት በአረቦችና በሲአይኤ ጣልቃ-ገብነትና ግፊት እንደሆነ ግልጽ ነው። ቄሮም የሚባለው የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴ ዋናው አንቀሳቃሾች የውጭ የስለላ ድርጅቶች ናቸው። በሃይማኖት ስም ተሳቦ በአገሪቱ ምድር በተለይም በሀረርና በወለጋ የሚዘዋወሩ የቱርክ፣ የእንግሊዝና የአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የስለላ ድርጅቶች የጀርባ አጥንት ሆነው በመስራት የወያኔን ውድቀት አፋጥነዋል። ዓላማቸው ግን በዚህ መልክ ስልጣንን ከአንዱ ወደ ሌላ ኃይል ለማሽጋገር ሳይሆን አገሪቱን አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ለመክተትና በቀጠና ለመከፋፈልና የራሳቸውን ጦር ለማስፈንና ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ከዓለም ካርታ ለማጥፋት ነበር።
ይህ ስትራቴጂ ግን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። ለማንኛውም ይህንን የሚክድ ካለ 27 ዐመት በሙሉ ምን ይሰራ እንደነበረ አያውቅም ማለት ነው። የውጭ ኃይሎች አንድን አገር ለማዳከም ሲሉ በአንድ ኃይል ብቻ አይመኩም። አንደኛው ኃይል በአንዳች ምክንያት የሚያፈነግጥ ከሆነ አሊያም ደግሞ ከህዝብ ግፊት ሲበዛበትና እራሱም በፈጠራቸው ቀውሶች ሲወጠር ስልጣን ላይ የመቆየት ኃይሉ ስለሚዳከም ከመጀመሪያውኑ አማራጭ ኃይል ያዘጋጃሉ። በዚህ መሰረት የእነቲም ለማ ስልጣንን መያዝ የሚያስገርም ነገር አይደለም።
ባጭሩ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ እንደትወጠርና ከውስጥ ደግሞ በጽንፈኛ ኃሎች እንድትበታተን ወይም የጦርነት አውድማ እንድትሆን ትልቅ የቤት ስራ የተሰራው በህውሃት ዘመን ነው። ሲአይኤ የሚባለው ትልቁ ሰይጣናዊ የስለላ ድርጅት፣ ሞሳድ፣ የግብጽና የሳውዲ አረቢያና የቱርክ የስለላ ድርጅቶች በመግባትና በመውጣት አስፈላጊውን አገርን የመበታተኛ ስትራቴጂ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል። ይህንንም ራሳቸው በግልጽ ይናገራሉ። አንደ አጋጣሚ ሆኖ በአንድ የግሎባል ፖለቲካን አስመልክቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ በየጊዜው ኢትዮጵያ የሚመላለስ ይሁዲ አሜሪካዊና ምናልባትም የሞሳድ ሰላይ ከሆነ ሰው ጋር ተገናኝቼ የነገረኝን ስሰማ በጣም ነው የተበሳጨሁትም፤ ያዘንኩትም። እንደነገረኝ ከሆነ ኢትዮጵያ የተሰረረች አገር ነች። ተጫውተንባችኋል ነው ያለኝ። በመፀፀትም እናንተ ኢትዮጵያውያን ምን ነካቸሁ? ብሎ እንደገና መልሶ ጥያቄ አቀረበልኝ። እነመለሰና ህወሃት እንዲዚህ ዐይነቷን እንደወንፊት ብዙ ቀዳዳ ያላትንና የሰላዮች መፈንጫ የሆነች አገርን ነው አስረክበውን የሄዱት። የዛሬው ሁኔታ በዚህ መልክ መከሰቱ ይህንን ያህልም የሚደንቅ አይደለም።
የመደመር ፍልስፍናና የፍቅር ፖለቲካ መክሽፍ!!
ዶ/ር አቢይ የጠቅላይ ሚንስተርነትን ቦታ ሲይዙና ንግግር ሲያደርጉ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። በእኝህ „ብሩህና መልከ መልካምና ሳቂተኛ መሪ“ አገራችን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ትሸጋገራለች የሚል ዕምነት ነበረን። የዲሞክራሲውና አገርን በጋራ የመገንባት ዘመን መጣ ብለን አንዳንዶቻችን ሻንጣዎቻችንን ለማዘጋጀት ቀና ደፋ ስንል ነበር። በእርግጥም አብዛኛዎቻችን መንፈሳችን ከመነቃቃቱ የተነሳ የዛሬውና የመጭው ትውልድ አዲስ የተስፋ ብርሃን የሚያዩበት አገር የተቃረበ መስሎን ነበር። በዚህ ላይ የፍቅር መዝሙርና የመደመር ፍልስፍና ለአገራችን ግንባታ መመሪያ ይሆናሉ የሚል ዕምነት ነበረን። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ተስፋ ባጭር ጊዜ ውሰጥ ወደ ጨለማነት እየተሸጋገረ ይመጣል። ጊዜው የኛ ነው በማለት መዝናናት የጀመሩ ፅንፈኝ ኃይሎች ፍቅርንና መደመርን ከማሳየት ይልቅ መጤ እያሉ ማሳደድና መግደል፣ ወይም ደግሞ ከቤታቸው እንዲወጡ በማድረግ በየሜዳው ላይ እንዲወድቁ ለማድረግ በቁ። በመደመር ፈንታ መቀነስና መቀናነስ፣ በፍቅር ፈንታ ጥላቻና ማሳደድ ቦታውን ተኩ። በጠባብ መንፈስ የተወጠሩና የፍቅርንና የመደመርን ትርጉም መረዳት ያቃታቸው የዘመኑ ፅንፈኛ ኃይሎችና አንዳንድ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር ቀደም መሪዎች መዝናናትንና ማስፈራራትን ዋናው የአመራር ስልታቸው አደረጉ።
