ዴሞክራሲያ ቅጽ 48 ፣ ቁጥር 3                                          ነሐሴ ፣ 2012 .

ጥላቻ፣ አክራሪነትና ዘረኝነት አንድም ሦስትም ናቸው!

ሀገራችን ኢትዮጵያ የታሪክ ባለፀጋ ብትሆንም፣ በዘመናዊ ሥልጣኔ ኋላቀር መሆኗ ያ ትውልድ በመባል የሚታወቀውን ትውልድ እጅግ አስጨነቀው። የኢሕአፓን ቀደምትና የአሁን ጀግኖችን ያቀፈው ትውልድ፣ አገራችን ወደ ሥልጣኔ ማማ በፍጥነት እንድትደርስ ለማድረግ ያልቆፈረው ድንጋይ፣ ያልዘየደው መላ አልነበረም። ይሁን እንጂ ችኩልነቱ ከውስጣዊ ድክመቱ ጋር ተደምሮ ዓለም የነበረችበት ታሪካዊ ኩነትና ሥልጣኑን ለሕዝብ ለማስረከብ ያልፈቀደው ወታደራዊ ደርግ ባካሄደው ወደርየለሽ ጭፍጨፋ፣ አገር እንኳን ወደ ሥልጣኔ ማማ ልትሻገር ይቅርና ብሩኅ አእምሮ የነበረው ትውልድ ያለቀበት ታሪክ እንዲከሰት ሆነ።

ያ አገር አፍቃሪ ትውልድ፣ ወደር የሌለውን መስዋዕትነት በሚከፍልበት ወቅት፣ ኢትዮጵያችን በአንድ በኩል በጉልበት ብቻ መፍትሄ ለማምጣት ትውልድ የፈጀው ወታደራዊ መንግሥት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ የታጠቁ ጎጠኛ ቡድኖች የሚፋለሙባት የጦርነት አውድማ ሆነች። የጎጠኞች ዓላማ ደርግን አሸንፈው ሕዝባችን የሚፈልገውን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመዘርጋት አልነበረም። በጥላቻ የታጀበውን ፀረኢትዮጵያ ዓላማቸውን መተግበር መሆኑን ለማወቅ ሥልጣን እስቲይዙ መጠበቅ አላስፈለገም። በ1982 መግቢያ ላይ፣ ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ፣ በአሶሳ ከተማ ኦነግና ሻዕቢያ የተሳተፉበት ክርስቲያኖችንና አማራዎች የሚሏቸውን ለይተው ቤት ዘግተው በእሳት ማቃጠላቸው የሕዝቡ መፃዒ ዕድል ምን ሊሆን እንደሚችል አመላካች አሰቃቂ ተግባር ነበር።

ህወሓት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከሸሪኩ ከኦነግ ጋር በምሥራቅ ሐረርጌ በወተርና አርባጉጉ በርካታ አማራ ያሏቸውን ዜጎች ገደል ውስጥ በመወርወር ጭምር ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን የወቅቱ ፓርላማ ተብዬው ሳይቀር ያመኑት እኩይ ተግባር ነበር። ህወሓት በኦነግ ሲያመካኝ፣ ኦነግም ህወሓት ነው ግድያውን የፈጸመው እየተባባሉ በፈጸሙትና ባመኑበት ወንጀል በሕግ ሳይጠየቁ ይህንኑ እርኩስ ተግባራቸውን ሕጋዊ ወደሚያደርግ ሕገመንግሥት ቀረፃ ተሸጋገሩ።

ህወሓት ሲመሠረት ጀምሮ የአማራ ብሄረሰብን በ1968.ም ባወጣዉ የትግል ማኒፌስቶ በጠላትነት ፈርጇል። በለስ ቀንቶት ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ ትግሌ የመገንጠል ነው ይልም ነበር። ህወሓት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር በተንሸዋረረ መንገድ በመተርጎም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋናው ቅራኔ በብሄረሰቦች መካከል ያለው ነው አለ። ኢሕአፓ፣ ህወሓት የተንሸዋረረ አተያዩን እንዲያስተካክል ለማድረግ ከፍተኛ ትግል አድርጓል። በኢሕአፓ ዕምነት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋነኛው ችግር፣ ያኔም ይሁን ዛሬ፣ የድህነት መንሰራፋት፣ የፍትህ መጥፋት፣ የዜጎች መብቶች አለመከበር፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመኖር ነው ብሎ ያምናል። ድህነት ትግራዋይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አፋር….ወዘተ ብሎ የማይለይ በመሆኑ ዜጎች በጋራ ተደራጅተው በመታገል መብትን ማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መመሥራት፣ ድህነትን መቅረፍ አለባቸው ብሎ ያምናል ኢሕአፓ። በተዛማጅነት ብሄረሰቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የማዳበርና የማሳደግ መብቶቻቸው መከበር አለበት ይላል ኢሕአፓ። የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች፣ ከግጦሽ መሬት ጋር ተያይዞ ከነበሩ ትንንሽ ግጭቶች ባለፈ፣ በማንኛውም ወቅት ማንነትን ብቻ መሠረት ባደረገና ጎራ በለየ ጦርነት ውስጥ ገብተው አያውቁም።

የኢሕአፓ ዕምነትና የፖለቲካ አቋም ያልተዋጠለት ህወሓት፣ በጠመንጃ ኃይል አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢሕአፓን ከሽግግር ሥርዓቱና ከሕገመንግሥት ቀረፃው ሂደት አገለለ። ፀረዴሞክራሲያዊው ህወሓት ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገት ይልቅ የማይስማማውን ሃሳብ የያዘውን ድርጅት ማገድን አማራጭ አደረገ። በወቅቱ የተሳተፉ ጠባብ ብሄረተኞችና አዳዲሶችንም ጠፍጥፎ ሠርቶ፣ የሕገመንግሥት ጉባዔ ብሎ ጠንካራና ሞጋች ሃሳቦች ሳይካተቱበት ሕገመንግሥት ቀረፃውን አካሄደ። ይህም ቀደም ሲል ኤርትራ ውስጥ ሰንዓፈ ላይ ከኦነግ ጋር የጨረሱትን፣ በዋናነት የራሱን ፖለቲካ ፕሮግራም ገልብጦ እንደ ሕገመንግሥት ረቂቅ በማቅረብ፣ በተመረጡ አውራጃዎች ውስጥ ውይይት አስደረኩ በማለት፣ የተወሰኑ አለማቀፍ ድንጋጌ በሆኑት የሰባዊና ዴሞክራሲ መብቶች ሸፍኖ የራሱን የፖለቲካ ፕሮግራምና የህዉሀት የፓርቲ ማኒፌስቶ በሕገመንግሥት ስም በ1987 .ም አፀደቀ።

ሕገመንግሥቱ ኢትዮጵያን “ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ” አደረጋት ተብሎ ስያሜው ቢያሰጣትም፣ እነሆ ከ30 ዓመታት በኋላም ኢትዮጵያ “ፌዴራላዊም ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክም” ሆና አልተገኘችም። ዘውግ ተኮር እንጂ ዜጋ ተኮር ሕገመንግሥት አይደለም የሚለውን ታላቅ የክርክር ነጥብ ለጊዜው ወደ ጎን እንተውና እስቲ በጎ በጎ የሚባሉትን ባህሪውን እንፈትሸ።

ህወሓት ሠራሹ ሕገመንግሥት መሠረታዊ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማለትም የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፎችን የማድረግ መብቶችን በፅሁፍ ቢያሰፍርም፣ በከፊልም ቢሆን እውን መሆን የጀመሩት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው። እነዚህን መሠረታዊ የዴሞክራሲ መብቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ዜጎች በሕይወት መኖር ሲችሉ ብቻ ነው። “ጽድቁ ቀርቶ በወግ በኮነነኝ” እንዲሉ፣ መንግሥት ባለበትና “ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ” ተብላ በምትጠራ አገር ውስጥ፣ እነዚህ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መብቶች አለመከበራቸው ብቻ አይደለም ዜጎች እንደ ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንደ ብርቅ የሚታይባት አገር ሆናለች። ሕገመንግሥቱ በፌደራላዊ አደረጃጀት ስም በተወሰኑ ብሄረሰቦች ስም የተሰየሙ ክልሎች ዜጎችን “መጤና የክልሉ ባለቤት” በሚል እንዲከፋፈሉ አድርጓል። በመሆኑም ዜጎች በደረጃ እንዲታዩ ያደረገ ስለሆነ፣ በዜግነታቸው በእኩልነት ማግኘት የሚገባቸውን የዴሞክራሲያዊናና የሰብዓዊ መብቶች ተነፍገው፣ ባይተዋርነት እንዲሰማቸውና ሕይወታቸውም በስጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጓል። የሕገመንግሥቱ ፅንሰሃሳብና መሠረት የቆመበት ከፋፋይ ትርክት፣ ዜጎች ቅድመ አያቶቻቸው ሳይቀሩ ተወልደው ባደጉበት ቦታ፣ የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ አባል ናችሁ በሚል፣ በሕይወት የመኖር መብት የተነፈጉበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች አገራችን ኢትዮጵያ። ባጭሩ ዛሬ ኢትዮጵያችን ዴሞክራሲም ይሁን እኩልነት የሰፈነባት አገር በፍጹም አይደለችም። የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ ደግሞ ሕገመንግሥቱ መሆኑን መደበቅ አይቻልም።

