3 መስከረም 2020, 17:47 EAT

በእስር ቤቱ በተስፋፋው የቆዳ በሽታ ብዙዎቹ ተጠቅተዋል
የምስሉ መግለጫ,በእስር ቤቱ በተስፋፋው የቆዳ በሽታ ብዙዎቹ ተጠቅተዋል

በሳዑዲ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች መካከል 2 ሺዎቹን የመመለስ ስራ ከአምስት ቀናት በኋላ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አስታውቋል።

በአሁኑ ሰዓትም 2 ሺህ ስደተኛ ዜጎች ዝርዝር እንደተለየና የመመለሱም ስራ ከጳጉሜ ሶስት- እስከ መስከረም 26 ይከናወናል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንንም ቅድሚያ በመስጠት እንደሚከናወንም ተገልጿል።

በተለያየ ጊዜ ስደተኞችን የመመለስ ስራ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢሰራም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ጫና እንዳሳረፈ መግለጫው ጠቁሟል።

በዚህም ችግርም ውስጥ ተሁኖ 3 ሺህ 500 የሚሆኑ ስደተኞችን በመመለስ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ወደመጡበት ስፍራም የመላክ ስራ ተሰርቷል ብሏል በመግለጫው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ለሳዑዲ መንግሥት ከወር በፊት በፃፉት ደብዳቤ ዜጎቹን ከሳዑዲ አረቢያ በአየር አንስቶ ወደ መቀሌ እንዲያደርስላቸው ጠይቀዋል።

ደብዳቤው የኢትዮጵያና የሳዑዲ ከጥንት ጀምሮ ያላቸውን የተሳሳረ ታሪክ እንዲሁም በትግራይ ያለውን አል ነጃሺ መስጂድ ለዚህም ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ትብብር ያስፈልጋል ብሏል።

ለዘመናት በተለይም በደርግ አገዛዝ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሸሻ አድርገው ሳዑዲ አረቢያን እንደቆዩና ከድህነት፣ ረሃብም ሆነ የተሻለ ኑሮን የፈለጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ እንደ ሁለተኛ አገራቸው ሆና ቆይታለች ብለዋል።

በቅርብ አመታትም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከትግራይ ክልል ቀይባህርን አቋርጠው የመንን በመሻገር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሻግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ስደተኞች የሚያዙበት ሁኔታ እንደተቀየረ የገለፀው ደብዳቤው በርካታዎቹ ከትግራይ ክልል መሆናቸውን አስምሯል።

“የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት በማያሳምን መልኩ ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም” ያለው ደብዳቤ ክልሉ ዜጎቹን ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆነም አትቷል።

የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹን መቀሌ በሚገኘው አሉላ አባ ነጋ አለም አቀፍ አየር መንገድ እንዲያደርሳቸውም ጠይቋል። ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነ ከኮሮናቫይረሰ መጠበቅ ይቻል ዘንድ የተሟላ አቅርቦት ወዳሏቸው የስደተኛ መጠለያዎች የሳዑዲ መንግሥት አንዲያስገባቸው ጠይቋል።

ከሰሞኑ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኢ-ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ በእስር ቤት ታጉረው ለተለያዩ በሽታዎችና ሞቶች መዳረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ከሰሞኑ የእንግሊዙ ጋዜጣ ቴሌግራፍ ታሳሪዎቹ በስልካቸው ከላኳቸው ፎቶዎች መካከል ከመስኮት ላይ ራሱን የገደለ ግለሰብና በብርድ ልብስ የተጠቀለለ አስከሬን መታየቱ ስደተኞቹ ያሉበትን ሰቆቃ አስደንጋጭ አድርጎታል።

ያሉበት መከራና ስቃይ የምድር ሲኦል የሆነባቸው እነዚህ ስደተኞች ራሳቸውን ለማጥፋት የተገደዱና በመተፋፈጋቸውም ሞተዋል ተብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች ምግብ፣ ውሃ እጥረትና ከሰው በታች ሆነው ህይወታቸውን ለመግፋት በመገደዳቸው ስቃያቸውን ለመግለፅ ቃል አጥተዋል። በስቃይ ያሉት ሰደተኞች ለባለፉት ስድስት ወራት በዚህ መልኩ ያሳለፉ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሳዑዲ መንግሥት ከነመኖራቸው እንደረሳቸው በምሬት ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ ወደ እስር ቤቱ መጥቶ እንዳናገራቸውና መንግሥት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽላቸውም ምንም ነገር ሳይሰሙ በመከራ ኑሯቸውን ለመግፋት እንደተገደዱ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ከሰው በታች በሆነ ሁኔታ ስደተኞቹ መያዛቸው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ውግዘትን ፈጥሯል ከሳዑዲ መንግሥት በኩል በመንግሥት በሚተዳደሩት እስር ቤቶች ውስጥ በሙሉ ስላለው ሁኔታ ምርመራ” እያደረገ መሆኑን ገልጾ “በእርግጥም አስፈላጊው ነገሮች የተጓደለ ሆኖ ከተገኘ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል” ሲል ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የትኛውም አገር ያሉ ስደተኛ ዜጎቹን አልቀበልም ብላ እንደማታውቅና ነገር ግን አቀባበሉ አስፈላጊውን አቅምን በተከተለ መርህ ነው ብሏል።

በባለፉት ሶስት አመታትም ከ40 ሺ በላይ ዜጎቿን ከሳኡዲ አረቢያ እንደተቀበለችም ለዚህም ማሳያ ነው ነው ብሏል።

ስደተኞቹን ለመመለስ የተለያዩ ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመጣመር የስደተኞቹን ማንነት የመለየት፣ ዜግነትን የማረጋጋጥ፣ ትራንስፖርትን ጨምሮ ከተመለሱም በኋላ የስነ ልቦና ድጋፍ፣ ራሳቸውን ማስቻልና ከህብረተሰቡ ጋር የመቀላለቀል ስራም አስፈላጊነቱን አስምሯል።

በቤይሩት ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት በመስራቷ አገሪቷ ውጤታማ መሆኗን የጠቀሰው መግለጫው በአሁኑ ሰዓትም በየመን ከተባበሩት መንግሥታት ጋር እንዲሁም ከሳኡዲ መንግሥት ጋር እየሰሩ መሆኑን አስፍሯል።

በተለይም ከየመን ድንበር ተሻግረው ወደ ሳዑዲ አረቢያ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች መንገድ ከፍተኛ ገፈት እየቀመሱ ሲሆን ቁጥሩም በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም ሳዑዲ እነዚህን ስደተኞችን ከመቀበል ችላ እንዳላለችና የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ምስጋናውን ችሯል።

በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክም እነዚህን እስር ቤቶች ሁኔታ የሚጎበኝና የሚቆጣጠሩ ሰራተኞች በቋሚነት እንዳሰማራ ጠቅሷል።

የሰዎች ህገ ወጥ ዝውውርና መመለስ የተወሳሰበ ሂደት ከመሆኑ አንፃር ስደተኞችን መመለስ ብቻ ሳይሆን ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መሆኑ፣ ዘላቂ በሆነ ሁኔታ በአገር ውስጥ የሚኖሩበትንና ከህዝቡ ጋር ተመልሰው የሚቋቋሙበት መንገድ መፈለግ እንደሚያስፈልግም አስምሯል።

ስደተኞችን ወደ አገር ቤት የመመለሱ ሥራው የተለያዩ የፌደራል ሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን፣ ኤምባሲዎችን እና የክልል ቢሮዎችን በቅንጅት የሚሰሩት ነው ብሏል።