29 ነሐሴ 2020

የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ እንደሚገልፀው ከሆነ በአሁኑ ወቅት በጣና ሀይቅ ላይ ያለው የእምቦጭ አረም መጠን 900 ሄክታር አካባቢን የሸፈነ ነው።
ይህንን መጤ አረም ለማስወገድ ከፌደራል መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ አካላት በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በሙያ ርብርብ ያደረጉ ቢሆንም አሁንም ግን እምቦጭ ከመጥፋት ይልቅ እየተስፋፋ ይገኛል።
አለም ዓቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር የሰሞኑን ጨምሮ ሁለት ማሽኖችን ከአውሮፓ እና አሜሪካ ገዝቶ ወደ ጣና ልኳል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ማሽን ሰርቷል። ባሕር ዳር ውስጥ ሙላት የተባሉ ግለሰብ የሰሩትን ማሽን ጨምሮ ቁጥራቸው ስድስት የሆኑ ማሽኖች እምቦጭን ለማጨድ ተዘጋጅተዋል።
ፌደራሉ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአረሙ ማስወገጃ ማሽን ለመግዛት 300 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ ስልጣን በመጡ በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥም ወደ ስፍራው በማምራት አረሙ በሃይቁ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ተመልክተው ለአካባቢው አርሶ አደሮች “እምቦጭን እናጠፋዋለን” የሚል ተስፋ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
ታዲያ እምቦጭን እስካሁን ለምን ማጥፋት ሳይቻል ቀረ?
የጣና ሀይቅ፣ በመጤ አረም መወረሩ ከታወቀ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ መጤ አረሙ ሀይቁን መውረሩ የታወቀው በ2004 ዓ.ም ነበር። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሀይቁን ከዚህ ወራሪ አረም ለመታደግ አልፎ አልፎ ዘመቻዎች ቢደረጉም፣ እምቦጩ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የሀይቁን መግቢያ በሮች ጥቅጥቅ አድርጎ ዘግቷል። በተለይ በሃይቁ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኙት የፎገራ፣ ሊቦከምከም፣ ጎንደር ዙሪያና ደምቢያ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ለም መሬት ያላቸውና በሀይቁ ዳርቻ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች የሚመረትባቸው ናቸው። የአካባቢው ነዋሪም ከአሳ ማስገር ጀምሮ የተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታዎችን ከሀይቁ በማግኘት ኑሮን ይመራ ነበር። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኑሯቸው የተመሰረተው በጣና ሃይቅ ዙሪያ ነው።
ዶ/ር አብዩ ዋሌ አለም አቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ውስጥ የማናጅመንት አባል ሲሆኑ በእምቦጭ ዙሪያ የተለያዩ ምርምሮችን ሰርተዋል።
የዶ/ሩ ጥናት እንደሚያመለክተው በፈረንጆቹ 2017 ከመስከረም አስከ ህዳር ባሉት ወራት ብቻ አረሙ በቀን 14 ሄክታርን ይወር ነበር።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 385 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው አጠቃላይ የጣና ዙሪያ እስከ 120 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሀይቁ ጠርዝ በእምቦጭ ተሸፍኗል።
በእነዚህ አካባቢዎች በቀላሉ ወደ ሀይቁ መግባት የማይታሰብ ነው። በመሆኑም በሃይቁ ጫፍ አካባቢ እየኖሩ ከጣና፣ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሚያገኙ ግለሰቦች መካከል በ120 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሰፈሩት ነዋሪዎች ከጣና ሀይቅ ጋር እንዳይገናኙ አረሙ ከልክሏቸዋል።

እምቦጭ ለምን አልጠፋም?
