September 3, 2020Konjit Sitotaw

‹‹አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር መሞከሯ በሞራልም በዲፕሎማሲም አግባብነት የሌለው ነው›› ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በአ.አ.ዩ. የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ

(ኢፕድ) አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ አማካይነት ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የገለጸችው ጉዳይ በሞራልም በዲፕሎማሲም አግባብነት የሌለው መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ፡፡ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ውሃ ሙሌት ምክንያት ያጋጥመናል በማለት ያሰጋቸው የውሃ እጥረት ሳይከሰት ቀርቶ የተጥለቀለቀ ውሃ ማግኘታቸውንም አመለከቱ።

የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በተለይ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ

እንደተናገሩት፤ አሜሪካ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ በተገባው ውለታ መሰረት ለአንዳንድ አስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች የምታደርገውን ፈሰስ ለማቋረጥ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል መግለጫ ሰጥታለች። አሜሪካ የምታደርገው የገንዘብ ወጪ የሚውለው ለኢትዮጵያም ለአሜሪካም የጋራ ጥቅም ነው። በተለይም ለአካባቢ ደህንነት ሁለቱ አገሮች የሚተባበሩበት የቆየ አይነት ስምምነትና አሰራር ላይ የሚውል ገንዘብ በመሆኑ የገንዘብ ፈሰሱን አቋርጣለሁ ስትል የገለጸችው ጉዳይ በሞራልም በዲፕሎማሲም አግባብነትም ተቀባይነትም የሌለው ነው።

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ የአሜሪካ አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ካለፈው ጥቅምት እና ህዳር ወር ጀምሮ አግባብ ባለው መግባባት ጉዳያችሁን በተመልካችነት ልይላችሁ ሲል ቆይቷል። ስትወያዩ ተመልካች እሆናለሁ ማለት የተለመደና የጨዋነት እንዲሁም የወዳጅነት ሐሳብ ነው በሚል ሐሳቡን ሶስቱም አገራት ተቀብለው እስካለፈው የካቲት ወር ድረስ ሲወያዩ እንደነበር አመልክተዋል።

ይሁንና አሜሪካ ቀስ በቀስ ውግንናዋን ወደግብጽ እያደረገች ስትመጣ ኢትዮጵያ ሁኔታው ሚዛኑን የሳተ መሆኑን በመረዳት ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ ላለመስጠት መወሰኗ የሚታወስ እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይ የግብጽን የቆየና ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ በፊርማ እንዲረጋገጥ አሜሪካ ግፊት ማድረጓ ስለተረጋገጠም ኢትዮጵያ ከውይይቱ የወጣችበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል ብለዋል። በወቅቱ አሜሪካ ራሷን ከተመልካችነት ወደ አደራዳሪነት አሸጋግራ ሰነድ በማዘጋጀት ፈርሙ በማለት ልካ እንደነበርም ተመራማሪው አስታውሰዋል። አካሄዱ ተቀባይነትን አለማግኘቱንም አመልክተዋል።–እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አሁን ባለንበት ደረጃ ግብጽ እና አሜሪካ ጉዳዩ ወደዓለም መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሄድ የገፉ ቢሆንም መድረኩ ግን የጸጥታን ጉዳይ በተለይም አገሮች በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የከፋ ሁኔታ ላይ ሲገቡ ጉዳዩን የሚመለከት የዓለም መንግስታት አሰራር እንጂ ሶስቱ አገሮች በግድብ አሞላል ብሎም በግድብ ስራና ውሃ ልማት ስራ እየገባ ጉዳዩን መመልከት ያልተለመደና አዲስ ነገር እና ለወደፊቱም ቢሆን የሚያዋጣ አለመሆኑን ኢትዮጵያ አበክራ አስገንዝባ፣ የጸጥታ ምክር ቤቱም በአብላጫ ቁጥር ይህንኑ ተቀብሎ ኢትዮጵያ በጠየቀችው መሰረት የአፍሪካ ህብረት የበላይ ተመልካች ሆኖ ስለህዳሴ ግድብ መወያየት ከተጀመረ ውሎ አድሯል። ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮም በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።

እየተካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር ስለ ውሃ ሙሌቱና ስለ ዓመታዊ የግድቡ አያያዝና አስተዳደር ነው። ግብጾችም ሆኑ ሱዳኖች እንዲሁም የአሜሪካ አስተዳደር በፊት ወደነበረውና የእነሱ ስምምነት እንዲገባ ውትወታቸውን ቀጥለው ቢገፉም በኢትዮጵያ በኩል የማይሆን ነገር መሆኑን በደንብ ምክንያታዊ በሆነ ማስረጃና ውይይት ልክ አለመሆኑ እየተገለጸላቸው እስካለፈው ሳምንት በዚህ አይነት ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብጽ፣ አሁንም በአፍሪካ ህብረት መድረክም ቢሆን ቀደም ሲል የነበረውን ለማሟላት ስትጥር ይስተዋላል። እርሷ የምትፈልገው ነገር የማይቻልና ተገቢ እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ስታስገነዝብ መቆየቷን አስታውሰው፤ ድርድሩ በዚህ የልዩነት ደረጃ ላይ እንዳለ ጠቁመዋል።