ከላይ እንዳየነው ሕገመንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት የተጀመረው ብሄረሰብ ተኮር ጥቃትና (በተለይም በአማራ ላይ) ሕገመንግሥቱ ከፀደቀ በኋላም ተጠናክሮ በመቀጠሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የጥቃቱ ሰለባዎች እንዲሆኑ አድርጓል።

ሕገመንግሥቱ ላይ የሠፈሩት አንቀጾች ስላልተገበሩ ከሃሳብና ከፖለቲካ ፍጆታ ያላለፉ የተፃፉበትን ወረቀት ዋጋ እንኳን የማይመጥኑ ባዶዎች ናቸው። ለምሳሌ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት እኩል መሆኑን፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የመኖርና ንብረት የማፍራት፣ በሚኖርበት ቦታ የመምረጥና የመመረጥ መብቶች የሚገልጽ ቢሆንም የይስሙላ ከመሆኑም ባሻገር ሦስት አሥርተዓመታት እያስቆጠረ ያለው ሕገመንግሥት በርካታ ህፀጾች ያሉት በመሆኑ ማሻሻሉ የግድ ነው።

የፌዴሬሽኑን ሕገመንግሥት ተከትለው የተቀረጹ የክልል ሕገመንግሥቶችም፣ የተዋቀሩት ባለቤት ናቸው በተባለላቸው ብሄረሰቦች ማዕከልነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በመሆኑም ባለቤት ናቸው ከተባሉት ብሄረሰቦች ውጪ ያሉትን “መጤ” ብለው ለሚጠሯቸው ግለሰቦችም ሆነ ማኅበረሰቦች መብት የማይሰጡና ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ዝቅ አድርገው የሚገባቸውን ከለላ በመንፈግ የሚጠቁበትን ሕጋዊና መዋቅራዊ ሰፊ በር አመቻችተዋል። ይህ ነው እንግዲህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የዜግነት መብት የነፈገ ሕገመንግሥት የ”ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ” ሕገመንግሥት የሚባለው!

በሀገራችን ውስጥ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ግምባር ቀደም ተጠቂ ይሁኑ እንጂ፣ “መጤ”ና “ኗሪ” በሚል የጥላቻ ትርክት የተቀመረው ሕገመንግሥት ሌሎች ብሄረሰቦችንም ለጥቃት አጋልጧቸዋል። ጉራጌዎች፣ ስልጤዎች ጋሞዎች…ወዘተ ተጠቂዎች ሆነዋል። በሃይማኖትም ክርስቲያን ኦሮሞዎች የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል ይገኛሉ። በአብዲ ኢሌ የሥልጣን ዘመን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዜጎቻችን ከሶማልያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ተፈናቅለዋል። በተመሳሳይ መልኩ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሌ ብሄረሰብ ዜጎቻችን ከኦሮሚያ ተፈናቅለው ለስቃይ ተዳርገዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጌዲዖ ዜጎቻችንም በኦሮሞ ፅንፈኞች ተፈናቅለው በብርድና በዝናብ በመጠለያ ሥፍራዎች እስከ አንድ ዓመት ድረስ ኖረዋል። የፈረደባቸው የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ከቤኒሻንጉል በተደጋጋሚ ተፈናቅለዋል፣ እስከዛሬም ያላቆመ ክስተት ነው። በጎንደር ህወሓት ያስታጠቃቸው የቅማንት ታጣቂዎች በፈጠሩት ጥቃትና በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ ተጠያቂነትን በማይወስዱ አካሎች ባደረሱት በደል ተፈናቃዮች ተበራክተዋል። ዛሬም የሰው ሕይወት እየጠፋ እንደሆን በወሩ መጀመሪያ ላይ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የገለጸው ጉዳይ ነው። በአዋሳ፤ በይርጋለምና በአካባቢውም እራሳቸውን ኤጀቶ ብለው በሰየሙ ወጣቶችም ብሄረሰብ ተኮር የሆነ ግድያና የንብረት ውድመት ተካሂዷል። በተጨማሪም በአክራሪ ኃይሎች የሚመራ በተለይም ወጣቶችን በግንባር ቀደምትነት ያሰለፈው በቡራዩ፣ በአርሲ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በሻሸመኜ፣ በዝዋይና በባሌ እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ የተካሄደው ጥቃት፣ ባመዛኙ የአማራና ሌሎችንም “መጤ” ተብለው የተሰየሙ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ፣ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞችንና የዕምነት ቤቶችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ነው።

በቅርቡ፣ እንደ መንግሥት አገላለጽ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳን በማስገደል መፈንቅለመንግሥት ለማድረግ የተወጠነ ነው የተባለለት ጥቃት፣ በአዲስ አበባና በኦሮምያ ከ200 በላይ የዜጎችን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ የቀጠፈ እኩይ ተግባር ተፈጽሟል። ከግድያው በተጨማሪ የሥራአጡ ቁጥር ጣሪያ በነካበት አገር፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ ሆቴሎችን በማቃጠል በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሥራ የነጠቀ ውድመትም ተፈጽሟል። ድርጊቱ በዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል ጭካኔ የታየበት ኢሰባዓዊ ድርጊት ነው። የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ የተሰቀለበት፣ ሬሣ በመኪናና በሞተር ብስክሌት የተጎተተበት፣ ሰው በገጄራ የተከተፈበት፣ እርጉዝ እሴት አንገቷን የተቀላችበት ክስተት ነበር።

በ“ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ” እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ወንጀል እንዴት ሊፈጸም ቻለ? ምናልባት የለውጥ ጊዜ ስለሆነ እንደማንኛውም የለውጥ ጊዜ ችግር አይጠፋም ብለን የምናልፈው ነው ወይ? ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ማጥፋቱና ንብረት ማውደሙ እንደገና እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት?

በጭፍጨፋውና በንብረት ውድመት ወቅት የክልሉ ልዩ ፖሊስና የመንግሥት የፍትኅ መዋቅሮች አንድም በቀጥታ የተሳተፉበት፣ አልያም ስልካቸውን በማጥፋት የዕርዳታ ምላሽ ያልሰጡበት፣ ወይም “ትዕዛዝ አልደረሰንም” በማለት ጭፍጨፋውን እያዩ በዝምታ ያለፉበት ሂደት እንደነበር መንግሥት ገልጿል። ስለሆነም በመቶዎች በሚቆጠሩ ፖሊሶችና የመንግሥት ሠራተኞችን የማጽዳት ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል። እስካሁን ከ7000 በላይ ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር ሥር እንዳደረገ መንግሥት እየነገረን ነው። እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ስንመለከት፣ በመናጆነትም የተያዙና ለፖለቲካ ሚዛን ሲባል ብቻ የታሰሩ እንዳሉ እንጠረጥራለን። “ሁለተኛ መንግሥት” ነን የሚሉ ያለ ኢትዮቴሌ መሥሪያ ቤት እውቅና ሳተላይት ከውጭ አስገብተው የዘረጉ እንደሆነ የተጠረጠሩና በሰላማዊ ታጋይነታቸው የሚታወቁም በጣምራ ታግተዋል። የፍርድ ሥርዓቱ ጥፋተኞችን ከመናጆዎች ለይቶ ለአጥፊዎቹ ተገቢውንና ተመጣጣኝ ፍርድ ይሰጣል ብለን እንጠብቃለን።

ከህወሓት ሕገመንግሥት በተጨማሪ ለዓመታት የተካሄደው የጥላቻ ትርክት ለዜጎች ዕልቂት ምክንያት ሆኗል። ለዘመናት በደምና በአጥንት ተሳስሮ የኖረውን ማኅበረሰብ መስተጋብርም ሸርሽሯል። ሌላው ቀርቶ የባንክ አገልግሎት እንኳን በብሄረሰብና በሃይማኖት እንዲበጣጠስ አስተዋፅኦ እንዳደረገ መጥቀስ ይገባል።

ከላይ እንደገለጽነው ጽንፈኞች ያነገቡት የጥላቻ ትርክትና አክራሪነት ሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ቂም አርግዞ፣ ወልዶና አሳድጎ ለዚህ እያበቃን እንደሆነ አይተናል። ይህንን ጥላቻም ሕገመንግሥታዊ ቅርፅና መልክ ሰጥቶ በአንድ አገር የሁለት ደረጃ ዜግነት ሥርዓት ሥር የሰደደበትን አስከፊ ገፅታ እንዳለም ተመልክተናል።

ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮና ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ጥላቻውንና ብሄረሰብ ተኮር ጥቃቱን በመረዳት የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ ታግሎታል። የሕዝባችን የጋራ ትግል ግቡ በዜጎች እኩልነት ላይ ለተመሠረተ ሃገራዊ አንድነት፣ አሳታፊ ለሆነ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርንና ዘላቂ ሰላምን ተከትሎ ለሚመጣ የሀገሪቱን ሁሉም አካባቢዎችና ሕዝቦች በተመጣጠነ የልማትና የዕድገት ጎዳና የሚወስድ ሥርዓትን መፍጠር ነው። ለውጡ ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ ሲከሰትም ሕዝባችን በተስፋና በንቃት የተሳተፈው እነኝህን እሴቶች ወደ መሬት ለማውረድ ነበር። ሆኖም በለውጡ ግቦች ላይ ያለው ሂደት አስተማማኝ አለመሆኑና እንዲያውም በተቃራኒው የሚኬድበት መንገድ መታየቱ “ለውጡ የት ገባ?” ብለን በቀደመው የዴሞክራሲያ ዕትም እንድንጠይቅ ተገደናል።

ለውጡን ወደ ሃዲዱ ለመመለስና በኢትዮጵያ አድሏዊ የሆነ የሁለት ደረጃ የዜግነት ሥርዓት እንዲያከትም፣ መንግሥት አሁን የጀመረውን የሕግ ማስከበር ሂደት፣ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውንና የሕግ የበላይነትን መተክል ሳይስት፣ በስፋትና በፅናት መቀጠል አለበት። መንግሥት እስካሁን ያሳየው ታላቅ ድክመት ሕግ በማስከበር ተግባር ላይ ወላዋይ ሆኖ መቆየቱ ነበር። ይህ አካሄድ ደግሞ ሕግ አፍራሾችን እያደፋፈረ በጥፋት ላይ ጥፋት እንዲፈጽሙ አበረታቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ሕግ ማስከበር የጀመሩት ሥርዓት አልበኝነቱ የሳቸውንም ሥልጣን ወደሚፈታተንበት ደረጃ በመድረሱ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ። በዚህም ሆነ በዚያ፣ በሀገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሕግ ማስከበሩ የቆየ የሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።

የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ጋር በተጓዳኝ ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ ብለን እናምናለን። ዋና ዋናዎችን ከመጥቀሳችን በፊት በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸመው ጥቃት በአስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን ላጡ፣ ለቆሰሉና ለተፈናቀሉ ዜጎች ቤተሰቦች ኢሕአፓ ፅናቱን እንዲሰጣቸው እየተመኘ መንግሥትም መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባል። በተያያዥም፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለታደጉ የኦሮሞ ብሄረስብ አባላት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል።

በኢሕአፓ እምነት በአስቸኳይ መከናወን ይገባቸዋል ብሎ ከሚያምናቸው ውስጥ፦

  1. ብሄረሰብና ሃይማኖት ተኮር በሆነ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የሚሳተፉት ቄሮ የተባሉ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ ባለፉት ሦስት አሥርተዓመታት በህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓትና ሌሎች አክራሪ ብሄርተኞች ባስፋፉት የጥላቻ ትምህርት ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው። የኢትዮጵያዊነትን እሴቶች በአግባቡ ስላልተማሩ፣ በዚህ ረገድ በጥናት ላይ የተመሠረተ ትምህርትና ሥልጠና፣ በኢትዮጵያ ታሪክና በአብሮነት መስተጋብራችንና ስለ ጋራ ዕሴቶቻችንና ስለ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታና መብቶች በተለያየ ደረጃ ተከታታይ ትምህርት መሰጠት ይኖርበታል።

  2. ሥራአጥነትና ሥራፈትነት ወጣቶቹን ለመጥፎ ተግባሮች ሊያጋልጥ ስለሚችል እንዲሁም ኑሯቸውን ከማዛባት አልፎ በአገሪቱ ኢኮኖሚም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚያሳድር መንግሥት ሥራአጥነትና ሥራፈትነትን ለመቅረፍ የተጠና ቀጣይነት ያለው እርምጃ መውሰድ ይገባዋል።

  3. ወጣቶቹ የሚማሩባቸው የትምህርት መጽሐፍትና ሥርዓተትምህርት በሙያተኞች ተጠንቶ መሻሻል እንዲደረግበትና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጠናክርና የብሄረሰቦችን ወንድማማችነትንና ትብብርን በማጠናከር ዕውነትን መሠረት ባደረጉ ትርክቶች ላይ የተመሠረተ ማድረግ ያስፈልጋል።