በመጀመሪያ መደመር የሚለው የፖለቲካ ዘይቤ ሳይንሳዊ ሳይሆን ሁሉንም ማግበስበስ ነው። „ፍልስፍናዉ“ በተግባር ሲመነዘር ብሩህ አመለካከትና ርዕይ ያላቸውን የተማሩ ዜጎችን መሰብሰቢያ ሳይሆን ቄሮዎችንና ኦነገዎችን ማግበስበሻ ዘዴ ለመሆን በቅቷል። በመደመር ስም ተግበስብሰው የገቡትና ቦታ የተሰጣቸው በቅናትና በጥላቻ መንፈስ ናላቸው የዞረና ስንትና ስንት ወንጀል የሰሩ ናቸው። አንዳንዶችም በውጭ ኃይሎች ደሞዝ እየተከፈላቸው በየሚኒስትሪው ውስጥ መቀመጫ የሚያሞቁ ናቸው። የአዲሱ የገዢ መደብ የማህበራዊ መሰረት ናቸው። በዚህ መልክ በመደመር ስም የፖለቲካ መድረኩ ለጽንፈኞች፣ ለሲአይኤና ለአረብ ተላላኪ ለሆኑት እንደነጃዋር ላሉት ሲለቀቅና እንደልባቸው እንዲፈነጩ ሲደረግ፣ ሰፊው ህዝባችን ደግሞ እንዲሸማቀቅ ተደርጓል። ባጭሩ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በመደመር ስም የፖለቲካ መድረኩን የሽወዳ ፖለቲካና የኦሮሞ ጽንፈኞች ማጠናከሪያ አድርጎታል ማለት ይቻላል። በዚህም መሰረት ይህንን አካሄድ የሚቃወሙ አይ ይታሰራሉ፤ ካሊያም በዘዴ እንዲወገዱ ይደረጋሉ። ሰሞኑን ወደ ውጭ የተለቀቀው የሺመልስ አብዲሳ ንግግር ይህንን ነው ያረጋገጠልን። አንደነ አቶ ታዬ ደንደዓን የመሳሰሉ የሺመልስ አብዲሳን አባባል ለማስተባበልና የፓርቲው የፖለቲካ ስልት እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ሞክረዋል። እነ አቶ ታዬና ሌሎች ቀና አመለካከት አላቸው የሚባሉ „የኦሮሞ ፖለቲከኞች“ በሻሸመኔና በዝዋይ እንዲሁም በሌላ ቦታዎች እንደዚያ ዐይነት የዘገነነ ስራ ሲፈጸም ጣልቅ በመግባት ነገሩ እንዲበርድ አላደረጉም። ድርጊቱን አደባብሰው ነው ለማለፍ የሞከሩት። በአነጋገራቸውና በድርጊታቸው አንድን ማህበረሰብ ለማስተዳደር እንደማይችሉ ለማረጋገጥ ችለዋል። ኦሮሞ ነኝ ለሚለው ወጣትም ሆነ እዚያው ተወልዶ ላደገውና ከሌላ ብሄረሰብ ከተወለደው የትምህርትና የሙያ መሰልጠኛና የስራ ዕድል ማመቻቸት አልቻሉም። ወጣቱ በየሺሻው ቤት ተቀምጦ ጊዜውን የሚያሳልፍና ጨአት የሚቅምና፣ ሌላው ደግሞ በየመንገዱ ጊዜውን ዝም ብሎ የሚያሳልፍ ነበር፤ አሁንም ነው። እንደዚህ ዐይነቱን ምንም ህልም የሌለውንና ስራ-ፈቶ የተቀመጠን ወጣት ለመቀስቀስና ለመጥፎ ተግባር ለማሰማራት ደግሞ ቀላል ነው። እነ ጀዋርን በገንዘብ የሚደጉሙት የውጭ ኃይሎች፣ ግብጽ፣ ሳውዲ አረቢያና ሲአይኤ በዚህ መልክ ነው ጊዜን ጠብቀው አጠቃላይ ጦርነት ያወጁብን። እነ ሺመልስ አብዲሳና ግብረአበሮቹ ይህንን የመሰለውን የውጭ ሴራ ነው በቅጡ ያልተገነዘቡት። የመጨረሻ መጨረሻ እነውክለዋለን የሚሉትም ህዝብ ተጠቃሚ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠቃና ኃይሉም ሊበታተን እንደሚችል የገባቸው አይመስልም። በጣባብ አስተሳሰባቸው በመገፋፋት በአማራውና በተቀረው ብሄረሰብ፣ እንዲሁም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ዘመቻ ሲከፍቱና ሲያሳድዷቸው በገንዘብ የናጠጡ እንደሳውዲ አረቢያ የመሳሰሉ አገሮችና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የውስጥ ለውስጥ አገርን የሚያፈራርስ ስራ እንደሚሰሩ ለመገንዘብ የቻሉ አይደሉም። ወደፊትም ሊገንዘቡ አይችሉም። ጭንቅላታቸው በዝቅተኛ ስሜት ስለተወጠረና ጥላቻን መመሪያቸው ስላደረጉ በጀመሩት የጥፋት ተግባር ከመግፋት ይልቅ የነገሩን ውስብስብነትና የውጭ ኃይሎችን ሴራ ቆም ብለው ለማጤን የሚችሉ ኃይሎች እንዳይደሉ አረጋግጠዋል። በሌላ ወገን ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ዘግናኝ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የፈለጉትን ቢዘላብዱም ከእንግዲህ ወዲያ ማንም የሚሰማቸውና የሚያምናቸውም የለም። ባለፉት ሁለት ዓመታትም ያረጋገጡት የራሳቸውን የበላይነት ለማስፈን ነው። በኦሮምያ ክልል የተካሄደውን ዘርና ሃይማኖት ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋ ትላንት የተጀመረ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ያየነውና እየተለማመድነው የመጣን ነን። ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና የቀብር ስርዓት በኋላ ዘርን የማጥፋትና ሀብትን የማውደም ዘመቻ ካለፈው የቀጠለና ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ነው። በዚህ የዘር ማጥፋትና አገርንና ሀብትን የማውደም ዘመቻ ሁሉም ተጠያቂዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ማንም እየተነሳ የሚፈነጭባት አገር ሳትሆን ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎባት ለእኛ የተላለፈች ነች። ኦሮሞዎች ብቻ አይደሉም ይህችን አገር የገነቡ፣ ወይም ደግሞ ብቻቸውን በመሆን ከውጭ የመጣን ጠላት የተጋፈጡት። ስለሆነም የኦሮሞ ልሂቃን በአውሮፓውያንና በአሜሪካን የኢቫንጄሊካን ሃይማኖት ቀስቃሽነትና ግፊት የሚያደርጉት ቅጥ ያጣ መራወጥና እነሱ ብቻ እንደተጨቆኑ አድርጎ ማቅረብ በህብረተሰብ ታሪክና ወይም በስልጣኔ ሚዛን የሚረጋገጥ አይደለም።
