25 ነሐሴ 2020, 11:20 EAT

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በእስልምና ሊቃውንት ላይ ያነጣጠረ ያለው ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫ ትናንት፣ ሰኞ ነሐሴ 18/2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው “የሐይማኖት ሊቃውንት ዑለማና ኢማሞች በጠራራ ጸሐይ በተከበሩ የአምልኮ ቦታዎች ሳይቀር” ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው ብሏል።
ምክር ቤቱ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልጿል።
ከሃጫሉ ግድያ በኋላ የመስጂድ ኢማሞችና ታዋቂ ሰዎች በአርሲና በሃረር የተለያዩ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አመራር ቦርድ ዋና ፀኃፊ ሃጂ ከማል ሃሩን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት መግለጫውን ለመስጠት የቻለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርሲና ሐረርጌ የተለያዩ አካባቢዎች የመስጂድ ኢማሞች፣ ኡላማዎች እና በአካባቢው ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥቃት በተደጋጋሚ በመሰንዘሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ሃጂ ከማል መግለጫው የተሰጠው ሰዉን ማረጋጋት “የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ. . . እንዲሁም ጉዳዩ መስመሩን የሳተ እንዳይሆን፣ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ስጋት ስላለን ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ጉዳቱ በማን እንደደረሰ፣ መቼና ማን እንዳደረሰው የማጣራት ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ወደፊት ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥበት አስረድተዋል።
ሃጂ ከድር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን በመግለጽ የኃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ እንዲህ አይነት ጥቃትን በጋራ ማውገዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በኦሮሚያ የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የደረሱትም ጥቃቶችና ጉዳቶችም ቢሆኑ የሁሉንም ሃይማኖት ተከታዮች የጎዳ መሆኑን በመግለጽ ችግሩ የጋራ በመሆኑ የመገናኛ ብዙኀን ዘገባ ሚዛናዊነት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ግድያ ከተፈፀመባቸው ስፍራዎች አንዱ ወደ ሆነው ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ ሃሳሳ ወረዳ የልዑካን ቡድኑን ልኮ እንደነበር ቡድኑን የመሩት ሃጂ ኢብራሂም ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ሃጂ ኢብራሂም አክለውም በስፍራው አሳሳ ከተማ አንድ ኢማም ከባለቤታቸው እና ከልጃቸው ጋር በታጣቂዎች መገደላቸውን በቦታው ከነበሩ የዓይን እማኞች መስማታቸውን ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊው አቶ ጂብሪል ከቢቢሲ ስለጉዳዩ በተጠየቁበት ወቅት በኢማሙ ግድያ ላይ ሁለት ዓይነት መረጃ መኖሩን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጂብሪል የአካባቢው ማኅበረሰብ ኢማሙ በቤታቸው ሳሉ በመንግሥት ታጣቂዎች ተገደሉ ብሎ እንደተነገረ ገልፀው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ደግሞ ኢማሙ በሌላ የፀጥታ ባልደረባ ላይ በስለት ጥቃት በመፈፀማቸው ባልደረቦች በተከፈተ ተኩስ እርሳቸውና ቤተሰባቸው መሞታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ጉዳዩ ማጣራት ያስፈልገዋል ሲሉ አቶ ጂብሪል ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
- በኦሮሚያ እና ድሬዳዋ ባጋጠሙ ግጭቶች ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ
- በምዕራብ ሐረርጌ ጉባ ኮሪቻ በኮቪድ-19 የተያዘው ግለሰብ ማን ነው?
- እሷ ማናት?፡ ፈቲያ መሐመድ ከዐረብ ሃገር ኑሮ ወደ ሚሊየነርነት
ወደ ስፍራው በቡድን የሄዱት ጉዳዩን በአካል ተገኝቶ ለማጣራት ቤተሰቦቹን ለማጽናናት መሆኑን የሚናገሩት ሃጂ ኢብራሂም “ያየነውና የሰማነው ነገር ልብ የሚሰብር ነው፤ አሳዝኖናል” ብለዋል።
የተገደሉት ኢማም ሼህ ኡመር ይባላሉ ያሉት ሃጂ ኢብራሂም፣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ መገደላቸውን ገልፀዋል።
“የግቢያቸው አጥር ቆርቆሮ ነው፤ ቆርቆሮው ከ20 ስፍራ በላይ በጥይት ተበሳስቷል፤ በትክክል የቆጠሩ ሰዎች ደግሞ 28 መሆኑን ይናገራሉ” ይላሉ።
“ምን እንደተፈጠረ ለማጣራት ስንሞክር ታጣቂዎች እርሱንም ሚስቱንም ልጁንም እንደገደሉ ነግረውናል። የታጣቂዎችን ማንነት ግን ሊነግረን የሚችል ሰው አላገኘንም።”
ከዚያ እንደተመለሱ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተናል ያሉት ሃጂ ኢብራሂም፣ “ኮሚሽነሩ መረጃው አልነበራቸውም። ወዲያው የሚያጣራ ኮሚቴ አዋቅረው ጉዳዩን ማጣራት እንደጀመሩ ነግረውናል።”
በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች በመስጂዶችና የሐይማኖት አባቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የገለፁት ሃጂ ኢብራሂም፣ በሻሸመኔ አንድ መስጂድ ላይ በመስኮት በኩል ተተኩሶ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውንና የሕክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮፈሌ ደግሞ በመስጂድ ውስጥ በመግሪብ ሰላት ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ ተተኩሶ የነበረ ቢሆንም ምንም የተጎዳ ሰው አለመኖሩ ተገልጿል።
“ምዕራብ ሐረርጌ በዴሳ እንዲሁ ሌላ ኢማም መገደላቸውን ሰምተናል” ያሉት ሃጂ ኢብራሂም እነዚህን ሁሉ እያጣሩ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋርም ምክክር መጀመራቸውን በመግለጽ የደረሱበትን ወደፊት እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ በነበረው አለመረጋጋት ቢቢሲ ከሆስፒታል ምንጮች ብቻ ባገኘው መረጃ መሰረት 11 ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉ ተነግሯል።
በጉዳዩ ላይ መንግሥት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ግን የመንግሥት አካላት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆተቡ ማሳሰቡ ይታወሳል።