August 27, 2020
ልማት ወይንስ ውድመት?
—ድህነትን ለማጥፋት ከተፈለገ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፤ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ዜግነት መቀበል ወሳኝ ነው–
አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም፤ እርጋታ፤ ፍትሃዊ፤ ተከታታይ፤ አስተማማኝ ልማት፤ በአገር ውስጥ ህይዎትን የሚቀይር የስራና የገቢ እድል ካልሰፈነባቸው አገሮች መካከል አንዷ ናት። በዚህ ምክንያት ነው፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ዘውግ፤ ኃይማኖት፤ ጾታና ሌላ መስፈርት ሳይለያቸው፤ በተለይ ባማካይ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑት በገፍ አገራቸውን እየለቀቁ የስራና የገቢ እድል በመፈለግ፤ በተለይ ወደ አረቡ ዓለም የሚሄዱት። ሰላም፤ እርጋታ፤ ደህንነት ለልማት ወሳኝ ነው። ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚገመተው “የቀን ሰራተኛ (Migrant Worker) የተጓዘው ወደ ሌባኖን፤ ሳውዲ አረብያ፤ የገለፍ አገሮችና መሸጋገሪያ (Transit Corridor) ወደ ሆነችው ወደ የመን ነው።
ይህ ሰው ሰራሽ የመጥፎ አገዛዝና የአስተዳደር ተግዳሮት ያስከተላቸው ተከታታይ ቀውሶችና ግፎች ብዙ መጻህፍት ተጽፎባቸዋል። ትኩረቴ መፍትሄው ምን ይሁን በሚለው ላይ ነው። ችግሩን የፈጠርነው ራሳችን ኢትጵያዊያን ነን። ይመስለናል እንጂ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በማምከን ዙሪያ፤ በያንዳችን ቤት ያልተሰማ ጉድ አለ። በተለይ የፖለቲካ ምሁራንና ልሂቃን በኪሳቸው ደብቀው የያዙት “ዘውድ” ማህበረሰባዊው ገጽታው ራስን ማገልገል እንጂ ህብረተሰቤን ካለበት ችግር እንዴት አድርጌ ላውጣው የሚል መርህ አይደለም።
አንድ ብልሃዊ አባባል አለ። “ሰው የዘራውን ያጭዳል” የሚል። የዘውግ ወይንም የኃይማኖት ጥላቻን የሚሰብክ ግለሰብ ወይንም ቡድን “ግፋበት፤ አይዞህ” ሲል ኢላማ ያደረገውን ግለሰብ፤ ቤተሰብና ማህበረሰብ በለው ማለቱ ነው። ኢላማ የሆነው ግለሰብ፤ ቤተሰብ ወይንም ዘውግ ህይወቱ ብቻ ሳይሆን፤ ኃብትና ንብረቱም ኢላማ ይሆናል። አረመኔነት፤ ሽብርተኛነት፤ ጽንፈኛነትና “ኬኛነት” በግለሰብና በቡድን አማካይነት በተደጋጋሚ ሲሰራጭ ወደ እልቂትና ወደ ኢኮኖሚ ውድመት ያመራል። ስለሆነም የተዘራው ጥላቻ እልቂትንና የኢኮኖሚ ውድመትን እያስከተለ ለልማት ጸር ይሆናል። ፈሰስ የሆነውን መዋእለንዋይ (Investment infrastructure) መልሶ ለመተካት ብዙ ዓመታት ይወስዳል። የተፈጠረው የስራና የገቢ እድል ይማክንና የአካባቢው ወጣት ይሰደዳል። ቢወድም ቢጠላም “ሰው የዘራውን አጭዶ” የራሱን ሕዝብም ጭምር ጎዳው ማለት ነው። በተለይ የሚጎዳው ወጣቱ ትውልድ ነው።
“የዘራነው” የዘውግና የኃይማኖት ጥላቻ አጥፊነትና አገር አፍራሽነት በምንም ደረጃ አያከራክርም። እኔ የምከራከረው ግን፤ ችግሩን ራሳችን ከፈጠርነው መፍትሄውንም መፈለግ ያለብን ራሳችን ነን። ፈረንጆች እኛን ከመገምገም ውጭ መፍትሄውን ሊያመጡልን አይችሉም። ለምሳሌ፤ የእንግሊዝ መንግሥት ፖሊሶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ሲወረርና” የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኦሮሞ ሲተካ ቆመው አይተዋል። በሲይትል፤ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገ አንድ ወጣት ፈረንጅ በጃዋር፤ ጽንፈኛ ቄሮዎች ሲደበደብ አይተዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ሂውማን ራይትስ ወች፤ አል ጃዚራና ሌሎች በሻሸመኔ፤ በሃረር፤ በድሪዳዋ፤ በባሌና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመውን ግፍ፤ በደል፤ የዘውግና የኃይማኖት መለያ ያደረገ እልቂትና የኃብት ውድመት ሚዛናዊ በሆነ ደረጃ ከመገምገም ተቆጥበው በአጥፊዎቹ ላይ የሚካሄደውን እርምጃ ሲኮንኑ ይታያል። ለይቶ መኮነን የሚያሳየው ምንድን ነው? ብለን የምንጠይቅበት ሁኔታ ይታያል።
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ተግዳሮቶች መፍትሄ መፈለግ ያለብን ራሳችን ነን። ይህን ለማድረግ የምንችለው ግን፤ አንድ ሁሉን አቀፍ፤ ሁሉን ባለድርሻዎች የሚያሳትፍና የሚያገልግል ኢትዮጵያዊ፤ ዲሞክራሳዊና ፍትሃዊ ራእይ፤ አቅጣጫ ተልእኮ ሲኖረን ብቻ ነው። አክራሪነት፤ ጠባብ ብሄርተኛነት፤ ጽንፈኛነት፤ “ኬኛነት፤ “የኔ ተራ ነው” ባይነት፤ ለውጭ አገር ኃይሎች አጎባዳጅነት፤ ሌብነት፤ ሙሰኛነት ወዘተ ከላይ ካለው መርህ ጋር አይጣጣሙም። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አይመጥኑም። የማይመጥን ራእይና ፕሮግራም ይዞ ኢትዮጵያና መላውን ሕዝቧን የሚመጥን ሕዝብን ያማከለ የልማት ፈር ለመቅደድ አይቻልም።
ነፍሳቸውን ይማርና ከእልፈታቸው በፊት ዶር ነጋሶ ጊዳዳ “ሕገ መንግሥቱና የክልሉ አስተዳደር” እትዮጵያን ሊሸከሙ አይችሉም፤ ለኢትዮጵያ ተመጣጣኝ አይደሉም፤ መለወጥ አለባቸው የሚል መንፈስ የያዘ መልእክት ተናግረው ነበር። ለምን ሰሚ አጡ? የሚለውን ጥያቄ ለባለድርሻዎች ሁሉ አቀርባለሁ፤ በተለይ ለፖለቲካ ስብስቦችና ልሂቃን።
የወደፊቱን የሚያመለክት ብሄራዊ መግባባት ወሳኝ ነው።
በቅርቡ አገር ቤት የሚገኙት “ተፎካካሪ” ተብለው የሚጠሩት ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ ሰለ ብሄራዊ መግባባት ባደረጉት አስፈላጊና ወቅታዊ ውይይት የታዘብኩትን ባጭሩ ለመገምገም እፈልጋለሁ። የዛሬ ሶስት ዓመት፤ በዳላስና በሲያትል በተደረጉ ብዙ የማህበረሰብና የፖለቲካ ድርጅቶችን ባሳተፉ ሁሉን አቀፍ ጉባኤዎች ጥልቀትና ጥራት ያላቸው ውይይቶች ተደርገው ነበር። ፍኖተ ካርታም ተቀርጾና ጸድቆ ነበር። ይህ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ምክንያቱ ይገባኛል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ተሹመው “ሽግግሩን ለኔ ተውት፤ እኔ አሸጋግራችኋለሁ” ካሉ በኋላ ወደ አገር ቤት የገባው የዱሮው ተቃዋሚና አክቲቪስት አና ውጭ ያለውም ለውጡን “እልል” ብሎ የተቀበለው የፖለቲካና የማህበረሰባዊ ድርጅቶች አባል፤ ምሁርና ሌላ አዲስ ዘመን መጣ በሚል ፍላጎትና ምኞት ሁሉን ነገር ችላ ብሎት ቆየ። ወደ አገር ቤት በገፍ የገቡት ኃይሎች ከመሰብሰብና ከአድር ባይነት ውጭ ወሳኝና መሰረታዊ ለውጦችን ስኬት ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን አላስተጋቡም።
ለምስሌ፤ ዘውግ ተኮሩ ህገመንግሥትና የክልሉ አሥተዳደር የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች እንዳባባሷቸው በመሬት ላይ የሚታዩ ብዙ ክስተቶች ቢኖሩም፤ ለአገሪቱና ለ 115 ሚሊየን ሕዝቧ ፍላጎት፤ አብሮነት፤ ልማት፤ ተስፋና ምኞት ተመጣጣኝ የሆነ አማራጭ ለማቅረብ አልደፈሩም። ለምን? ማንን እየጠበቁ?
እንዲያውም ይህን መሰረታዊ ችግርና ብሄራዊ ግዴታ ችላ ብለውት ቆይተዋል። ስንት ሰው እስከሚሞት?
ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂትና ፍልሰት ዛሬ አልተጀመረም። በወልቃይት ጠገዴ- ጠለምት፤ በራያና አዜቦ፤ በጋምቤላ፤ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ በጉራ ፈርዳ፤ በኦሮምያ፤ በሶማሌ ክልል፤ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በተከታታይ እልቂትና የኃብት ውድመት ሲካሄድ ይህን ሁኔታ ማን ፈጠረው፤ ለምን ተፈጠረ፤ ማንን ይጠቅማል፤ ማንን ይጎዳል፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት አደገኛ ነው፤ አማራጭ ባሰቸኳይ እንጠቁም፤ ብሄራዊ ውይይት ይካሄድ? ወዘተ ብሎ የጠየቀና አማራጭ ያቀረበ የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም የማህበረሰብ ድርጅት አለ ለማለት አያስደፍርም።
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ወሳኝነት
ከሌሎች አገሮች አመሰራረት ታሪክ ልንማር አለመቻላችን ያሳፍራል፤ ያሳዝናል። አገርን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ለመለየት አለመቻል ድንቁርና ነው። የምኖርበት አሜሪካ፤ የጃዋር ደጋፊዎች “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ብለው በሚጮሁበት፤ አንድም ተቃዋሚ ግለሰብ አሜሪካን “ዳውን ዳውን” ሲል ሰምቸ አላውቅም። ቢል ዜግነቱን ሊቀማ ይችላል። “ዳውን ዳውን አሜሪካ” አይታሰብም። ሌላው ቀርቶ የእርስ በእርስ እልቂት ተጠቂ በሆኑት በሶርያ፤ በሊቢያ፤ በየመን፤ በአፍጋኒስታን፤ በየመንና ሌሎች አገሮች አገርን “ዳውን ዳውን” የሚል ጭኸት አልሰማሁም። ጽንፈኞች ኢትዮጵያን “ዳውን ዳውን” ሲሉ በምትኳ ማንን ከፍ ሊያደርጉ ነው? ማን የምትባል አገር ሊመሰርቱ ነው? ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መልስ እፈልጋለሁ።
ብሄራዊ መግባባት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ያለፈውን ታሪክ፤ “ግፍና በደል” በማጋነን ሊሆን አይችልም። አሜሪካ ነዋሪዎቹን ህንዶች በሚል መለያ የሚጠሩትን በገፍ ጨፍጭፋለች፤ ጥቁሮችን በባርነት ተጠቅማለች፤ እስካሁን መብታቸውን ስኬታማ ለማድረግ አልቻለችም። ሌሎችንም አገሮች ለመጥቀስ ይቻላል። በእልቂትና በጦርነት ያልተበከለ አገር ፈልግ ለማግኘት ያዳግታል። ትኩረቱ ከወደፊቱ ላይ እንጅ ወደ ኋላ እየሄዱ የፈጠራ መረጃ ማቅረብ ለማን ሊጠቅም ይችላል። የግራኝን ታሪክ አንስተን ማን ሃላፊነቱን ይውሰድ ብንል ፋይዳው ምንድን ነው?
ሌላው እጅግ የሚያሳስበኝ፤ የግብጽና የሌሎች መርሰናሪዎች (የጥቅም ነጋዴዎች) (Mercenary) እየበዙ መሄዳቸው ነው። ተፎካካሪ ነን የሚሉ ኃይሎች ከወንበርና ከመዋእለ ንዋይ ሽሚያው ውጭ የማሰብ ግዴታ አለባቸው። ምክንያቱም እነሱ ተጠቃሚ ቢሆኑም፤ እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ ግን በድህነት፤ በስራ አጥነት፤ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ መሆኑን ሊረሱት አይገባም።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ምን ያስፈልጋቸዋል?
አገራችን ድሃና ኋላ ቀር ናት። ይህ ሊቀረፍ የሚችል ክስተት ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ድህነትን ቀርፎ ፍትሃዊና ዘላቂነት ያለው ልማትን የሚያስተጋባ ስርዓትና አገዛዝ ነው። የአሁኑ ዘውግ ተኮር ህገመንግሥትና የክልል አስተዳደር ይኼን ስኬታማ ለማድረግ አያስችልም። ሕገ መንግሥቱ፤ የክልሉ አወቃቀርና በየደረጃው ያሉት መሪዎች ካልተቀየሩ በስተቀር፤ እልቂት፤ መፍለስ፤ ድህነት፤ ስደት፤ ሙስና፤ ተረኛነት፤ ስግብግብነትና ሌሎች ሁከቶች አያቆሙም። የውጭ ጠላቶች እነዚህን ክፍተቶች እየተጠቀሙ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያደርጉት ጥረት ፈር ይይዛል የሚል ግምት አለኝ።
አንዱና ወሳኙ ትኩረት ከፖለቲካ ሥልጣን ከስግብግብነት ይልቅ፤ የስራ እድልን በገፍና በፍጥነት ለወጣቱ ትውልድ በመፍጠር ላይ እንዲሆን አሳስባለሁ።
ብንወድም ባንወድም ያለው ሃቅ እንደሚከተለው ነው። ከዘውግና ከኃይማኖት ባሻገር፤ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በገፍ ሲሰደ ቆይቷል። ለምን ይሰደዳል? ስደት የኢትዮጵያዊያን መለያ ነው ወይንስ አዲስ ክስተት?