የኦሮሞ ሊህቃን ትረካና ይህንን ዐይነቱን ትረካ በተግባር የሚመነዝረው የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ያልተገነዘቡት ነገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ አንዳቸውም ቢሆን የራሳቸውን የጎሳ አወቃቀር ስርዓትና የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሰረት በፍጹም አያውቁም። ይሁንና ግን እየደጋገሙ ሊያሳምኑን የሚሞክሩት የአፄ ምኒልክ አገዛዝ ወደ ደቡቡ ክፍል ከመስፋፋቱ በፊት የዳበረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ማህበረሰብ እንደነበራቸው ነው። ትላልቅ ከተማዎች የነበሯቸውና፣ የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴያቸውም ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ነበር። በጥበብና በአርክቴክቸር፣ እንዲሁም በስነ-ጽሁፍ የላቅን ነበርን ይሉናል። በኢንፍራስትራክቸርም የተያያዙና በባቡርና የውስጥ ለውስጥ በሚካሄድ ተጓዥ የሚገናኙ ከተማዎች ነበረን ይላሉ። በስራ-ክፍፍልና በምርምርም ከሌላው ኢትዮጵያ ግዛት በልጠን የምንገኝ ነበርን ይሉናል። ይህንን ዐይነቱን ወርቅ የሆነና የዳበረ ስረዓት ነው በአፄ ምኒልክ የሚመራው ኋላ ቀር የአማራ ህዝብ መጥቶ ስልጣኔያችንን ያወደመብን እያሉ የተረት ተረታቸውን ይተርካሉ። በሌላ አነጋገር፣ የኦሮሞ ልሂቃን በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ የማይረጋገጥ ነገር ነው የሚነግሩን። በሁለተኛ ደረጃ፣ እነዚህ ልሂቃን በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ህብረ-ብሄር ሲመሰረት ስንትና ስንት መንገዶችን መጓዝ እንዳለበት ሊረዱ ያልቻሉ ናቸው። በሶስተኛ ደረጃ፣ አንድ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ በአንድ ጎሳ ብቻ አገርን ለመገንባት እንደማይችል የተረዱ አይደሉም፤ ለመገንዘብም አይፈልጉም። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ በአንድ ጎሳና በአንድ ቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተና የዳበረ፣ እንዲሁም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነ አገር በፍጹም የለም። በአራተኛ ደረጃ፣ አብዛኛዎቹ የእሮሞ ልሂቃን በውጭ ኃይሎች እየታገዙ ነው የሚንቀሳቀሱት። አስተማሪዎቻቸው የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ፋሽሽታዊ አመለካከት ያላቸው ናቸው። በጥቁር ህዝብ ዘንድ መከፋፈል እንዲኖርና ወንድማማች ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ ሌት ተቀን የሚሰሩ ናቸው። እንደነ ጃዋር የመሳሰሉት ደግሞ በሳውዲ አረብያ፣ በግብጽና በአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት የሚደገፉና የሚመከሩ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ናቸው በመደመር ስም አገር ቤት ተግበስብሰው በመግባት አገሪቱን ወደ ጦር አውድማነት የለወጧት። የሁለቱም ኃይሎች ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተሳሰሩ ነገሮችን ማውደምና አዲስ የውጭ ኃይሎች ተቀጥያ የሆነች አገር መመስረት ነው። እነጃዋር ደግሞ የእስላሚክ ሪፑብሊክን ማቋቋም ነው። የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ይህንን ነው ያዘጋጀልን።
