August 25, 2020

ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ በምርጫ ስም እየፈፀመ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ገብቶ ያስቁም ፤ ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ ይስጥ!

ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤

—-

የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፍ አደጋ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት የ2012 ዓ/ም ምርጫ እንዲተላለፍ በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል መወሰኑ የሚታወቅ ነው። መንግስት ከበርካታ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች በኋላ ያስተላለፈውን ይህን ውሳኔ ሁሉም አካል እንዲያከብረው ይጠበቃል። ይሁንና የፌደራል መንግስቱ ምርጫው እንዲተላለፍ ውሳኔ ባስተላለፈበት የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) ከፌደራል መንግስቱ ውሳኔ ፍፁም ባፈነገጠ መልኩና በእልህ ምርጫውን ለማካሄድ እየሰራ ይገኛል። በተለይ ከሦስት አስርት አመታት በላይ በቅኝ ግዛትና አፓርታይዳዊ ሥርዓት በሚመሰል አገዛዝ ስር የሚያሰቃየውና የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈፀመበት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ላይ በምርጫው ሰበብ በርካታ የመብት ጥሰቶች እየተፈፀሙበት ነው።

ለአብነት ያህል፡-

1) ብዙ ወጣቶች ምርጫውን ትቃወማላችሁ፣ የብልፅግና አባል ናችሁ ተብለው በዚህ የኮሮና ወቅት ለበሽታው በሚያጋልጥ መንገድ በስቃይ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። በሽዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ምርጫውን ትቃወማላችሁ፣ የብልፅግና ደጋፊዎች ናችሁ፣ እንዲሁም ቤተሰቦቻችሁ ምርጫውን ይቃወማሉ በሚል ስማቸው ቤት ለቤት እየተመዘገበ፣ በየቀኑ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ይገኛል።2) የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ምርጫውን ባለመደገፉ ምክንያት በትህነግ በግድ ከተያዘው ርስቱ፣ ከሚኖርበት አካባቢ “አማራ ይውጣ” የሚል ዘመቻ እየተደረገበት ይገኛል። ትህነግ በተለያዩ አካባቢዎች ያደረጋቸው ሰልፎች የአማራን ሕዝብ የሚዘልፉ፣ ከቀየው እንዲለቅ ዛቻ አዘል መልዕክት የተላለፈባቸው ናቸው:: እነዚህ መልዕክቶች ምርጫው እየቀረበ ሲመጣ በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ጭፍጨፋ መሰረት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።3) ምርጫውን ሰበብ በማድረግ የጦርነት ነጋሪነት እየጎሰመ ያለው ትህነግ ሕዝባችን በግድ ቀለብ እንዲሰፍር ከማስገደድ ባሻገር፣ ወጣቶችን የልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባል ሆነው እንዲመዘገቡ እያስገደደ ይገኛል። የልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባል መሆን ያልፈለጉትን የእስርና ወከባ ሰለባ ሲሆኑ ከወገናችን ጋር ጦርነት አናደርግም ያሉ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ታስረዋል፣ ተገድለዋል፣ መሳርያቸውን ተነጥቀዋል። ከዚህ ስጋት ለማምለጥ ወደ አማራ ክልል ኮብልለው የመጡ ከሰላሳ በላይ የሠራዊቱ አባላት እንዳሉም ይታወቃል።4) ወልቃይት ጠገዴ ላይ ምርጫውን በግዴታ ለማድረግ የቆረጠው ትህነግ የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ አማራዎች የገንዘብና የእስር ቅጣት እንዲጣልባቸው ለካድሬዎቹ ተልዕኮ ከሰጠ ሰንብቷል።5) የወልቃይት ጠገዴ አርሶ አደር ከመኖርያው ርቆ የሚያመርት መሆኑ ይታወቃል። ከፌደራል መንግስቱ ውሳኔ ውጭ በዚህ የምርት ወቅት ምርጫ አደርጋለሁ እያለ የሚገኘው ትህነግ፤ ሰብሉን እየተንከባከበ የሚገኘው አርሶ አደር ለምርጫ ለመመዝገብና ለመምረጥ በተደጋጋሚ ከርቀት ሰብሉን ጥሎ እንዲመጣ በማድረግ የፌደራል መንግስት የኮሮና ቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖን ለመቀነስ “አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም” ባለበት ወቅት ገበሬውን ለማክሰር እየሰራ ይገኛል።ትህነግ የፌደራል መንግስቱ አባል የሆነውን የትግራይ ክልል አስተዳደራለሁ እያለ ለማዕከላዊ መንግስቱ ሕግ፣ አሰራርና ውሳኔ አልገዛም ከማለቱ ባሻገር የፌደራል መንግስቱም እስካሁን በሚጠበቅበት ልክ ሕግና ስርዓት ማስከበር አልቻለም። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ግብር በመክፈል፣ ዳር ድንበሩን በመጠበቅና ሌሎች ሀገሪቱ የምትጠብቅበትን ግዴታውን እየተወጣ ሲሆን፤ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በትህነግ የሚፈፀምበትን በደል ግን የሀገረ-መንግሥቱንና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ ያለበት የፌደራል መንግስት በአደጋው መጠን ልክ ትኩረት አልሰጠውም::ትህነግ ከቅኝ ግዛት በባሰ ጭቆና ውስጥ ይዞት የቆየው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በራሱና በሌሎች ወንድም ሕዝቦች የጋራ ትግል የአመራር ለውጥ ሲመጣ፣ ትህነግ ከመሀል አገር ፖለቲካ ተነቅሎ ወደ ዳር ሲሸሽ በአገዛዙ የተነጠኳቸው ሰብአዊ መብቶቼ ይከበሩልኛል፣ የተቀማሁትን የአማራ ማንነቴን አስመልሳለሁ በሚል ከለውጡ ኃይል ጋር ቆሟል። ይሁንና ‘የብልፅግና አባል ናችሁ ‘፣ ‘ብልጽግናን ትደግፋላችሁ’፣… እየተባለ ለግድያ፣ ለአሰቃቂ እስር፣ ለስደትና ስቃይ ከመዳረግ ውጭ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝባችን ማህበራዊ እረፍት ማግኘት አልቻለም:: ዛሬም እንደትላንቱ ማንነቱን ተነጥቆ፣ ፖለቲካዊ ነጻነቱን አጥቶ በግፍ ቀንበር ስር ይገኛል፡፡አሁን ትህነግ አደርገዋለሁ የሚለው የሕዝበ ውሳኔ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ምርጫ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ ከአማራ ወገኑ እና ከኢትዮጵያ ሀገሩ የማቆራረጥ ፖለቲካዊ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ሕዝባችን በምርጫ ሰበብ እየተጎሰመ ያለውን የጦርነት ነጋሪት አልቀበልም በማለት በመቃወሙ በርካታ በደል እየደረሰበት ይገኛል።የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በግዳጅ ከተካለለበት የትግራይ ክልል ይልቅ የፌደራል መንግስቱን ሕግና ስርዓት በማክበር ትህነግን እየታገለ ቢገኝም የፌደራል መንግስቱ የሚገባውን ያህል እገዛ አላደረገለትም። በተለይም የፌደራል መንግስቱ እንዲተላለፍ የወሰነውን ምርጫ ትህነግ አደርጋለሁ ሲል ሕዝባችን የፌደራል መንግስትን ሕግና ስርዓት አክብሮ ተቃውሞውን አቅርቧል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ምርጫውን በመቃወሙ ከትህነግ እየደረሰበት ያለውን ድርብ ጭቆና ግን የፌደራል መንግስቱ እያስቆመ አይደለም። የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት፣ የሐገረ-መንግሥቱን ህልውና የሚፈታተኑ፣ ሕግና ስርዓት የማያከበሩ ኀይሎች ላይ የፌደራል መንግስቱ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት።የፌዴሬሽን ምከር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀፅ 3(8) ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ማንኛውም ክልል ፌደራል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል” በማለት የተቀመጠው ሥልጣን አሁን ተግባራዊ ካልሆነ መቸ ሊሆን ይችላል? ወልቃይት ጠገዴ ላይ እየተፈፀመ ካለው ማንነትን መሰረት ያደረገ የመብት ጥሰት በላይ ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ ጉዳይ የለም::