እምቦጭ በ2004 ዓ.ም ሃይቁን መውረሩ ከታወቀ በኋላ የመጀመሪያው የመከላከያ መንገድ ተደርጎ የተወሰደው በሰው ኃይል በማስወገድ ከሃይቁ ውጭ እያወጡ መከመርና ማድረቅ ነው።
ይህ አሁን ድረስ ቀዳሚ መፍትሄ ተደርጎ የሚሰራበት የእምቦጭ አረም መከላከያ መንገድ ነው። ቢሆንም ግን በዚህ መንገድ እምቦጭን ለማጥፋት የተሰሩት ሥራዎች በአካባቢው የሚኖረው አርሶ አደር የሚናፍቀውን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።
የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ለዚህ ዋነኛው “የመቀናጀት ችግር ነው” ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ በጉዳዩ ላይ ያገባናል የሚሉ አካላት ለሀይቁ ህልውና መፍትሄ ነው የሚሉትን የመፍትሄ ሃሳብ በግል ከመያዝ ባለፈ በጋራ የተመከረበት ጥቅልና ሁሉም ሊከተለው የሚችለው ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አልተቻለም ባይ ናቸው።
የዶ/ር አያሌው መሥሪያ ቤት ከመቋቋሙ በፊት ይህን ሥራ በዋናነት ይመራ የነበረው የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ነበር። ይሁንና በሀይቁ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ሌሎች በጎ አድራጊና መንግሥታዊ ተቋማትም ተሳታፊ ነበሩ።
መቀመጫውን በአሜሪካን አገር ያደረገውና በዶ/ር ሰለሞን ክብረት የሚመራው “አለም ዓቀፍ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ” አረሙ ሊወገድ የሚችልበትን የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትና የአረሙ ማስወገጃ ማሽን ገዝቶ በማበርከት ቀዳሚ ተሳታፊ ነው።
ማህበሩ ሰሞኑን በ5.8 ሚሊዮን ብር ገዛሁት ያለውን ሁለተኛውን የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን ባሀር ዳር አድርሶ ለክልሉ መንግሥት አስረክቧል። ይህ ማሽን 28 ሜትር ኪዩብ አረም በአንዴ ማረምና መሸከም የሚችል ሲሆን 75 የፈረስ ጉልበትም አለው ተብሏል።
አለም ዓቀፍ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር በውጭ ሃገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተ የበጎ አድራጎት ማህበር ሲሆን፣ አባላቱም በነጻ ለሃገራቸው ድጋፍ ለማድረግ የተሰባሰቡ በአካባቢ ጥበቃና ውሃ አያያዝ ዙርያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በጎ ፍቃደኞች ናቸው።
ማህበሩ ሌላ የእምቦጭ ማጨጃ ማሽን በካናዳ አሰርቶ የጨረሰ ሲሆን ሰሞኑንም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ ገልጿል።
የባህርዳርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎችም በሀይቁ ላይ ሥራ ከሚሰሩ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ናቸው። ይሁንና ሁሉም በየራሳቸው መንገድ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከመጣራቸው ባለፈ በአንድ የአሰራር ሰንሰለት የታሰሩ አልነበሩም።
ይህንን ችግር ለመፍታት ባለፈው ዓመት የአማራ ክልል መንግሥት “የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲን” አቋቁሟል። በአረሙ አወጋገድ ላይ በተለይ በደምቢያ ወረዳ ምርምር ያደርጉ የነበሩት ዶ/ር አያሌው ወንዴ ይህንን ተቋም እንዲመሩ ተደርጓል። አሁንም ግን ችግሩ አልተቀረፈም። ይህ የሆነበትን ምክንያትም “የተለያየ ሃሳብ በመኖሩ ነው” ይላሉ ዶ/ር አያሌው።
በሌላ በኩል ዶ/ር ሰለሞን የክልሉ መንግሥት በቂ ትኩረት አለመስጠቱ ችግሩ እንዳይፈታ ማድረጉን ይገልጻሉ። የጣና ጉዳይ ለክልሉ መንግሥት “የህዝብ ጥያቄ ትኩሳት ሲያቃጥለው ብቻ የሚያነሳው አጀንዳ መሆን የለበትም” የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን፣ “ብዙ ባለሙያዎች ተሳትፈውበት የተዘጋጀ የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ አለ፤ ፍኖተ ካርታው ሀይቁን ከተጋረጠበት ችግር ለመታደግ መሠራት ያለባቸውን ዝርዝር ሥራዎችና ስትራቴጂዎች አስቀምጧል። ይህን ለመተግበር የሚያስፈልገውን ሃብትና መዋቅር በእያንዳንዱ የሃይቁ ቀበሌ ይዘርጋ” በማለት የክልሉን መንግሥት ይመክራሉ።
