
DW : የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አመራር ቦርድ እና የዑለማዎች ምክር ቤት ባለስልጣናት ዉዝግብ ገጥመዋል።
–
የምክር ቤቱ ቦርድ ትናንት ባወጣዉ መግለጫ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች በኦሮሚያ መስተዳድር በተለያዩ መሳጂዶች ላይ አድርሰዉታል ያለዉን ጥቃት፣በየኢማሞችና ምዕመናን ላይ ተፈፅሟል ያለዉን ግድያም አዉግዞ ነበር።
–
መንግስት የሕዝቡን ደሕንነት እና ሠላም የማስከበር፣ የኃይማኖት ተቋማትን የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም መግለጫዉ ጠይቆ ነበር።የዑለማዎች ምክር ቤት ግን መግለጫዉን ጠቅላይ ምክር ቤቱ «ሳያዉቀዉ፣ ሳይነጋገርበትና በችኮላ» የወጣ በማለት ነቅፎታል። ቦርዱንም «ከኃላፊነቱ ዉጪ» እየተንቀሳቀሰ ነዉ በማለት ተቃዉሞታል።
–
የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች፣ የታሰሩ መሪዎቻቸዉን ለማስፈታት፣ ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ በኦሮሚያ መስተዳድር አድማና ተቃዉሞ እንዲደረግ ያሰራጩትን ጥሪ ደግፈዉ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ዞኖች አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል እርምጃ መዉሰዳቸዉን የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።
–
ሮይተር ዜና አገልግሎት ባለፈዉ ሐሙስ የሐረር ሁለት ሆስፒታሎች ሐኪሞችንና የጭሮ የጤና ኃላፊን ጠቅሶ ቢያንስ 9ኝ ሰዎች በጥይት ተደብድበዉ መገደላቸዉን እና ከ50 በላይ መቁሰላቸዉን ዘግቧል።የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም ፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚዎች ላይ ከመጠን ያለፈ እርምጃ መዉሰዳቸዉን አስታዉቆ ነበር።የኦሮሚያ መስተዳድር ባለስልጣናት ዘገባዉን አልተቀበሉትም።ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በበኩላቸዉ አርሲ ዞን አሰሳ ከተማና ምዕራብ ሐረርጌ በዴሳ ከተማ ቢያንስ ሁለት ኢማሞች መገደላቸዉን እየዘገቡ ነዉ።