4 መስከረም 2020, 17:09 EAT

በጋምቤላ ክልል እስካሁን 863 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የሰባት ሰዎች ሕይወት አልፏል። የቫይረሱ ስርጭት አሁንም አልተገታም።
ከሳምንታት ወዲህ ግን ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች የኮቪድ- 19 ዕለታዊ ሪፖርቶችን በመደበኛነት አያወጣም።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንድምአገኘሁ በላይነህ እንደሚሉት፤ የክልሉ የኮሮናቫይረስ ዕለታዊ መረጃ እንደሌሎች ክልሎች እየወጣ አይደለም።
“የናሙና ምርመራ ውጤት ቀጥታ ለኮሚዩኒኬሽን ክፍል አይላክም። የኢመርጀንሲ ኦፕሬሽን ሴንተር ከተላከ በኋላ ነው ወደ ኮሚዩኒኬሽን የሚልኩት። በየቀኑ መረጃ መውጣት እንዳለበት ተማምነናል። በየቀኑ አለመውጣቱ ሰውን ያዘናጋል” ሲሉ ክፍተቱን ለመሸፈን እየሠሩ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በየቀኑ ውጤት እየወጣ አይሁን እንጂ ምርመራ ግን እንዳልተቋረጠ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ከገባ ወዲህ የዛሬ አርብ ነሐሴ 29/2012 መረጃን ሳያካትት ለ970 ሺህ 591 ናሙናዎች ምርመራ አድርጋለች።
በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 55 ሺህ 213 ደርሷል። ከእነዚህ መካከል 20 ሺህ 283 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸው ተገልጿል። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 856 ደርሷል። ይህ መረጃ የአርብ ነሐሴ 29 ቁጥርን ያካተተ አይደለም።
- በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ
- በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ20 በላይ ተለማማጅ ሐኪሞች በኮሮናቫይረስ ተያዙ
- በሚሊኒየም አዳራሽ የሚገኘው የኮቪድ-19 ጽኑ ህሙማን ክፍል እየሞላ ነው
ቀደም ሲል በክልሉ በቀን እስከ 90 የናሙና ምርመራ እንደሚደረግና አሁን ግን በክልሉ 13 ወረዎች ወደ 1 ሺህ ናሙና ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ አቶ ወንድምአገኘሁ ተናግረዋል።
በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ንብረት የሆነ አንድ የምርመራ ማዕከል ብቻ እንዳለ አቶ ወንምአገኘሁ ይናገራሉ።
ከቀናት በፊት የትግራይ ክልል ምርመራ መቀነሱን በማስመልከት ለፌዴራል መንግሥት ቅሬታ ማሰማቱ አይዘነጋም። ክልሉ የፌዴራል መንግሥት ለኮቪድ-19 ምርመራ ለሚውል ሶፍትዌር መክፈል የነበረበትን ገንዘብ ስላልከፈለ ነው ምርመራ የቀነሰው ብሎ ነው ቅሬታ ያሰማው።
ምንም እንኳ ቅሬታዎች ይሰሙ እንጂ ኢትዮጵያ በየቀኑ የምታደርገው የኮሮናቫይረስ ምርመራ እየጨመረ መጥቷል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ አሳይቷል። ይህ ቁጥር መቀነስ ከምርመራ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ግን የተገለፀ ነገር የለም።
