August 28, 2020
ከታገቱ ዘጠኝ ወር የሞላቸውን የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማሰብና መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር ያለመ ውይይት ተዘጋጀ።
–
ከደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲመለሱ ደብዛቸው የጠፋው 17 ተማሪዎች የመጨረሻ ሁኔታ ሳይታወቅ ትናንት ዘጠኝ ወር ሞልቷቸዋል፡፡
–

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ህዝባዊ ሰልፍ ጠርተው በከተማ አስተዳደሩ በተፃፈ ደብዳቤ ፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ስላለ ፤ ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ የተገደዱት ፤ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ በጎ ፍቃደኛ የአዲስ አበባ ወጣቶች ቅዳሜ በዋቢ ሸበሌ በታገቱት ተማሪዎች ዙርያ ባላድርሻ አካላት የሚገኙበት ውይይት ማዘጋጀታቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቀዋል፡፡
–
በዚህ ውይይት ላይ በመንግስትና በሌሎች ባለድርሻ አካላት እስከዛሬ በጉዳዩ ዙርያ ሲሰራ የነበረው ላይ ዳሰሳ ይቀርባል ተብሏል፡፡
–
ከአዘጋጆቹ ወጣቶች መሀከል የሆነችው ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገረችው ከአንድ ወር በፊት ገደማ መንግስት ለኦነግ ሸኔ አስተላልፈው የሰጡትን ተጠርጣዎች አስሬያለው ቢልም ወደነሱ የሚያመራ ምንም አይነት ፍንጭ አልተገኘም፤ የሚመለከታቸው ሰብአዊ መብት ተቋማትም፣ ሌሎች ድርጅቶችም ይሄ ነው የሚባል ነገር አላደረጉም፡፡
–
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉደዩ ከአቅም በላይ እየሆነባቸው እንደመጣና ፤ ልትረዱ የምትችሉ አካላት ብትረዱ መልካም ነው የሚል ጥሪ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን ልንቀመጥ አይገባንም በሚል ያለፈውን ዘጠኝ ወር የሚዳስስና ለወደፊቱ ምክረ ሀሳብና መንግስት ላይ ጫና የሚፈጥር ውይይት ነው ያዘጋጀነው ብላናለች፡፡
–
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ኢዜማ፣ ባልደራስ፣አብን ኦፌኮና ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች መጋበዛቸውም ተገልጿል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የሚገኙ ሲሆን የአማራ ተማሪዎች ማህበር፤ ይገኛሉ ስትል ተናግራለች፡፡
–
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጉዳዩን ሲከታተል ነበር ፡፡ እነሱንም ጭምር እስካሁን ምን አድርገዋል? ወደፊት ምንስ ለማድረግ አስበዋል? በእለቱ የሚነሳ ጉዳይ ነው ብላለች ጋዜጠኛ መአዛ።
–
የታገቱት ተማሪዎች አስታዋሽ አጥተዋል ይሙቱ ይኑሩ አይታወቅም፤ የምትለው መአዛ በኛ ጥናት መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ብሎ ወይም ፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ሊያደርጉት ስለፈለጉ ፤ የመጣ ነው እንጂ ጭራሽ እገታ የሚባል ነገር አልተፈጠረም ብለው የሚያስቡ መኖራቸውን ማወቃችን የሚያሳዝን ነው ብላለች፡፡ – መነሻችንም መድረሻችንም የነዚህ ታጋቾች ቤተሰቦች ናቸው፡፡ እነሱ ግን ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ እርም አውጥተው ለቅሶ የተቀመጡም አሉ ብላለች መአዛ፡፡
–
መንግስት የሰጣቸው መግለጫዎች እያንዳንዱን ይዘናል በእለቱ ይቀርባል፡፡ የሄደበት መንገድ ቸልተኝነት ያለበት፤ አሳዛኝ ነው ብላለች ፡፡
–
በመንግስት የተሰጡት እያንዳንዱ የተለያዩና የማይገናኙ መረጃዎች ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ለማውጣትና የፖለቲካ ፍጆታነት አድርጎ ከመጠቀም በዘለለ ፍላጎት አላሳየም ፤ ይሄ ስህተት ነውም ብላለች።
–
መንግስት የተሳሳተ መረጃ ሰጥቷል፣ እስካሁን ድረስ እልባት አልሰጠም፣ ምን እያደረገ እንደሆነ እንኳን ለማወቅ አልተቻለም፣ መንግስት በዚህ ጉዳይ ሀላፊነት መውሰድ አለበት፣ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ስትል ተናግራለች መአዛ፡፡
–
ጉዳዩን እንደ ጉዳይ መውሰድ ነው እንጂ አልተፈጠረም ብሎ መካድ ወንዝ አያሻግርም የምትለው ጋዜጠኛ መዓዛ በእለቱ የሀገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በውይይቱ እንዲገኙ ጋብዛለች፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም