5 መስከረም 2020, 10:18 EAT

ደብዳቤውን ከጻፉት ስድስት የኮንግረስ አባላት መካከል ሶስቱ። ከግራ ወደ ቀኝ ኢልሃን ኦማር፣ ጄሰን ክሮው እና ጆይስ ቤቲ
የምስሉ መግለጫ, ደብዳቤውን ከጻፉት ስድስት የኮንግረስ አባላት መካከል ሶስቱ። ከግራ ወደ ቀኝ ኢልሃን ኦማር፣ ጄሰን ክሮው እና ጆይስ ቤቲ

ስድስት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ እንዲቀነስ መደረጉን በመቃወም ለአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ እና ለግምጃ ቤት ኃላፊው ስቲቭ ሙንሽን ደብሳቤ ጻፉ።

የኮንግረስ አባላቱ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ እንዲቀነስ መደረጉ እጅጉ አሳስቦናል” ብለዋል።

“ይህ የውጪ ድጋፍ እንዲቀነስ መደረጉ ታማኝ ከሆነች አጋራችን ጋር ያለንን ግንኙነት ከማሻከሩም በተጨማሪ አሜሪካ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል በሚደረገው ድርድር ላይ የሚኖራትን ተሳትፎና ገለልተኝነትን ጥያቄ ውስጥ ይጥላል” ብለዋል የኮንግረስ አባላቱ።

ቀደም ሲል የሲአይኤ ኃላፊ ለነበሩት የአሁኑ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ ደብዳቤውን የጻፉት የኮንግስ አባላት ጄሰን ክሮው፣ ኢልሃን ኦማር፣ ኮኒን አልሬድ፣ ጆህን ግራሜንዲ፣ ጆይስ ቤቲ እና ጄራልድ ኮንሊይ ናቸው።

አሜሪካ ኢትዮጵያ ግንባታውን በማካሄድ ላይ ባለችውና ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የሚደረገው ድርድር መቋጫ ባላገኘው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዳ የነበረውን ወደ 130 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የእርዳታ ገንዘብ ልትከለክል መሆኑ በስፋት ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋ ከአሜሪካ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ጠይቀው ባገኙት ምላሽ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ከታቀደው የገንዘብ ድጋፍ የታገደው “በጊዜያዊነት” ነው በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።

የ Twitter ይዘትን ይለፉት, 1

Rep. Jason Crow

@RepJasonCrow

The Grand Ethiopian Renaissance Dam is a point of national pride for Ethiopia. #GERD could provide stable electricity & boost economic security in the region.

This week, I led a letter to @SecPompeo & @stevenmnuchin1 urging them to halt cuts in foreign assistance to Ethiopia.

Image
Image

2:26 PM · Sep 4, 2020

1.8K 860 people are Tweeting about this

የ Twitter ይዘት መጨረሻ, 1

ደብዳቤውን የጻፉት ስድስቱ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት “የህዳሴው ግድብ እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያውያን የገንዘብ መዋጮ ነው።. . . ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት ነው በቀጠናውም ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማፋጠን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ይሆናል” ብለዋል።

የኮንግረስ አባላቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን፤ በአሜሪካም ከሩብ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

የኮንግረስ አባላቱ ኢትዮጵያ በምሥራተቅ አፍኢካ የአሜሪካ ቁልፍ የደኅንነት አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤ በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ውስጥ ቁልፍ ሚና የምትጫወትና በተለይም እንደ አል-ሸባብ ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን ለመዋጋት ቁልፍ አጋር ናት ብለዋል።

ጨምረውም “ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀንስ ማድረጉ በቀጠናው ከአሜሪካ ፍላጎት አንጻር ተጻራሪ ነው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ለክፍለ ዘመን የዘለቀውን መልካም ግንኙነት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል።”

የኮንግረስ አባላቱ በደብዳቤያቸው “የጉዳዩን ውስብስብነት እንረዳለን” ካሉ በኋላ፤ ድጋፉ እንዲቀነስ መደረጉ አሜሪካ ለአንድ ወገን መወገኗን ያሳያል ካሉ በኋላ፤ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያለው መፍትሄ ለማምጣት ዩናይትድ ስቴትስ ገለልተኛ አሸማጋይ መሆን ይኖርባታል ብለዋል።

“ስለዚህም ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ መቋረጥ እንደሌለበት እና ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት አሜሪካ ገለልተኛ አደራዳሪ እንድትሆን እንጠይቃለን” በማለት ስድስቱ የኮንግረስ አባለት ጠይቀዋል።

ከሳምንት በፊት ‘ፎሬይን ፖሊሲ’ የተባለው መጽሔት የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከመደበው ድጋፍ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላር ላለመስጠጥ መወሰኑን የውስጥ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቦ ነበረ።

ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን በዚሁ መሰረት ነው ገንዘቡ በጊዜያዊነት እንዳይሰጥ መደረጉን ገልጸው ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ከቀናት በፊት ባወጠው ዘገባ አንድ የአሜሪካ መንግሥት ምንጭን ጠቅሶ አገሪቱ ለኢትዮጵያ ለመስጠት አቅዳ ከነበረው ገንዘብ ውስጥ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የእርዳታ ገንዘብ ልትከለክል መሆኑ አመልክቷል።