  4. አኖሌ ላይ የተተከለው የተቆረጠ ጡት ሃውልት በውሸት ትርክት ላይ የተመሠረተና ከስምምነት ይልቅ ጥላቻን በቋሚነት የሚወክል በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግሥቱ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ባስቸኳይ እንዲፈርስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

  5. የብልፅግና ሹማምንትና የአንዳንድ የብሄረሰብ ድርጅት መሪዎች በሚያደርጓቸው የጥላቻ ንግግሮች ለወጣቶች የሚሰጡት ትምህርት አርአያነት የጎደለውና አሉታዊ በመሆናቸው መታረም ይኖርባቸዋል። ለዚህም ከፍተኛ ስህተት ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ይገባል።

  6. ክልሎች ያቋቋሟቸው ልዩ ኃይል ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎችና የክልል ፖሊሶች፣ እስካሁን ሰላምና መረጋጋት ሲያመጡ አልታዩም። እንዲያውም የሁለት ደረጃ የዜግነት ሥርዓትን የሚያጠናክሩ ብቻ ሳይሆኑ ሙያቸው የሚጠይቀውን በገለልተኛነት ሕግን የማስከበር ተግባር እየፈጸሙ አይደሉም። በመሆኑም አንድን ብሄረሰብ፣ የወገነ የሌሎች ብሄረሰቦች ተወላጆችንና የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮችን (በተለይም የኦርቶዶክስ) ከወጣት አሸባሪዎች ጋር በመተባበር የሚያጠቁ ኃይሎች እንዲፍርሱና ወደ ፌዴራል ፖሊስና አገራዊ ሕግ አስከባሪነት እንዲለወጡ ማድረግ ይገባል።

  7. በዜጎች ላይ የጭፍጨፋ ወንጀል የፈጸሙ ወጣቶች የስም ዝርዝር ይዘው መታወቅያ እየጠየቁ ለጥቃት ያስቧቸውን የብሄረሰብ አባሎች እንዳጠቁ ከበቂ በላይ ማስረጃ ቀርቧል፤ ስለሆንም ኢትዮጵያውያን በመታወቂያ ወረቀታቸው ላይ ብሄረስባቸው እንዳይሰፍር በሕግ ማገድ ያስፈልጋል።

  8. በሁሉም የአገራችን ከፍሎች ውስጥ የተፈጸሙ ዘግናኝ የመብት ጥስቶች ሰፋትና ጥልቀታቸውን ለመረዳት፣ ለሰብዓዊ መብት ሰላባዎች አስፈላጊውን እውቅናና ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያውያን መካከል እንድነትን መልሶ ለማጠናከር፣ ወንድማማችና እህትማማችነትን ለማጎልበት፣ ትርጉም ያለው የብሄራዊ ዕርቅና የብሄራዊ መግባባት ሂደት ሳይውል ሳያድር መጀመር ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም ደጋግመን እንዳሳሰብነው አሁንም እጅግ አስፈላጊነቱን አጠንክረን እያሳስብን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ በአስቸኳይ ሂደቱን እንዲጀምር እንጠይቃለን፣ ኢሕአፓም የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን።

በመጨረሻም ብሄረሰብ ተኮር የሆነውና የሁለት ደረጃ ዜግነትን የፈጠረው ሕገመንግሥት በሀገራችን ውስጥ ለተከሰቱት ቀውሶች ሁሉ መሠረትና ምንጭ ነው። ለተፈጸሙት ዕልቂትና የንብረት ውድመት ዋናው ምክንያት ሕገመንግሥቱ እንደሆነ አረጋግጠውልናል። ዜጎች ያመኑበትና ያፀደቁት ሕገመንግሥት መኖር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ሕገመንግሥቱን ማሻሻል ለነገ የማይባል ዋነኛ ተግባር ነው። በሥራ ላይ ያለው ሕገመንግሥት እንዲቀጥል ከሆነ አገራችንን ወደ መፈራረስ አደጋ ሊያደርሳት ይችላል የሚል ፍራቻ አለን። ስለዚህ በአስቸኳይ ለውይይት ቀርቦ ደጋፊዎችና ተቃሚዎች ሃሳባቸውን ሰጥተውበት በውሳኔሕዝበ ብያኔ እንዲያገኝ መደረግ አለበት እንላለን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!