ለማንኛውም አገዛዙም ሆነ እነዚህ ኃይሎች ያልገባቸው አንድ ነገር አለ። በእነሱ አካሄድና ቅስቀሳ የፈለጉትን ግብ መምታት እንደማይችሉ ነው። ምናልባት ዋና ዓላማቸው አገርን ወደ ጦር አውድማነት መለወጥ ባይሆንም ድርጊታቸውና ቅስቀሳቸው ሁሉ የውጭ ኃይሎችን በመጋበዝ የኢራክ፣ የሶርያ፣ የሊቢያና የአፍጋኒስታን ዐይነት ሁኔታ መፍጠር ነው። የሰሜን አትላንቲክ ጦርም (NATO) ይህንን ይነቱን የግብዣ ሁኔታ ነው የሚጠባበቀው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የዛሬው የገዢ መደብና ሌሎች የኦሮሞ ጽንፈኞች የዓለም ፖለቲካ እንዴት እንደሚካሄድ አልገባቸውም። የእኛው መፋጠጥና የእርስ በእርስ መጨራረስ ለእነሱ የስርግ ምላሽ እንደሆነ የተገነዘቡ አይደሉም። አንድ አገር በጠንካራ ዕይታና ውስጣዊ አንድነት ብቻ እንደሚገነባ የተረዱ አይመስሉም። ከቻይና፣ ከራሺያና፣ ከሲንጋፖርና ከጃፓን የተማሩት ነገር የለም። ጥረታቸውና ትግላቸው በሙሉ በደመ-ነፍስ በመመራት የኢትዮጵያን መፈረካከስ ማፋጠን ነው። ግፉበት እንላቸዋለን!! በርቱ በርቱ እንላቸዋለን!! ይሁንና ግን በዚህ ድርጊታቸው ገነት ውስጥ ሳይሆን ገሃነም ውስጥ እንደገሚገቡ ልናረጋግጥላቸው እንችላለን!!
ባጠቃላይ ሲታይ ዶ/ር አቢይ ስልጣንን ከተቆናጠጡ ጀመረው በአገሪቱ ውስጥ ስላም እንዲሰፍን ያደረጉት ምንም ዐይነት ዕርምጃ የለም። የዶክትሬት ስራቸው ሰላምና መታረቅ (Peace and Reconciliation) የሚል ቢሆንም ድርጊታቸው በሙሉ የኦሮሞ በላይነትን ማስፈን ነው። አቶ ሺመልስ አብዲሳም የነገረን ይህንን ነው። የብልጽግና ፓርቲ ዋና ዓላማው አዲስና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሳይሆን የኦሮሞ የበላይነትን ማስፈንና አዲስ የታሪክ አሻራ ማስፈር ነው። የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ መለወጥና ስሟንም ወደ ፍንፍኔ የመለወጡ ጉዳይ የስትራቴጂው ዋናው አካል ነው። ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባው ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የቤት ስራውን ሰርቷል። ባጭሩ ታሪክ እንደዚህ ነው። አሁን ትግሉ የለየለት ነው። እኛ ሳንናገር ምን እንደሚፈልጉና ዓላማቸውም ምን እንደሆነ በዝርዝር ነግረውናል። በሌላ ወገን ግን የሺመልስ አብዲሳ አስተማሪ የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው እንደነገሩን ከሆነ ሺመልስ አብዲሳ ፍልስፍና የተማረና፣ በተለይም የፕላቶንን ሪፑብሊክ መጽሀፍ እንዳነበበና ለከፍተኛ ሹመትም እንደሚበቃ ነው። ይሁንና ግን ፕላቶ ሪፑብሊክ በሚለው መጽሀፉ ውስጥ የሚያስተምረን ስለፍትሃዊነት፣ አንድን ከተማ ወይም አገርን በስነ-ስረዓትና ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባትና ማስተዳደር፥ እንዲሁም በገዢው መደብና በተገዢዎች መሀከል መቃቀር እንዳይኖር አንድን ከተማም ሆነ አገርን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ምን ዐይነት ፖለቲካ መከተል እንዳለባቸው ነው። ከዚህም አልፎ ፕላቶ በመጽሀፉ ውስጥ ስለ ስራ-ክፍፍልና ስለንግድ አስፈላጊነት በማውሳት በዚህ አማካይነት በአንድ አገርም ሆነ በአንድ ከተማ ውስጥ በሚኖር ህዝብ መሀከል ውስጣዊ ግኑኝነት(Organic Link) ይፈጠራል። በመቀጠልም በፕላቶንም ሆነ የሱን ፈለግ በመከተል የፖለቲካ ፍልስፍናን ባስተማሩት ጠቢባን መሰረት ተፈጥሮም ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጽባቸው፣ እዚያው በዚያው አንድነትና ብዝሃት የሚታዩባቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር ተፈጥሮም ሆነ አንድ ህብረተሰብ አንድ ወጥና አንድ ዐይነት አመለካከት ባላቸው ነገሮች በፍጹም አይመሰረቱም። ይህ የተፈጥሮና የህብረተሰብ ህግ ነው። ከዚህም በላይ በፕላቶ ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠር ቀውስ ዋናው ምክንያቱ ኢ-ፍትሃዊነት ሲነግስና ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ከጥበባዊ ፖለቲካ ይልቅ ሲባልጉና፣ በትዕቢትና በደመ-ነፍስ አገርን መምራት ሲጀምሩ ነው። ፖለቲካን ከሞራል ጋር ማገናኘት ሲሳናቸውና ከሀቀኛነት ይልቅ ማታለልን ዋናው የፖለቲካቸው ዘይቤ ሲያደርጉ በአንድ አገር ውስጥ ያልታቀደ ብጥብጥ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲከሰት መንገዱን ያሳምራሉ። ስለሆነም የፕላቶ ዋናው የፖለቲካ መመሪያ ፍልስፍናዊ አርቆ ማሰብ ነው። አንድ መሪ ራሱን ወደ ውስጥ የመመልከትና በየጊዜውም የመመርመር ኃይል እንዲኖረው ያሳስባል። በእሱ ዕምነትም በጎሳ ላይ የተመሰረት ፖለቲካ ፖለቲካ ሳይሆን የብጥብጥ መነሻ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንደነፃ ሰው አድርጎ መቁጠርናና፣ እንዲሁም የጠቅላላው የማህበረሰብ አካል መሆኑን መገንዘብ ያለበት እንጂ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የመጣሁ ነኝ ብሎ ማሰብ የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻ ማንኛውም ሰው ሰው መሆኑና በእግዚአብሄርም አምሳል እንደተፈጠረ ይገነዘባል። ይሁንና በፕላቶን ፍልስፍና የተመረቀው ሺመልስ አብዲሳ የሚነግረንና ተግባራዊም የሚያደርገው ፖለቲካ ሌላ ነገር ነው። ፕላቶንም ይህንን የሺመልስ አብዲሳን ንግግር ከመቃብሩ ውስጥ ሆኖ ቢሰማ ኖሮ ይገላበጥ ነበር።