አሜሪካ፣ ስምምነቱን በፍጥነት እሷ ቀደም ሲል ባሳሰበችው እንደዚሁም ግብጽ ተጎዳሁ በማትልበት መንገድ ካላደረጋችሁ እና የግብጾችን ፍላጎት አላሟላችሁም በሚል ምክንያት በየዓመቱ በተገባው ውለታ መሰረት የሚደረገውን ወጪ ለማቋረጥ መነሳሳቷን ጠቅሰው ፤ አሜሪካ የምታደርገው ወጪ የሚውለው ለኢትዮጵያ ብሎም ለአሜሪካም ጭምር መሆኑን ፤ በተለይም ለአካባቢ ደህንነት ሁለቱ አገሮች የሚተባበሩበት የቆየአይነት ስምምነትና አሰራር ላይ የሚውል ገንዘብ እንደሆነ ገልጸዋል።

በጨዋ ደንብ የተስማሙበት ፈሰስ እንደ ነበር የተናገሩት ፕሮፌሰር ያዕቆብ፣ እሱን ሊያቆሙ እንደሚችሉ መግለጫ መስጠታቸው ተገቢ አካሄድ አለመሆኑን ገልጸዋል። ይህንን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ልክ አለመሆኑን በሚገባ እንደሚያስረዳቸውም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

ዋናው ነገር ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የመተባበር ልምድ ያላቸው አገሮች ናቸው ያሉት ተመራማሪው፣ ኢትዮጵያ ግድቡን በምትገነባበት ጊዜና ግድቡን አልምታ ለልማት በምታውልበት ጊዜ በመጀመሪያ ደረጃ አሜሪካንንም ሆነ ግብጽና ሱዳናን የሚጎዳ ምንም ነገር አለመኖሩን አረጋግጠዋል። ግድቡ በጥንቃቄ እየተሰራ ያለ ስለሆነ አሜሪካ ለግብጽና ሱዳን ወግና ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሄራዊ ልማቷን እና አገራዊ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ሌሎቹን ጉዳት ላይ ሳትጥል ስትራመድ የቆየች አገር እንደሆነችም አስታውሰዋል። አሁንም ከዚህ ውጭ ሌላ ያቀደችው ነገር የለም ሲሉ ጠቅሰው፤ የምትፈራም ነገር አለመኖሩንም ገልጸዋል። ማንም የኢትዮጵያን እጅ ጠምዝዞ ብሄራዊ ጥቅምንና አገራዊ ሉዓላዊነቷን በሚጎዳና ልማቷን ለማስተጓጎል ቢሞከር መንግስትም ሆነ ዜጋው የሚቀበለው ነገር እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፣ ዘንድሮ ግብጽና ሱዳን ለወደፊትም ቢሆን የውሃ እጥረት ያጋጥማቸዋል ተብሎ አይታሰብም ሲሉ ጠቅሰው፤ ምክንያቱም የውሃ ሙሌት በኢትዮጵያ በኩል በጥሩ ዲዛይን ላይ የተመሰረተ እና ድርቅ እንኳን ቢያጋጥም ግድቡን መሙላት የማዘግየት እድል በመኖሩ ለእነሱ የከፋ ጉዳት እንዳያመጣ ተብሎ የታሰበ መንገድ ነው ብለዋል። ስለሆነ የዘንድሮ ዝናብ በርከት ማለቱ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ቢሆን የውሃ እጥረት እና በኢትዮጵያ ግድብ ምክንያት የሚያጋጥማቸው አለመሆኑ አስቀድሞም በደንብ የተመዘነ እና በዲዛይኑ ውስጥ ያለ መሆኑንም አመልክተዋል።

ቀድሞውንም ቢሆን ማንንም ጉዳት ላይ ለመጣል የታሰበ ነገር አለመኖሩን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ከጀመረች ውሃ ያጥረናል በሚል በምናብ ሲታሰብ የነበረው የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ነው እንጂ አገራቱ በትክክል ውሃው ይቀንስብናል በማለት ያጠኑት አሊያም የቀመሩት ሳይንሳዊ የሆነ ውጤት አልነበራቸውም ብለዋል።

እርሳቸው በቂ ውሃ ከማግኘት ባለፈ እንዲያውም በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ናቸው። ትንንሽ በበረሃ አሸዋ የሰሯቸው ግድቦቻቸው አንዳንድ ቦታ በውሃ ብዛት የተነሳ መፍረሳቸውን አመልክተዋል ።