አገርን ለቆ መሄድ ወይንም መሰደድ ከጥንት ጀምሮ የተለመደ ጉዳይ ነው። ይህ ሁኔታ ግን እየተስፋፋ የሄደው በሃያኛውና በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ነው። የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና የማህበረስባዊ ጉዳዮች መስሪያ ቤት ባደረገው ሰፊ ጥናት መሰረት፤ በ 2017 መጨረሻ፤ ከአለም በሰራተኛነት የተሰደደው ሕዝብ መጠን 258 ሚሊየን ነው። ከእነዚህ መካከል ከአፍሪካ የተሰደደው መጠን 25 ሚሊየን ነበር;፡ የአብዛኛው ስደተኛ መናኸሪያ አገር አሜሪካ ናት ይባላል፤ አምሳ ሚሊየን የሚገመተው። በገፍ የሚሰደደው ደግሞ ከኤዥያ ነው፤ ለምሳሌ ህንዶች።
በዘልማድ የሚነገረው ስራ ፈላጊዎችና ሌሎች አገር ለቀው የሚሄዱ ግለሰቦች የሚያመሩት ወደ በለጸጉ አገሮች ነው ይላል። ትክክል አይደለም። አምሳ ሶስት በመቶ የሚገመተው አፍሪካዊ የሚሄደው ቅርብ ወደ ሆኑ አገሮች ነው፤ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሰሜን ሱዳን፤ ሜክሲካኖች ወደ አሜሪካ ወዘተ።
በእድሜ ሲገመገም ያለው ገጽታ እንደሚከተለው ነው። የእድሜው አማካይ 39 አመት ሲሆን፤ ሴቶች ከግማሽ ወይንም ከአምሳ በመቶ በታች የሚሆነውን አሃዝ ይዘዋል። “Younger persons, below age 20, tend to be underrepresented amongst international migrants: globally, 14 per cent of all migrants were under the age of 20 years, compared to a proportion of 34 per cent of the total population.” ህጻናት እንደ ስደተኛ አይቆጠሩም።
እነዚህ አገራቸውን ለቀው የሚሰደዱት ግለሰቦች ምን ፋይዳ አላቸው?
- ከሚያገኙት ገቢና ወደ አገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ለዘመድ አዝማድ መደጎሚያ መሆኑ፤ ድህነትን መቅረፉ፤
- ለመንግሥት የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱና ላወቀበት፤ ምንዛሬው ለልማት መዋሉ፤
- ማይግራንቱ ወይንም ስደተኛው የሚሸምተው ልምድና እውቀት ለተወለደበት አገር ልማት ሊውል መቻሉ፤ ቢያንስ እድል መኖሩ፤
- ፈቃደኛና አንድነቱ የጠነከረ በሆነበት ጊዜ ለተወለደበት አገር አምባሳደርና ጠበቃ ሊሆን መቻሉና
- አገር ቤት ሊነሱ የማይችሉትን ጥያቄዎች ለማንሳት ማስቻሉ ይገኙበታል።
አገርን ለቆ መሄድ ለምን አስፈለገ?
የተባበሩት መንግሥታት ባደረገው ጥናትና ምርምር መሰረት ግለሰቡ አገሩን ትቶ እንዲወጣ ወይንም እንድተወጣ የሚገፉት ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው:
- የስራ እድል አለመኖሩና ቢኖርም ገቢው ዝቅተኛ መሆኑ፤
- ኑሮና ህይወት ለግለሰቡና ለቤተሰቡ አስተማማኝ አለመሆኑ፤
- የሰብአዊ መብቶች አለመከበራቸው፤ የሕግ የበላይነት አለመኖሩ፤
- የዘውግና የኃይማኖት ግጭቶች መከሰታቸውና መፍትሄ አለማግኘታቸው እና፤
- 5. የአገር ሁኔታ ጤናማ አለመሆኑ።
ውጭ ለመሄድ የሚስቡ ሁኔታዎችስ ምንድን ናቸው?
