By ዘ-ሐበሻ
August 31, 2020
በንጉስ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንግስታዊ ሃይማኖት ነበረች ።የደርግ መንግስት ሲመጣ ደግሞ የዕምነት ዕኩልነትን ያረጋገጠ ቢሆንም ፥ከእግዚአብሄር በላይ ሌኒንና ማርክስ እንዲመለኩ መትጋቱም ግልጽ ነበር።እርግጥ ነው ያኔ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በሚባል ደረጃ ኢሕአፓም ሆነ መኢሶን ሕወሓትም ሆነ ኦነግ ሁሉም የሰማዩን አምላክ የካዱ ለምድሩ ሌኒን የሰገዱ ነበሩ።
በ1983 ሕወሓት የሚመራው ኢሕአዴግ ደርግን ጥሎ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት ሥልጣን ሲቆጣጠር የዕምነት ተቋማት ይበልጥ ነጻነታቸው የተረጋገጠበት ሁኔታ ቢፈጠርም ፥በመንግስት ግልጽ ጣልቃ ገብነት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ከመንበራቸው እንዲነሱና እንዲሰደዱ ተደረገ ።አቡነ ጳውሎስ ከስደት ተመልሰው ፓትርያርክ የሆኑት ፥ አቡነ መርቆርዮስም የተነሱት በመንግስት ግልጽ ጣልቃ ገብነትና ውሳኔ መሆኑን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ጭምር በድምጽና በምስል አረጋግጠዋል።ይህ ዕውነታ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስጢር ማህደር ውስጥ ጭምር ተመዝግቧል።
የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች ሁለት ቦታ የከፈለው የመንግስት ጣልቃ ገብነት እና የተከተለው ውጥንቅጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአማኞቿ ቁጥር እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል።
በደርግ ዘመነ መንግስት በ1976 በተካሄደ የሕዝብ ቆጠራ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 54.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ቁጥር በ23 ዓመታት ግዜ ማለትም እስከ1999 ከ10 በመቶ በላይ ቀንሶ 43.5 በመቶ ወርዷል።ባለፉት 13 ዓመታት ቆጠራ ባለመካሄዱ ዛሬ የቤተክርስቲያኒቱ አማኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እርግጡን መናገር አይቻልም።
ቤተክርስቲያኒቱ ባለፉት 30 ዓመታት በከፍተኛ መከራ ውስጥ አልፋለች። በሕወሃት /ኢሕአዴግ የመጀመሪያ ዓመታት ከሰኔ 83 እስከ ግንቦት 1984 በአርሲ አርባ ጉጉ በ6 ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ እና የቤተክርስቲያናት ቃጠሎ በብዛቱ ብቻም ሳይሆን አሰቃቂነቱ እስከዛሬ አቻ አልተገኘለትም።በጎንደር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን 13 ምዕመናን በመንግስት ታጣቂዎች የተገደሉበት ጭፍጨፋ እንዲሁም በ1998 በጅማ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ እና ቃጠሎ ተጠቃሽ የ27 ዓመታት የቤተክርስቲያኒቱ ሰቆቃዎች ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማም ከቅዱስ ዮሃንስ ፥ከቅዱስ እስጢፋኖስ እና ከቅድስት ልደታ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን በጅምላ ታፍሰውና ተቀጥቅጠው ወደ ኮልፌ ፖሊስ ማሰለጠኛ የተጋዙበት እና እነ ባሕታዊ ፈቃደ ሥላሴ የተገደሉበት ሁኔታ በቤተክርስቲያኒቱ አማኞች ፈጽሞ የማይረሱ መራር ትወስታዎች ናቸው።
5 የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳሳት ሃምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም በምሽት በተመሳሳይ ሰዓት በየመኖርያ ቤታቸው የተሰነዘረባቸው ጥቃት እና ተጠያቂ አለመኖሩ ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ከተፈጸሙ የማዳከም እና የማዋረድ ርምጃዎች ተጠቃሹ ነው።
እነዚህ ሰቆቃዎች በቤተክርስቲያኒቱ፥በአባቶች እና ምዕምናን ላይ ሲፈጸሙ፣ ታሪካዊው እና መንፈሳዎው ዋልድባ ገዳም ጭምር ሲታረስ ስለ ቤተክርስቲያኒቱና ስለምዕመናንዋ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ያላየናቸው ይልቁንም ፍርሃታቸውን እና ጥቅመኛነታቸውን ለመሸፈን ” እግዚአብሄር ያመጣውን እግዚአብሄር ይመልሰው ” ሲሉ የነበሩ ዛሬ መሬት ለምን እንደጠበባቸውም ይገባናል፣መቼ እንደሚደበቁም አይጠፋንም።እነዚህ ወገኖች ከራሳቸውም አልፈው ስለሃገራቸው እና ቤተክርስቲያናቸው ድምጻቸውን የሚያሰሙትን ሲገስጹ እንዳልነበር ዛሬ የቤተክርስቲያኒቱ ጠበቃ፥ የምዕመናኖቿ ተሟጋች ነን ሲሉ ትናንት ለምን ፈራችሁ ማለት ተገቢ ባይሆንም፣ ከዕምነት አልባዎች ጋር ግንባር ፈጥረው ቤተክርስቲያኒቱን የፖለቲካ መድረክ እንዲያደርጉ ግን ሊፈቀድላቸው አይገባም።
በብሄር ወይንም በሰፈር መብት ተሟጋችነት ሽፋን ሃገርን ወደ ቀውስ ለመውሰድ ተወራጭተው ጉዟቸው በኪሳራ የተደመደመባቸው ወገኖች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ተንጠላጥለውና ፣ቤተክርስቲያኒቱን 27 ዓመታት ከቀጠቀጠ ቡድን ጋር አብረው የንጹሃንን ሕይወት ለመገበር እየተጣደፉ አለመሆኑን ማረጋገጥ ከሁሉም በላይ የአባቶች እና የምዕመናን ጭምር ሃላፊነት ነው። በመከራ ውስጥ ያለፉትንና ከሰቆቃ ውስጥ ያልወጡትን ምዕመናን ምንም የሚታደጉበት አቅም ሳይኖራቸው በ14 ሺህ ኪሎ ሜትር ላይ ሆነው የሚፎክሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሰለባዎቹን ለሌላ አደጋ እያጋለጡ በመሆናቸው ከዚህ ሃላፊነት የጎደለው የጭካኔ ቅስቀሳ እንዲታቀቡ ማሳሰቡም ተገቢ ነው።
በጥላቻ ናላቸው የዞረ የተደራጁ ቡድኖች እና ያልተደራጁ ግለሰቦች ባሉበት እና ባልከሰሙበት በመከራ ውስጥ ላለው ሕዝብ ዋስትናው የሕግ የበላይነት መከበር ሲሆን፥ ሕግና ሥርዓት የሚከበረው ደግሞ ጠንካራ መንግስት መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። . . . ንጹሃኑን ላትታደጉ ከሩቅ የምትፎክሩ ቤተሰቦቻችሁና የቅርብ ዘመዶቻችሁ ቢሆኑ ኖሮ ይህን ሃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ ታደርጉ ነበርን ? እባካችሁ ከገዳዮች እና ዘራፊዎች ጥቃት የማታድኑትን ሕዝብ ቢያንስ ከሚሸሽገው ወገኑ ከጎረቤቱና ወንድሙ ጋር አታጣሉት!
ነሃሴ 24/2012 (August 30/2020)