ከ 5 ሰአት በፊት

ከሰሞኑ አፍሮ ባሮ ሜትር የተባለ ተቋም ኢትዮጵያውያን ስለ ሕገ መንግሥቱ ምን አስተያየት እንዳላቸው የሚጠቁም የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።
የአፍሮ ባሮ ሜትር ስምንተኛ ዙር ጥናት ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል፣ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችም በፌዴራል የሥራ ቋንቋነት እንዲካተቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን እንዲገደብ በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚስማሙ ይጠቁማል።
ሕገ መንግስቱ አሁን ባለው ይቀጥል ወይስ ይሻሻል በሚለው ላይ ከጥናቱ ተሳታፊዎች 68 በመቶዎቹ መሻሻል አለበት ያሉ ሲሆን፤ 18 በመቶዎቹ ባለበት ቢቀጥል፤ 11 በመቶ ደግሞ በአዲስ መተካት አለበት ማለታቸውን ጥናቱ አመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ዘመን በሁለት የምርጫ ጊዜ መገደብን በተመለከተ፤ 68 በመቶዎቹ ሲደግፉ፣ 23 በመቶዎቹ ተቃውመው፤ 9 በመቶዎቹ ደግሞ ድምጽ አልሰጡበትም።
ገለልተኛ የሆነ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ማቋቋም በሚለው ላይ 55 በመቶ ሐሳቡን የደገፉ ሲሆን፤ 25 በመቶ ተቃውመውታል፤ 21 በመቶ ደግሞ ሐሳብ አልሰጡበትም።
አንቀጽ 39 የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ማስወገድ፣ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መሀል ላይ ያለውን አርማ ማስወገድ እንዲሁም አዲስ አበባን በፌዴሬሽን አባልነት ማካተት የሚለውን በአብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች የተቃወሙት ሲሆን፤ ጥቂቶች ደግፈውታል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ፌዴራሊዝምን በተመለከተ ስምምነት ቢኖራቸውም ብሔርን መሠረት ያድርግ ወይስ የመልከዓ ምድር አቀማመጥን የሚለው ላይ ልዩነት እንዳላቸው ጥናቱ አሳይቷል።
የጥናቱን ውጤት በተመለከተ፤ ናሙናው ምን ያህል ወካይ ነው? የጥናቱ ውጤት ለምን በዚህ ወቅት ይፋ ተደረገ? የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን ለድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ሙሉ ተካ አቅርበናል።
ናሙናው ወካይ ነው?
አቶ ሙሉ እንደሚሉት የጥናቱ አላማ የሕዝቡን አስተያየት ማንጸባረቅ ነው።
ሕገ መንግሥቱን እንዲሁም የፌደራሊዝም ሥርዓቱን በተመለከተ የፖለቲከኞች እና የምሁራን ሐሳብ በመገናኛ ብዙኃን እንደሚገለጽ በመጥቀስ፤ ተቋሙ የሰራው ጥናት ደግሞ የሕዝቡ እይታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጥናቱ ውጤት ለሕዝቡ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላትም እንደሚሰጥም ያክላሉ።
“በጉዳዮ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ስምምነት የለም። ስለዚህ ሕዝቡ መካከልም ስምምነት የለም ተብሎ ይታሰባል። ግን ጥናት ያስፈልጋል። ስለዚህ ነው ጥናቱን የሠራነው።”
ከታህሳስ እስከ ጥር በተካሄደው ጥናት 2400 ሰዎች መካፈላቸው ተገልጿል። ለመሆኑ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ይህ ናሙና ምን ያህል ወካይ ነው? ስንል ጠይቀናል።
“የወሰድነው ናሙና ሳይንሳዊ ነው” ያሉት፤ በጥናቶች ናሙና ሲወሰድ ስህተት (ሳምፕሊንግ ኤረር) እንደሚኖር ያስረዳሉ።
በሺዎችም ይሁን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ናሙና ሲወሰድ፤ ሁሌም ስህተት እንደሚኖር ጠቅሰው፤ ጥናት ሲካሄድ የሚነሳው ዋናው ጥያቄ ስህተቱ ምን ያህል ይሁን ነው? የሚለው እንደሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ።
“አፍሮ ባሮ ሜትር በመሠረታዊ ሐሳቡ 95 በመቶ ተቀራራቢ የሚሰጥ አማካይ ነው የሚወስደው። ስህተት (ማሪጅን ኦፍ ኢረር) 2 በመቶ ብለን አስቀምጠናል” ይላሉ።
ከ2400 በላይ የናሙና ቁጥር ሲጨምር ስህተቱ የሚቀነስበት መቶኛ ከግምት መግባት እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
ውጤቱ ከአጠቃላይ የሕዝቡ ቁጥር መቶኛ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ “ውጤቱ ወካይ ነው” ይላሉ።
- የትግራይ ምርጫ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይጥላል?
- ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ ካዘዘ ፖሊስ አልለቅም ማለት ይችላል?
- ልዩ ኃይል፡ የአገር አንድነት ስጋት ወይስ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና?
ናሙናው ከየት ተወሰደ?
ናሙናው የተወሰደው በኤሌክትሮኒክ መረጃ መሰብሰቢያ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአገሪቱ ያሉት ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች ያላቸው የሕዝብ ቁጥር ከግምት ገብቶ ናሙና መወሰዱንም ያስረዳሉ።
ከናሙናው 50 በመቶው ወንዶች ከፊሉ 50 በመቶ ደግሞ ሴቶች እንደተካተቱም አክለዋል።
ለምን አሁን?
ጥናቱ ምርጫ እንዲራዘም ከተወሰነ በኋላ ለምን ይፋ ተደረገ? የሚልና በተቋሙ ገለልተኛነት ላይም ጥያቄ ያነሱ አሉ።
በተለይም ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ካለበት መቼ ይሁን? በሚል ጥናቱ ያነሳውን ጥያቄ በተመለከተ አቶ ሙሉ “ኮሮናቫይረስ ሊመጣ እንደሚችል አላሰብንም። ኮሮናቫይረስ ከመጣ በኋላ ቢሆን ሌላ ጥያቄ ይሆን ነበር። ስለዚህ ከመንግሥት የስልጣን ዘመን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አፍሮ ባሮ ሜትር የተቋቋመው እአአ 1999 ላይ ነው።
በዴሞክራሲ፣ በአስተዳደር፣ በምጣኔ ሀብትና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አስተያየት ይሰበስባል።
ውጤቱንም ለፖሊሲ ቀራጮች፣ ለምክር ቤት፣ ለእርዳታ ሰጪዎች፣ ለሲቪል ማኅበሮች እና ለሌሎችም የሚመለከታቸው አካሎች ይሰጣል።
“የኛ ትኩረት ውጤቱ ሳይሆን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት መስጠት ነው” ይላሉ አቶ ሙሉ።