ይህን ካልኩኝ በኋላ አንዳንድ አገዛዙን የሚደግፉ፣ በተለይም ለዶ/ር አቢይ ልዩ ፍቅር ያላቸው በአገራችን ምድር የተካሄደውን ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ጂኖሳይድ አይደለም፣ ዘር ተኮርም ሊባል አይገባውም፣ ወይም አትበሉ ለሚሉት የምነግራቸው ነገር ማፈር አለባቹሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያም እንደሰው አንቆጥራችሁም ነው የምላቸው። አቶ ኦባንግ ሜቶ በትክክል እንዳለው ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገውን ጭፍጨፋ ጄኖሳይድ ብላችሁ አትጥሩ ማለት ከሰው በታች እንደመውረድ የሚቆጠር ነው። ይህንን የሚሉ ሰዎች መንፈሰ-አልባ ናችው። ፍቅራቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ለአንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን ነው ያረጋገጡት። ምናልባት በዚህ አስተሳሰባቸው ፖለቲካ የሰሩ መስሏቸው ይሆናል። ተሳስተዋል። ፖለቲካና ሞራል፣ ፖለቲካና ሀቀኝነት፣ ወይም ለዕውነት መቆም አንድ ላይ ሊሄዱ አይችሉም ያለው ማነው? በፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና መሰረት ሰውን ስትገድልና ስታሳድድ ወይም ስቃዩን ስታሳየው ብቻ ነው ፖለቲካ የሚባለው ነገር ሳይንስነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው ያለው ማንነው? በአንድ አገር ውስጥ እንደዚህ ዐይነት አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም የአንድ ጠቅላይ ሚኒስተር ዋና ተግባር ዝም ብሎ መመልከት ብቻ ነው ያለውስ ማን ነው?
ያም ሆነ ይህ ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ በአገራችን ምድር የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽልና እርግጠኝነትም እንዲሰማው የሚያደርገው ነገር ተግባራዊ ሲሆን አይታይም። ሰፊው ህዝብ የመደራጀትና የመታጠቅ መብት፣ እንዲሁም የመጠየቅ መብት የለውም። ያልተማረና ያልነቃ እንዲሁም ያልተደራጀ ህዝብ ደግሞ በቀላሉ በውጭ ጠላት ሰለባ ይሆናል። አርቆ የማሰብ ኃይሉም ደካማ ስለሚሆን መንግስትም ሆነ የውጭ ኃይሎች የሚነግሩትን ብቻ በመስማት አገርና ባህል እንዲፈራርሱ ያደርጋል። ዶ/ር አቢይም እንዲዚህ ዐይነቱን ዝም ብሎ የሚሰማቸውን ዜጋ ወይም ሰው የሚፈልጉ ነው የሚመስለው። ስለሆነም የምጠየቅና የምተች አይደለሁም ባይ ናቸው። እኔ የምለውን ዝም ብላችሁ ስሙ ነው የሚሉን። የሳቸውን ዕምነት የሚያራምዱና በየኤምባሲዎች በመጋበዝ መጽሀፍ ቅዱስን የሚያነቡ የሚነግሩንም ይህንን ነው። መንግስትን አትጠይቁ፣ አትተቹ ይሉናል። የእናነተ ዋና ተግባር እንደከብት ዝም ብላችሁ መነዳት ነው። በዚህ አነጋገራቸው እነካንትና ሄገል፣ እንዲሁም በሺሆች የሚቆጠሩ የኢንላይተንሜንት ምሁራን ያስተማሩንንና የተዋጉትን ዲስፖታዊ አመለካከትና አገዛዝ ትክክል አይደለም ነው የሚሉን። ስለሆነም ቄሮዎች ሲደበድቧችሁና ሊገድሏችሁ ሲመጡ ዝም ብላችሁ እጃችሁን ስጡ የሚል ፍልስፍና ነው የሚያስፋፉት። አገዛዙን መቃውም ወይም መተቸ ክልክል ነው። አትተቹ፣ አትተንፍሱ እየተባልን ነው። በሌላ ወገን ደግሞ መጽሀፍ ቅዱሱ የሚለን፣ ፈልግ ታገኛለህ፣ ጥያቄም ጠይቅ መልስ ይሰጥሃል፤ በመጠየቅና በመመራመር ብቻ አዲስ ነገር ታገኛለህ፤ አንኳኳ በሩ ይከፈትልሃል፤ ለማየት ዐይን ሰጥቼሃለሁ፤ ለማሰብም አዕምሮ ለግሼአለሁ፤ ስለሆነም ዝምብለህ እንደ ከብት አትነዳ ነው የሚለን። በማሰብና በመመራመር ኃይልህ የተፈጥሮን ምስጢር በማወቅ አዲስና የተሻለ ማህበረሰብ በመገንባት ተስማምተህ ኑር። ጭንቅላትህን የማትጠቀምና አርቀህ የማታስብ ከሆነ ግን ለዝንተ-ዓለም እንደተረገምክ ትኖራለህ ይለናል።