- የስራ እድል ይኖራል የሚል እምነትና የገቢ ፍላጎትን ለመጨምር ያለው ፍላጎት፤
- በውጭ አገር የሚኖረው የተሻለ የኑሮ ሁኔታና የማህበረሰባዊ መሰረታዊ ልማት፤
- የመንቀሳቀስ፤ የመናገር፤ የመሰብሰብና የመደራጀት ነጻነት፤
- የማህበረሰባዊ ቴክኖሎጅ ስርጭት ዘመናዊነትና አስተማማኝነት፤
- የመጓጓዣ ቀላልነትና አቅርቦት እና
- የዓለም ትሥስር ጋባዢነት።
ሁለቱም ሁኔታዎች በአንድ ላይ መገምገም ይኖርባቸዋል። ይህን ሁኔታ በፍጥነትና በማይመለስ በሚመስል ደረጃ የለወጠው ዛሬ መላውን ዓለም ያስጨነቀው ኮቢድ-19 የተባለው ወረርሽኝ ነው። ለምሳሌ፤ ይህ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በሌባኖን የሚገኙ ከአራት መቶ ሽህ በላይ የሚገመቱ ኢትዮአጵያዊያን የቀን ሰራተኞች፤ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ከዚህ በላይ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያንና በሌሎች የገልፍ አገሮችና በየመን የተሰደዱ ወገኖቻችን አሰቃቂና አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ቀደም ሲል የነበሩ እድሎች እየተዘጉ መሄዳቸው አይቀርም።
የዚህ የእድሎች እየጠበበ መሄድና የባሰውን መፈናፈኛ ማጣት አንደምታ ምን ይሆናል? ብለን እንጠይቅ።
የፊሊፒኖዎች ልምድ እንደሚያሳየው፤ ስደተኞች የሚያስገኙት ጥቅም ግዙፍ ነው።
አንደኛ፤ ቤተሰቦቻቸው ከድህነት ነጻ እንዲሆኑ አድርጓል፤ ቤት ይሰራሉ፤ ለምግብና ለጤና አገልግሎት ገቢ ይሰጣሉ፤ ዘመድ ያስተምራሉ፤ ቤተሰቦቻቸው የራሳቸውን የግል ተቋም እንዲመሰርቱ ካፒታል ወይንም መዋእለንዋይ ይለግሳሉ።
ሁለተኛ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገራቸውን ኢኮኖሚና የገቢ መጠን ያሳድጋሉ፤ የስራ እድል ይፈጥራሉ።
ሶስተኛ፤ የኤዥያ አገሮች በ 2016 ካገኙት $240 ቢሊየን መካከል ግዙፍ ገቢ አግኝታለች የምትባለው አንዷ አገር ፊሊፒንስ ናት። ይህች አገር ለተሰደዱት ዜጎቿ የተለየ እንክብካቤ ታደርጋለች፤ ወሳኝ የሆነ ገቢ ስለምታገኝ። ችግር ሲደርስባቸው ትደርስላቸዋለች። የፊሊፕንስ ኤምባሲ የተለየ ትርኩረት እንዲሰጥ ታደርጋለች።
አራተኛ፤ በ 2018, ፊሊፒኖዎች ወደ አገራቸው የላኩት የውጭ ምንዛሬ መጠን $31 ቢሊየን ነበር፤ ከውጭ እርዳታ፤ ከውጭ ኢንበስትመንት በላይ ግዙፍ መሆኑ ነው።
አምስተኛ፤ የፊሊፒንስ ሰራተኞች ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊት ስለ የሚልኩት ገንዘብ ለአገራቸው ወሳኝ ስለመሆኑ፤ ስለ መብታቸው፤ ስለ ጤናቸውና ደህነታቸው፤ ስለ ገነዘብ አጠቃቀማቸው (Financial Literacy) ወዘተ ልዩ ስልጠናና ትምህርት ይሰጣቸዋል፤ እርስ በርሳቸው ይደጋገፋሉ።
ስድስተኛ፤ ጥናቶች የሚያሳዩት ገንዘብ ወደ አገር መላክ ብቻ ሳይሆን፤ የሚላከው ገንዘብ ምን ላይ እንደሚውል እቅድ አውጥቶ ውጤቱንም ለሕዝብ ማቅረቡ ጠቃሚ መሆኑ ይታያል።
ሰባተኛ፤ በተቻለ መጠን የውጭ ምንዛሬው እንዳይባክንና በትክክል ገቢ እንዲሆን በባንክ እንዲላክ የሚደረግበትን ሁኔታም እንዲገነዘቡት ይደረጋል። በሌሎችም አገሮች የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ማስተላለፍ በሕግ የተከለከለ ነው።
አንዱ ኢትዮጵያን ለመርዳት የምንችልበት ዘዴና መንገድ የውጭ ምንዛሬን በጥቁር ገበያ ከመቀየር ማቆምና በህግ ወደ አገር መላክ ነው። ሌላው የዲያስፖራ ቦንድ መግዛትና ለልማት እንዲውል ማድረግ ነው፤ ለምሳሌ፤ የህዳሴ ግድብን ስኬታማ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ መስጠት።
የተባበሩት መንግሥታት ምክር ሲሰጥ እንዲህ ብሏል።
“Channeling remittances into the country’s development projects requires not only devising investment products targeting at migrant workers and diasporas, but also much broader policy interventions. Currently, the major portion of remittances, apart from investing in housing, education, and health, is used for consumption. For remittances to be channeled into investments, remittances have to be captured first in the financial system and intermediated by government institutions as investment assets. Brochures showing end use will strengthen the remitter’s behavior.”
