3 መስከረም 2020, 13:05 EAT

አሜሪካ

የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) የአሜሪካ ግዛቶች የጤና ኃላፊዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ቀድሞ የሚታደልበት አማራጭ ላይ ቀድመው እንዲዘጋጁ ማሳሰቡ ተነገረ።

ሲዲሲ ትናንት በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍ ላይ ክትባቱ ለበሽታው የበለጠ ተጋለጭ ለሆኑ ሰዎች እስከ ጥቅምት አጋማሽ ሊሰራጭ እንደሚችል ጠቁሟል።

“ሲዲሲ ግዛቶች ቀድመው እንዲዘጋጁ በማሰብ ዝግጁ ሊሆን የሚችል የክትባት መጠን እና ጊዜን ለግዛቶች አሳውቋል።

ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ሕዳር መጨረሻ ድረስ መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንም የክትባት ስርጭት ሊኖር ይችላል” ሲሉ የሲዲሲ ቃል አቀባይ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

ኒው ዮርክ ታይመስ ደግሞ ቀደም ሲል ሲዲሲ ከሁሉም 50 የአሜሪካ ግዛቶች እና አምስት ግዙፍ ከተሞች ከስርጭት ጋር ተያይዞ ያሉ የእቅድ መረጃዎችን ጠይቋል።

በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ላይ ሲዲሲ ጥቅምት አጋማሽ ላይ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ አንድ ወይም ሁለት የኮቪድ-19 ክትባቶች ለስርጭት ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁሟል።

ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ እንደ የጤና ባለሙያዎች፣ ለደህንነት ሰራተኞች እና እድሜያቸው የገፉ ሰዎችን የሚንከባከቡ ነርሶች እና ባልደረቦች ክትባቱ ያለ ክፍያ ይሰጣቸዋል ይላል የሲዲሲው ዶክመንት።

የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያው ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ ለኤምኤስኤንቢሲ ቴሌቪዥን ትናንት ሲናገሩ፤ ለኮቪድ-19 ክትባት ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥርን ከግምት በማስገባት እስከ ሕዳር ወር ድረስ የትኛው የኮቪድ-19 ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ እንደሚሆን መለየት ይቻላል ብለዋል።

ሞደርና፣ አስትራዜኔካ እና ፐፊዘር የተሰኙ መድሃኒት አምራቾች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ የሆነ የኮቪድ-19 ክትባት ለማዘጋጀት ጥረት ላይ ይገኛሉ።