ጣናን ይታደጋል ተብሎ የተቋቋመውን መሥሪያ ቤት የሚመሩት ዶ/ር አያሌው ወንዴ ደግሞ “የተለያየ ሃሳብ መጥቷል፤ ለውጥ ግን አልመጣም” በማለት እስካሁን የነበረው እምቦጭን የማስወገድ ዘመቻ ውጤቱ እምብዛም መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም ከክልል እስከ ፌደራል የሚገኙ በጣና ጉዳይ የሚያገባቸው ተቋማት “ቅንጅት ፈጥረን ሁላችንም ድርሻችንን እንውሰድ” የሚል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት እምቦጭን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች በስፋት መሰራት ጀምረው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ የመከላከል ስራውን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ ማሰባሰብ ስራ ይገኝበታል።
ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮችን ማረጋገጥ እንደቻለው ለዚሁ ተግባር ተብሎ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ከግለሰቦችና ተቋማት ተሰብስቧል። የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው “አሁን ላይ የፋይናንስ ችግር የለብንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከአሁን በኋላም አረሙን የማስወገድ ስራ በክፍያ አርሶ አደሩን ለማሰራት ማቀዳቸውን አብራርተዋል።
የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ይረዳሉ ተብለው የተለያዩ ማሽኖች በስጦታ ቢቀርቡም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀይቁ የገቡ ብዙዎቹ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም።
ለምን አገልግሎታቸው እንደተቋረጠ የተጠየቁት ዶ/ር አያሌው “ሲበላሹ የምንጠግንበት ጋራጅ የለንም፣ የአቅም ማነስ አለብን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ማሽኑን ያበረከቱት አካላት ማሽኑ እንደሚሰራ ቢያረጋግጡም የእነ ዶ/ር አያሌው መስሪያ ቤት ግን በማሽኖቹ መሥራት ላይ እምነት የለውም። በመሆኑም በሁለቱ አካላት ላይ ያልተቋጨ ስምምነት መኖሩን ዶ/ር አያሌው ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር አያሌው መረጃ ከሆነ በዚህ ወቅት በሀይቁ ላይ ያለው የእምቦጭ አረም መጠን 900 ሄክታር አካባቢ የሸፈነ ነው። ይህን በመንቀል ለማጥፋት ወይም ስርጭቱን ለመግታትና ለማዳከም 10 አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል። በዋናነት በክፍያ አርሶ አደሩን ማሰራት የሚለው አማራጭ እንዳለ ሆኖ እምቦጭ ያለበትን አካባቢ አጥሮ ማቆየት፣ ያሉት ማጨጃ ማሽኖችን መጠቀምና ሌሎች ጀልባዎችን በመከራየት አረሙን ማስወገድ የሚሉት መፍትሄዎች መቀመጣቸውንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የአለም ዓቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ዶ/ር ሰለሞን ክብረት “እንቦጭ አረም ለጣና ሃይቅ ከተደቀኑ ችግሮች አንዱ እንጅ ብቸኛው አይደለም” ይላሉ። በመሆኑም ጣና ሃይቅን በዘላቂነት ለመታደግ “የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን መሥራት፣ የአፈር መሸርሸርን መቀነስና ከተሞች ወደ ሀይቁ የሚለቁትን ፍሳሽ አጣርተው እንዲለቁ ግዴታ ማስቀመጥ” የሚሉት ዋነኛ የሀይቁን ደኅንነት ማስጠበቂያ መሣሪያዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።