ላሰምርበት የምፈልገው ስደተኛው ወይንም በጠቅላላ ስሙ ዲያስፖራ የሚባለው ከገንዘቡ በተጨማሪ የፖሊሲ፤ የእውቀትና የልምድ አስተዋፆው ግዙፍ ሊሆንና እውቅና ሊሰጠው ይገባል የሚለውን ነው። የኤዢያው ልማት ባንክና የዓለም ባንክ ባጋራ ሆነው የሚከተሉትን ጠቁመዋል።
- ተቋማትን ማጠናከር፤ እውቀትንና የአስተዳደር አቅምን ማጎልበት፤
- መረጃን ማጠናከር፤
- ግልጽነትና ሃላፊነት እንዲኖር ማድረግና
- ለሰራተኞች ሰብአዊ መብት መከከበር ድጋፍ እንዲኖራቸው ማድረግ።,
ብዙ ጊዜ በቀን ሰራተኛውና በዲያስፖራው መከከል ያለውን ልዩነት በሚገባ አናውቀውም፤ ይምታታል።
አንድ፤ የቀን ሰራተኛ ወይንም ማይግራንት ወርከር የሚባለው “ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሂዶ ስራ ፈልጎ ወይንም አግኝቶ በደሞዝ የሚቀጠር” ማለት ነው፤
ሁለት፤ ዲያስፖራ ተብሎ የሚጠራው ደግሞ ልክ አይሁዶች እንዳደረጉት “በራሱ የዘውግ ማንነት የሚታወቅ ግለሰብ፤ ስብስብ፤ ማህበረስብና ሕዝብ” ማለት ነው። ከሃገሩ ፈልሶ በሌላ አገር ኑሮውን የመሰረተ ማለት ነው። ይህ የሕዝብ ክፍል በመላው ዓለም ቢሰራጭም፤ ስለ እናት አገሩ ማሰቡና እናት አገሩን መርዳቱ የተለየ ያደርገዋል።
ሁለቱም ክፍሎች የሚልኩት ገንዘብ ሬሚታንስ ተብሎ ይጠራል። “ገንዘብ ወይንም የውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገር ወደ አገር ቤት ሲገባ ሬሚታንስ ነው። ብዙ ጊዜ የሚላከው ለቤተሰብ፤ ለበጎ አድራጎት በገንዘብ ወይንም በቁሳቁስ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ መድሃኒት፤ ኦምፒውተር፤ መኪና።
ለዚህ ትንተና ግን አግባብ ያለው ለልማት የሚውለው የውጭ ምንዛሬ ፋይዳነት ነው። ልማትን ግን ከእድገት ጋር አናማታው። የተለያዩ ናቸው። ጥናቱ የሰጠውን ትርጉም እጋራለሁ። ይኼውም፤ “Development is more than an economic parameter and encompasses human rights. Development goes beyond economic growth to embrace notions linked to human development, which focuses on the individual, his/her family and community, and seeks to expand individual capabilities and choices through health, education, a decent standard of living, and political freedom.”
ልማት ከሰብአዊ መብቶች መከበር ጋር፤ ከዜጎች ደህንነት ጋር፤ ከጤና፤ ከትምህርት፤ ከመልካም አስተዳደርና ከኑሮ መሻሻል ጋር የተያያዘ ክስተት ነው። ዲያስፖራው ሬሚታንስን ለመጥፎ ነገር፤ ለምሳሌ፤ ለሽብርተኛነት፤ ለብሄርና ኃይማኖት ጥላቻ፤ አገርን ለማፈራረስና ለተመሳሳይ ወንጀሎች ሲያውለው ግን ልማትን ይበክላል እንጅ አያጎለምስም። ለምሳሌ፤ በቅርቡ በሻሸሜን የተፈጸመውን እልቂትና የኢኮኖሚ ውድመት ለፈጸሙ ወንጀለኞች ከውጭ ሆኖ በገንዘብና በሌላ የረዳ ግለሰብ ወይንም ስብስብ በሕግ ሊጠየቅ ይችላል የሚለው አግባብ አለው። ሌሎች ብዙ የሚጠቀሱ ምሳሌዎች አሉ፤ ግን ለትንተናየ አግባብ የላቸውም፡:
ብሄራዊ መግባባት ከመወነጃጀል መርህ ውጭ መሆን አለበት።
የብሄራዊ መግባባት ውይይት ሲደረግ ከላይ የጠቀስኳቸውን ጥሩና መጥፎ ምሳሌዎች መጥቀስ አግባብ ነበረው፤ ሲጠቀሱ ግን አልሰማሁም። ዲያስፖራው በነጻነት በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች እየኖረ የትውልድ ሃገሩን ለእልቂትና ለጥፋት ከዳረገ በሃላፊነት መጠየቅ አለበት። እነ ጃዋርን፤ እነ በቀለ ገርባንና ሌሎቹን በሰሩት የእልቂትና የንብረት ውድመት ወንጀል የተከሰሱትን ግለሰቦች እየለዩ “የህሊና እስረኞች ናቸው” ማለት፤ የሰሩት ጥፋት ሁሉ “የፖለቲካ ጥያቄ እንጅ የሕግ የበላይነትን የሚመለከት” ግድፈትና ወንጀል አይደለም የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን፤ ጽንፈኞችና ብሄርተኞች በዓለም የማይታሰብ ትርጉም ያለው ክስተት በመፍጠር ላይ ናቸው። በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ “ኣኛን ሕግ አይመለከተንም፤ የመንግሥት አገዛዝ ስርዓት አንቀበልም” የሚል ትርክት ነው። ይህን ከተቀበልን ግን፤ የህወሓት ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን በኦሮሞው፤ በአማራው፤ በሶማሌው፤ በአኟኩና በሌለው ንጽህ ኢትዮጵያዊ ላይ የፈጸመው ወንጀልና ያካሄደው ድርጅታዊ ምዝበራ ሁሉ ትክክል ነበር፤ የሕግ የበላይነት አይመለከተውም ማለት ነው።
እኔ እንደሚገባኝ፤ የሕግ የበላይነት ይከበር ሲባል፤ ዘውግን፤ ቡድንን፤ የኃይማኖትንና የፖለቲካ እምነትን መለያ መስፈርት እያደረጉ፤ “እኛንና የእኛን” ሰዎች አትንኩብን ማለት ከሆነ ብሄራዊ መግባባት ስኬታማ ሊሆን አይችልም። የሕግ የበላይነት ፋይዳ ቢስ ይሆናል።
