ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ
International Ethiopians Solidarity Forum
መስከረም 4 ቀን 2013 ዓም(14-09-2020)
ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም!
ውድ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጽሁፍ ልናሳውቃችሁ የምንወደው ሁላችንንም በሚመለከት ጉዳይ ላይ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ድርጅታችን ላቀረበው አቤቱታ የሰጠውን መልስ ነው።
በተለያዩ ወቅቶች በተከታታይ በተለያዩ ያገራችን ክፍላተ ሃገር ከተሞች በተለይም ከሦስት ወራት በፊት አሸባሪዎችና ነውጠኞች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ጭፍጨፋ ወይም እልቂት(ጀኖሳይድ) በተመለከተ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአውሮፓውያን አቆጣጠር በጁላይ 15 ቀን 2020 አቤቱታ አቅርበን ነበር።አቤቱታውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ከዚህ ጋር አባሪ ያደረግነውን ምላሽ በዛሬው ዕለት ማለትም በአውሮፓውያን አቆጣጠር በሴፕቴምበር 14 ቀን 2020 ሰጥቶናል።
በላከልን ምላሽ እንደተብራራው የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጠውና የሚያዬው በመንግሥታት በተለይም ወንጀሉ የተፈጸመበት አገር መንግሥት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደሆነ በግልጽ አብራርቷል።አያይዞም ጉዳዩ በሌሎች አስተማማኝ ድርጅቶች በኩልም የተጠናቀረ ማስረጃ ያለው አቤቱታ ቢቀርብ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማዬት እንደሚችልም ጨምሮ ገልጿል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
ይህንን ወንጀል አስመልክቶ በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወንጀሉ ተባባሪ እንደመሆኑና ያንንም ለመሸፋፈን የሚያደርገውን ማወናበድ ስንመለከት ለተበደሉት ወገኖቻችን ጥብቅና በመቆም ወንጀለኞቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በአገር ውስጥም ሆነ፣ለዓለምም ፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀርባል የሚል ግምት ሊኖረን አይችልም።ለይምሰል በአገር ውስጥ የሚካሄደው የፍርድ ሂደትም በሆነ ባልሆነው ምክንያት ሊቋረጥና ወንጀለኞቹ በነጻ የሚለቀቁበት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ የእኛም ሆነ የብዙዎች ስጋትና ጥርጣሬ ነው።ይህንን በዓለም ማህበረሰብ የተወገዘ ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት እንዳልተፈጸመ አድርጎ የማዬቱ አዝማሚያ ክህደት ከመሆኑም በላይ ዋጋ ቢስ በማድረጉ ሌሎቹ ትኩረት እንዳይሰጡት አድርጓል።ለዚያም ነው ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ያልነው።
ስለሆነም በየአቅጣጫው የሚደረገው የተበታተነ ጥረት በአንድ ብሔራዊ የሕግ ባለሙያዎች ስብስብ በኩል ቢቀናጅ ሌሎቹን ሊያሳምንና የዓለም ፍርድ ቤቱን ትኩረት ሊያገኝ ይችላል ብለን እናምናለን።ለዚያም መንደርደሪያ እንዲሆን ድርጅታችን ለላከው የአቤቱታ ደብዳቤ ያገኘውን ምላሽ ከዚህ ጥሪ ጋር አያይዘን ልከነዋልና ሳይውል ሳያድር አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን እናሳስባለን።በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋህዶና የእስልምና እምነት ተከታዮች የጥቃቱ ሰለባ በመሆናቸው ተቋማቱ ከሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ ለዓለም ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡ ተሰሚነት ሊኖራቸው ይችላል ብለን እናስባለን።
ምናልባትም ጉዳዩ የአፍሪካ ህብረትን ስለሚመለከት፣በአንድ አባል አገር ሕዝብ ላይ የተፈጸመና ወደፊትም ወደ ሌሎቹም ያፍሪካ አገሮች ሊዛመት የሚችል ስጋት በመሆኑ፣ከሩዋንዳ ተመክሮ በመውሰድ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መሰራት የሚገባው የጸረ ጭፍጨፋ( ጀኖሳይድ) አቤቱታ በህብረቱ በኩል ትኩረት እንዲያገኝ የማድረጉ ሥራ ቢሠራ ምናልባት ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለን።ስለሆነም ጥረቱ ሁለገብ መልክ ቢይዝ እንደሚበጅ አምነን ትኩረት እንዲሰጠው ለማሳሰብ እንወዳለን።
ለፍትህና ለዴሞክራሲ አንድ ላይ እንቁም!
የሕዝባችንን መብትና የአገራችንን ክብር በዓለም አቀፍ መድረኮች እናስጠብቅ!!i
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን መድረክ
International Ethiopian solidarity Forum(IESF)
E mail inter.ethiopiansolidarityforum1@gmail.com
