የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው ሁከት ምክንያት ተጎድተዋል ወደ ተባሉ አካባቢዎች ተሰማርታ ምልከታ ካካሄደች በኋላ በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መግለጫ በመስጠት ላይ ትገኛለች። መግለጫውን ከታች ያገኙታል።

ቤተ ክርስቲያኗ በዚህ ጊዜ እንዳለችው ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ፣ በሐረሪ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር በተፈጠረ ሁከት 67 ምዕመናን ሲገደሉ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በአጠቀላይም ሁከቱን መነሻ በማድረግ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምዕመናን ንብረት መውደሙም በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል፣በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር እና በሌሎች አካባቢዎች ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ እንደ ሰውም አስክሬናቸው በክብር አልተቀበረም ፣ ሴቶች በባለቤታቸው፣በወንድምና በአባታቸው ፊት መደፈራቸው በምልከታ መረጋገጡ በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

ጥቃቱ ሆን ተብሎ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮችን በመለየት የተፈጸመ እንደነበር ያስታወቀችው ቤተ ክርስቲያኗ መንግስት ሕግን እንዲያስከብርም ጠይቃለች።