ስለሆነም የዛሬውን የአገራችንን ሁኔታ በምንቃኝበት ጊዜ አገራችን በለውጥ ስም ወደ ዲስፖታዊ አገዛዝ እያመራች ነው። ወደ ኦሮምያ ክልል ስንመጣ ደግሞ ፋሺሽታዊ አገዛዝ የሚመስል የሰፈነባት ነው። የክልሉን የተለያዩ ከተማዎችም ሆነ ገጠሩን ያለሙና የገነቡ፣ የቅድመ-አያቶቻቸው ያቀኗቸውና ከሶስት መቶና አራት መቶ ዐመት በፊት የመሰረቷቸውን መንደሮችና ከተማዎች የልጅ ልጅ ልጆቻቸው መጤዎች እየተባሉ ይባረራሉ፤ አሊያም ይገደላሉ፤ የተቀሩት ደግሞ ፍዳቸውን ያያሉ። በዛሬው ወቅት የእሮሚያን ክልል የሚያስተዳድሩት መሪዎችና ቄሮዎች ለማሳመን የሚሞክሩት መሬቱንና በመሬት ውስጥ የሚገኘውን ሁሉ እኛ ነን የፈጠርነው፣ አሊያም ደግሞ እግዚአብሄር ለእኛ ብቻ ባርኮ የሰጠን መኖሪያ ነው እያሉ የሚነግሩን። ባጭሩ ፀረ-ስልጣኔና አገር በታታኝ የሆነ አገዛዝ መጤ የሚባለውን፣ ግን ደግሞ እዚያው የተወለደውንና ያደገውን፣ እንዲሁም ሀብት ያፈራውን እያዋከበና በፍርሃት እንዲኖር አድርገውታል። ይህ ዐይነቱ አገዛዝ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን መኖር የለበትም።
ወደ ፌዴራል አስተዳደሩ ስንመጣ ደግሞ በመንግስት መኪና ውስጥ አሁንም ቢሆን ስንትና ስንት ወንጀለኞች ተሰግስገዋል። ከወያኔ ጋር እጅና ጓንቲ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ አዲስ ሹመት ተስጥቷቸው አሁንም ቢሆን ፀረ-ዲሞክራሲ ስራቸውን ይሰራሉ። የመንግስቱ መኪና ባልተገለጸላቸውና አደገኛ በሆኑ ሰዎች የተሰገሰገ ነው። ስለሆነም በፖለቲካው መስክ ምንም ዐይነት ለውጥ አልተካሄደም። ወደ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ስንመጣም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አሁንም ቢሆን የወያኔ አገዛዝ ያራምድ የነበረውን የኒው-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ የሚያደርገው። የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነዳፊዎችም በዓለም ባንክ የተቀመጡና በእሱና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የሚታዘዙ ናቸው። የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚያስቀድሙና ኢኮኖሚውም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ተመስርቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርጉ ሳይሆን ዋና ዓላማቸው አገራችን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኦሊጋሪክ ስር እንድተወድቅና በኢንቬስትሜንት ስም እንድትቸበቸቭ ማድረግ ነው። ሞራላዊ ብቃትና ታሪካዊ ኃላፊነት የማይሰማችው ናቸው። የአገር ወዳድነትና የብሄራዊ ስሜት የሌላቸው ናቸው። ከዚህም በላይ የዎል ስትሪት ታዛዢዎችና የኧርንስት ያንግ ተጠሪዎች በአማካሪነት በመስራት የአገር ሀብት እንዲሸበሸብ እያደረጉ ናቸው። በመዋዕለ-ነዋይ ስም አገሪቱ ወደ ተራ ሸቀጣ-ሸቀጥነት እየተለወጠችና ህዝባችንም ብሄራዊ ነፃነቱ እየተገፈፈ ነው። የኢኮኖሚ ፖሊሲውን የሚያረቁና ከነፃ ገበያ ገበያ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም ብለው የሚነግሩን ሰዎች ካፒታሊዝም በምን ዐይነት ሎጂክና ህግ እንደተገነባ የሚያውቁ አይመስለኝም። በእነሱ ዐምነት አንድ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ነው በኢኮኖሚ ፖሊሲና በአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ያለውና ለዘለዓለምም የሚኖረው። ይኸውም ኒዎ-ሊበራሊዝም ነው።
ከአጠቃላዩ የአገራችን ሁኔታ ስንነሳ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ፣ በማህበራዊም ሆነ በአጠቃላይ የአገር ግንባታ አገራችን ለውጥ የሚካሄድባት አገር አይደለችም። ለለውጥና ለአገር ግንባታ መሰረታዊ የሆነው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ የሚተገበርባት አገር አይደለችም። ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በታጠቁና የመንግስትን መኪና በተቆናጠጡ ሰዎች በፍርሃት የሚኖርባትና ፍዳውን የሚያይባት አገር ሆናለች። የመንግስት መኪና ከተጨቋኝ ባህርይው እስካልተላቀቀና ህዝቡም በማንኛውም መስክ የመሳተፍና ሃሳቡን የመግለጽ፣ እንዲሁም የመጠይቅና የመተቸት፣ ሰላማዊ ሰልፍም የማድረግ መብት እስከሌለው ድረስ ስለ ብልጽግና ማውራት በፍጹም አይቻልም። ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በተገለለበት አገርና መንግስት የሚባለው ፍጡር ከአገር ጥቅም ይልቅ የውጭ ኃይሎችን ጥቅምና ፍላጎት በሚያስቀድምበት አገር ብልጽግና እያሉ መወትወት ትልቅ የታሪክ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል። አንዳንድ ጋዜጠኞች ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ግለሰቦችና የቴለቪዥን ጣቢያዎች የዛሬውን አገዛዝና በአገዛዙ ዙሪያ የተሰበሰቡትን የለውጥ ኃይሎች እያሉ መጥራታቸ ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል እንደሰሩ ያስቆጥራቸዋል። ስለሆነም በእናት ኢትዮጵያ ስም የምንለምናቸው ክሪቲካል የሆኑ መጽሀፎችን እንዲያነቡና አገሮች እንዴት እንደተገነቡና፣ ደሃ ወይም ኋላ-ቀሩ የሚባሉ አገሮች በምን ምክንያት ኋላ እንደቀሩ እንዲማሩ ነው። ችግር ካለባቸው የሊትሬቸር ዝርዝር ልናቀርብላቸው እንችላለን። ልናስተምራቸውም ዝግጁ ነን። ለመማርና ሀቁን ለማወቅ አንፈልግም የሚሉ ከሆነ ደግሞ የምንለምናቸው ዝምብላችሁ ተቀመጡ ነው። ሰውን አታሳስቱ እንላቸዋለን። ካለበለዚያ ገሀነመ-እሳት ትገባላችሁ እንላቸዋለን።
መደምደሚያ!
ዛሬ አገራችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለመውደቅ የቻለችው በዛሬው አገዛዝ የግንዛቤ እጦት ብቻ አይደለም። ለዛሬው ሁኔታ መፈጠር የተለያዩ ኃይሎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተሳትፈዋል። አፄ ኃይለስላሴ ባለማወቅ ተግባራዊ ያደረጉት የኢኮኖሚና የትምህርት ፖሊሲ ብሄራዊ ባህርይና በራሱና በህዝቡ ላይ የሚተማመን ዜጋ ብቅ እንዳይልና የታሪክን አደራ እንዳይሸከም አድርጎታል። በአፄው ዘመን የተካሄደው ፖለቲካ ፊዩዳላዊና የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ ቆልፎ የሚይዝ ነበር። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመስራት ዕድል ቢያገኝም ስልጣን ለመያዝና ፋሺሽታዊ አገዛዝን ለማስፈን በፈለጉ የግራና የቀኝ ኃይሎች ህልሙ ሊጨናገፍ ችሏል። ከዚህም በላይ በሲአይኤ የተመለመሉና፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሽከር ከመሆንና ታሪክን ከመስራት ይልቅ ለአሜሪካን አገልጋይ መሆንን የመረጡ ኃይሎች የአብዮቱ ፍሬ እንዲቀለበስ አድርገዋል። ከሲአይኤ በሚጎርፍላቸው ዕርዳታ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ጦርነት አውጀዋል። በአጠቃላይ ሲታይ አገራችን እንደዚህ ዐይነት ፈተና ውስጥ ልትወድቅ የቻለችው በውስጥ ኃሎች ነው። ህውሃትና ሻቢያ፣ ኦነግና ሌሎች የነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ ኢህአፓና ኢድህ… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ከዚያች ምስኪን አገር የተወለዱና አገሪቱን ፍዳዋን እንድታይ ለማድረግ የበቁ ናቸው። በተጨማሪም ዛሬ አገራችን እየፈራረሰች ነው ብለው የሚጮሁና ለአንድ ኢትዮጵያ እንታገላለን የሚሉ አንዳንድ ሻለቃዎችና ጄኔራሎች፣ እንዲሁም የደጃዝማች ልጆች የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጥፋት ተላላኪ በመሆን በህዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት አውጀው እንደነበርና ዛሬም የጥፋት ተልዕኮአቸውን እያሟሉ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዋና ዓላማቸውም ስልጣን ላይ ቁጥጥ በማለት የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማሟላት እንጂ አዲስና የጠነከረች፣ እንዲሁም ዲሞክራትክ ኢትዮጵያን ለመገንባት አይደለም።
የእነዚህ የውስጥ ኃይሎች ችግር ግልጽ ነው። ህልማቸው ስልጣኔና ማምጣት ሳይሆን ስልጣን መያዝ ብቻ ነው። የዚህ ዐይነቱ ጭፍን አስተሳሰብና የሴራ ሰለባ መሆን ዋናው ምክንያት የዕውቀት ማነስና ጭንቅላታቸው ባለመዳበሩ ነው። አዕምሮአቸው በሰብአዊነት መርሆ ላይ በተመሰረተ ዕውቀት ያልተገነባ በመሆኑ ሀቀኛውን ከአሳሳቹ የመለየት ኃይል የላቸውም። ድርጊታቸውንም ለመመርመርና ጥፋታቸውንም ለማረም የሚችሉ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሰለሳና አርባ ዓመት ያህል ታግለናል ቢሉም በሂደት ውስጥ ምንም የተማሩት ነገር የለም። መንፈሳዊ ተሃድሶንና ነፃነትን የተቀዳጁ አይደሉም። በ21ኛው ክፍለ-ዘመን እየኖሩ ለማድመጥና ለመማር የሚፈልጉ አይደሉም። የችኮነት ባህርይ የሚያጠቃቸው ናቸው። ራሳቸውን መመልከት የማይችሉና የታሪክን ሂደት ያልተገነዘቡ ናቸው። በፈጸሙት የታሪክ ወንጀል የሚዝናኑ ናቸው። ትላንትም ሆነ ዛሬ ድርጊታቸው በሙሉ ሳይንስንና ፍልስፍናን እንዲሁም ቲዎሪን የሚፃረር ነው። ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊ መመሪያ የላቸውም። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የአገራችን ሁኔታ በጣም አሳሳቢና ህዝባችንም ካለአንዳች መሪ ብቻውን የቀረ ነው። ስለሆነም ጥያቄያችን ከዚህ አሳሳቢ ሁኔታ እንዴት እንውጣ? የሚል ነው። መጮኽና ድረሱልኝ ማለት የሚያዋጡ የትግል ስትራቴጄዎች አይደሉም። አንድ ህዝብ ነፃ ሊወጣ የሚችለውና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊሆን የሚችለው በራሱ ጥረትና ኃይል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ኃይልን መሰብሰብና በጠራ ፍልስፍና ዙሪያ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል። በፉከራና በዛቻ አንድ አገር ነፃ ልትወጣ አትችልም። አንድ አገር ነፃ ሊወጣ የሚችለው በምሁራዊ ኃይልና በምሁራዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ብቻ ነው። የጠብመንጃ ትግል ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ስልጣኔ ነው። ኃይል ጨራሽና የአንድን አገር ሁኔታ የባሰውኑ ውስብስብ የሚያደርግ ነው። ስለሆነም መደረግ ያለበት ትግል ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሆን አለበት። በአገዛዙም ላይ ዕውነተኛ ጫና ማድረግ የምንችለው በዕውቀት ዙሪያ የተሰባሰብንና በጠራ ዕውቀት አማካይነት ትግልና ግፊት ስናደርግ ብቻ ነው። ይሁንና ግን በኢትዮጵያ ስም እዚህና እዚያ ባንዲራ አንግበው የሚታገሉና፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአማራው ላይ ጦርነት ተከፍቶበታል ብለው ድምጻቸውን የሚያሰሙ- ነገሩ ሀቅን ያዘለ ቢሆንም- አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ግንዛቤያቸው በጣም ደካማ ነው። እናካሂዳለን የሚሉት ትግል በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ፣ በፖለቲካ ሳይንስና በሶስዮሎጂ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ ትግል አይደለም። አስተሳሰባቸው ይበልጥ ፊዩዳላዊ እንጂ ከበርቴያዊ ወይንም የሊበራል አስተሳሰብን ያዘለና የተገለጸለት አይደለም። ስለሆነም ታሪክን የሚረዱት ቆሞ እንደሚቀር እንጂ ሂደታዊ እንደሆነና በሂደት ውስጥ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሊበላሹም ሆነ ሊታደሱ የሚችሉ ነገሮች እንደሚኖሩና የኃይል አሰላለፍ ለውጥም እንደሚካሄድ አይደለም። ስለሆነም ትግላቸው ንቃተ-ህሊናን የተላበሰና ለፖለቲካ ዲስኮርስና የአንድን ህብረተሰብ ችግር ተረድቶ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል አይደለም። ባጭሩ ትግላቸውና አገላለጻቸው ዘመናዊነት የሌለው ወይም ደግሞ ያልተገለጸለት ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ከዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ እስካልተላቀቅን ድረስ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ለመረዳትና መፍትሄም ለመፈለግ በጣም ያስቸግራል።
በሌላ ወገን ደግሞ በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ሊገነዘበው የሚገባው መሰረታዊ ነገር አለ። አንድን አገር በሽወዳና በተንኮል መምራት በፍጹም አይቻልም። ወደ ተፈለገው ግብም አያደርስም። በግልጽ እንደሚታየው የውጭ ጠላቶቻችን፣ ከግብጽ እስከሱዳን፣ ከሳውዲ አረቢያ እስከተቀሩት የአረብ አገሮችና አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ሌላ ዐይነት የሩዋንዳ ዐይነት ዕልቂት በአገራችን ምድር እንዲታይ ይፈልጋሉ። ከዚያም በኋላ አገራችንን እንደዩጎዝላቢያ ለመሰነጣጠቅና የተዳከሙና በቀላሉ ሊታዘዙ የሚችሉ ትናንሽ አገሮችን ማየት ይፈልጋሉ። አሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከጎናችን ይቆማሉ ማለት የዋህነትና የዓለምን የፖለቲካና የሚሊታሪ ኃይል አሰላለፍ አለማወቅ ነው። ስለሆነም አገዛዙ ስትራቴጂካሊ ማሰብ አለበት። ኃይልን የሚበታትንና አገር ወዳድ ኃይሎችን የሚያጠቃ ፖለቲካ ማካሄድ የለበትም። በዚህ ዐይነት ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የሚጠቃው። ስለሆነም ስትራቴጂካሊና አርቆ ማሰብ የፖለቲካ ዋናው ጥበብ መሆን አለባቸው።
መልካም ግንዛቤ!!