ሌላው እጅግ በጣም የተሳሳተ ትርክት የኢትዮጵያን ረዢምና ዓለም የሚያውቀው ታሪክ የመቶ ዓመታት ታሪክ ነው የሚለው ትርክት ነው። ጥናቶችንና ምርምሮችን ለሚከታተል ምሁርና ሌላ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው በ 1, 500 B.C. እንጅ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አይደለም። H.G. Wells እና ደራሲ ተክለ ጻድቅ መኩርያ ብቻ የጻፏቸውን ማንበብ ይጠቅም ነበር። ታላቁ የአክሱም ሥልጣኔ በ 400 B.C. እንደ ተመሰረተ መራጃ ካለ፤ የኢትዮጵያን ዝናና ታሪክ መጽሃፍ ቅዱስና ኮራን በተደጋጋሚ እውቅና ከሰጡት መለወጥ ያለበት ይህን አልቀበልም የሚለው ክፍል እንጅ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም።
በእኔ ጥናት፤ ምርምርና እምነት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ድርድር ሊካሄድ አይችልም። ይህን የሚያጠናክሩ ሌሎችም ሁኔታዎች አሉ። ኢትዮጵያ በ 1974 ዓ.ም. የሰብአዊ ፍጥረት መነሻ አገር መሆኗን ለዓለም ህብረተሰብ ያበረከተችና እውቅና ያገኘት አገር ናት። ቁም ነገሩ፤ ኢትዮጵያ ተከታታይነት ያላት አገር መሆኗ፤ የኢትዮጵያ የሕዝብ ስርጭት ደግሞ የተጀመረው የዛሬ መቶ ዓመት አለመሆኑን የሚያንጸባርቅ ወርቃማ ሕዝብ መሆኑ ነው። አብዛኛው የኢትዮጱያ ሕዝብ በአንድነቱና በኢትዮጵያዊነቱ ያምናል። እስኪ ይጠየቅና ምን እንደሚል ይናገር!!
ይህ ለብዙ ሽህዎች ዓመታት የተዋለደና የተዛመደ ሕዝብ ጽንፈኞችና ጠባብ ብሄርተኞች እንደሚሉት ሳይሆን፤ በምንም አይነት እንዳይፈርስ የሚያደርገው ከብረት ሰንሰለት የጠነከረ ብሄራዊ ትሥስር አለው።
ለማጠቃለል፤
- ኢትዮጵያ ትላንት የተመሰረተች፤ ነገ የምትጠፋ አገር አይደለችም።
- ኢትዮጵያዊነት “መንፈስ” ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ልማት መሰረትና የጥንካሬው መንስኤ እሴት ነው። ዘውግ ተኮሩ ሕገመንግሥትና የክልሉ አስተዳደር መቀየር አለበት ብየ የምከራከረው ይህን የጋራ እሴት ስለናዳቸው ነው።
- ኢትዮጵያን የዘውግና የኃይማኖት እልቂት ሲዖል የሚያደርጉትን በአገር ውስጥና ከሃገር ውጭ የሚኖሩትን ጽንፈኛ፤ ሽብርተኛና ከፋፋይ ግለሰቦች፤ ስብስቦችና አጋር የሆኑትን የውጭ ኃይሎች በማያሻማ ደረጃ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን፤ በሃላፊነት እንዲጠየቁ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
- “ጩኸታችን” ነጥቀው የተሳሳተና በመረጃ ያልተደገፈ ትርክት የሚያስተጋአቡትን ግለሰቦች ለወንጀለአኞች፤ በተለይ ለሽብርተኞች ምሽግ መሆናቸውን የምንጋለጥበትና የምንታገልበት ወቅት ዛሬ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።
- በእኔ ጥናት፤ ምርምርና እምነት፤ ከኮረናው ወረርሽኝ በባሰ ደረጃ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወረርሽኝ የሆነው የዘውግና የኃይማኖት ጥላቻን፤ እልቂትንና የኃብት ውድመትን ያስከተለው የዘውግና የኃይማኖት ፅንፈኛነት ስለሆነ ይህን ወረርሻኝ ለማጥፋት በህበረት ለመታገል ከፍተኛ ርብርብ እንዲካሄድ ሳይሰለቹ ዘመቻ ማድረግ ወሳኝ ነው።
- የዐማራውን ሕዝብ “ወራሪና ጡት ቆራጭ ነው” ብሎ ከመወንጀል ይልቅ፤ ለሃገሩ ብሄራዊ ነጻነትና ደህንነት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረትና ሥልጣኔ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተ፤ ከሌሎቹ የዘውግና ኃይማኖት አባላት ወገኖቹ ጋር የተዋለድና የተዛመደ ሕዝብ መሆኑን ተቀብሎ ወደ ልማቱ ጉዞ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ማስተጋባት አስፈላጊ ነው።
- እኛ ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጥ ህብረታችን ሰንሰለት ካጠናከርናቸውና በአስተማማኝ ብሄራዊና አገራዊ ተቋማት ከደገፍናቸው፤ ለምሳሌ የደህንነትና የመከካለያ ኃይል፤ ሚዛናዊ የባጀት ስርጭጥት ወዘተ፤ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የሆነ ልማት ለማሳየት የምትችልበት ሁኔታ ይታያል። አንዱ ምሳሌ የህዳሴ ግድብ ጉዞ ነው።
- ከፍተኛው የሁሉም ባለድርሻዎች ትኩረት መሆን ያለበት፤ ሰላምና እርጋታ፤ የሕግ የበላይነትና የሰብአዊ መብቶች በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ያለ ምንም ገደብ እንዲሰርጹና እንዲከበሩ ማድረግ፤ እውነተኛ የዲሞክራሲ አገዛዝ እንዲሰፍን ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ የስራ እድሎች ለብዙ ሚሊየን ወጣቶች እንዲፈጠሩ ከፍተኛ ብሄራዊ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።