ስለሆነም፡-

1ኛ) የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የሕገ-መንሥት ትርጉም በሚጻረር መልኩ ሕገ-ወጥ ምርጫ ለማካሄድ ከቀድሞው የቀጠለውን በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን በደልና ጭቆና፤ ማንነትን መሰረት ያደረገ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም፤

2ኛ) ሕገ-ወጡን ምርጫ በማካሄድ ሰበብ ማንነታችን መሰረት አድርጎ እየተፈፀመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም እንዲቻል ፣የፌደራል መንግስቱ የፀጥታ ኃይሉን ወደ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ እንዲያስገባ እና የጠየቅነው የማንነት ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ አካባቢው በፌደራል ፀጥታ ኃይል ስር እንዲቆይ እንዲያደርግ፤

3ኛ) ሕገ-ወጡን ምርጫ ሰበብ በማድረግ በትህነግ የተከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ሸሽተው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ የወልቃይት ጠገዴ ተፈናቃይ አማሮችን፣ የትህነግ የሽብር ፖለቲካ አገር ያፈርሳል በሚል ጽኑ እምነት ከፀጥታ ኃይሉ ኮብለለው ወደ አማራ ክልል እየገቡ ያሉ የልዩ ኃይሉና የሚሊሻ አባላትን፣… አያያዝ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ረገድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እያደረገ ያለውን ድጋፍ እያደነቅን፣ በቀጣይም ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመነጋገር በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ለማስቆም፣ ሕገ-መንግሥታዊ የሆነው የማንነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ፣… አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ፤

4) የአማራ ሕዝብ፣ የአማራም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኀይሎች፣ የአማራ ወዳጅ የሆናችሁ መላ ኢትዮጵያውያንና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣

… በወልቃይት ጠገዴ አማራ ላይ ከትላንት የተሻገረው የማንነት ጥቃት ሕገወጡን ምርጫ ሰበብ በማድረግ አድማሱን አስፍቶ የቀጠለ በመሆኑ ትግላችን በመኖር እና ባለመኖር መካከል ብርቱ ፈተና ላይ የወደቀ መሆኑን ተገንዝባችሁ ወገናዊና ሰብአዊ አጋርነታችሁን እንድታሳዩን፣ የትግላችን ደጀን ሆናችሁ ድምጽ እንድትሆኑን፤5) የተለያዩ ሚዲያዎች በቅርብ ጊዜ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ድምፅ ለማሰማት ያሳዩትን ተነሳሽነት በእጅጉ እያደነቅን፣ ሆኖም ትህነግ/ሕወሓት እስካሁን ሲፈፅመው ከኖረው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ባሻገር ሕገወጡን ምርጫ ተከትሎ እየፈፀመ ያለው ከፍተኛ በደል የሚዲያዎችን ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ሚዲያዎች የትህነግ/ሕወሓትን ሀገር አፍራሽ እና ሕገወጥ ተግባር በማጋለጥ ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጎን እንድትቆሙ፤

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል::

—-

የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራ ማንነት በልጆቹ ትግል ይረጋገጣል!ድልና ነጻነት ለወልቃይት ጠገዴ አማራ!