- በክልል ደረጃ ሆነ በፌደራል፤ ዋናው የኢትዮጵያ ትኩረት ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል መፍጠርና ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ መሰረት መጣል ነው (Create a resilient and strong national economic foundation).
- ማንኛውም ግለሰብና ስብስብ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያካሂደውን የዘውግና የኃይማኖት ጥላቻና እልቂት፤ በንብረት ላይ የሚፈጽመውን ውድመት ማውገዝና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን በማያሻማ ደረጃ ማወጅና መተግበር።
- ብሄር ተኮሩ ሕገመንግሥትና የክልሉ አስተዳደር ስርዓት ለልማት ማነቆ መሆኑን ጭምር ተገንዝቦ በሞያተኞች የተጠና አማራጭ ለሕዝብ እንዲቀርብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከአሁኑ ለዚህ አማራጭ ያላቸውን ግምገማና አቋም እንዲገልጹ ማሳሰብ።
- ሕዝብን ያሳተፈ የእርቅ፤ የሰላምና የብሄራው መግባባት ስራን በሰፊውና በተከታታይ ማካሄድ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑትን ባለሞያዎች ተሳታፊ ማድረግ።
AB/8/26/2020
Citations and References
United Nations, Department of Economic and Social Affairs, Population Division (2017a): Trends in International Migrant Stock: The 2017 revision (United Nations database, POP/DB/MIG/Stock/Rev.2017)
World Bank (2017). Migration and Remittances: Recent Developments and Outlook Special Topic: Global Compact on Migration, Migration and Development Brief No. 27
ADB, the World Bank and ILO, LABOR MIGRATION IN ASIA: Increasing the Development Impact of Migration through Finance and Technology, Manila, 2017
United Nations, Department of Economic and Social Affairs, Population Division (2017)
Asian Development Bank and the World Bank, Migration and Remittances: Migration and Remittances for Development in Asia and Recent Developments and Outlook, May 2018
Special Topic: Global Compact on Migration, Migration and Development Brief No. 27 reads and interviews, May 2018
LABOR MIGRATION IN ASIA: Increasing the Development Impact of Migration through Finance and Technology, ADB, OECD and ILO, 2018
UN International Migration Report, 2017
Remittances and Vulnerability in Somalia: Assessing sources, uses and delivery mechanisms, Rift Valley Institute, Nisar Majid, with Khalif Abdirahman and Shamsa Hassan. November 2017
Diaspora Engagement and the Global Initiative on Somali Refugees—emerging possibilities, UNHCR, January 2016
Migration and Remittances, the World Bank, August 2017
Migration and Remittances: Recent Developments and Outlook. Migration and Development Brief, No. 30, December 2018. World Bank, Washington, DC.
Migration and Remittances: Recent Developments and Outlook. Migration and Development Brief, No. 29, April 2018. World Bank, Washington, DC
MIGRATION DATA PORTAL: The bigger picture, IOM, Berlin
UN Migration Agency: “Remittance Flows Can Be an …https://www.iom.int/…/un-migration-agency-remittance-flows-can-be-econ and IOM AND REMITTANCES, Annual Reports