ኢሕአፓ/eprp

January 29

የቀረ ሰው አለ

አምና የተነሳ መንገድ የጀመረ

ካሰበበት ሊደርስ ወገቡን ያሰረ

ትናንት የነበረ ዛሬ ግን የሌለ ሰው አለ የቀረ

እኛስ ተገኝተናል ዘመን ተሻግረናል

በለቅሶ ሸለቆ ሰንጥቀን አልፈናል

እንደ ሻማ ቀልጦ እዚህ ያደረሰን አለ ሰው የቀረ

አጥንቱ እንደ ጀልባ ደሙ ባህር ሆኖ እኛን ያሻገረ

ሆዴን ባርባር አከው ባዶነት ተሰማኝ

የቀረ ሰው አለ የለም አትበሉኝ

ሞቷል አትበሉኝ አልሞትም ህያው ነው?

እዚህ ያደረሰን ያመጣን ሰው ማነው?

እንፈትሽ አምባውን ቆላ በረሀውን

ገጠር ከተማውን

አናግሩት ይናገር የሰሜን ተራራ

አርማጮ ጠገዴ የጀግኖች ስፍራ

ይናገር ወልቃይት መተማና ሻውራ

አቸፈር በለሳ ጠለምትና ቋራ

አትመሰርክርም ወይ ምነው ጃን አሞራ

የቀረ ሰው አለ ያደረ አንተ ጎራ

አብሮን የተጓዘ አብሮን የነበረ

ልቡ ተሰብሮበት ከመንገድ የቀረ

ታላቅ ሰው አጥተናል እኛ ግን መጥተናል

አይሰማም አትበሉት ጥሩት ይሰማናል

እስኪ ነው እንጥራ ያልመጣ የቀረ

ዮሴፍ የከተመ በረሀ ያደረ

እሱ ለሱ ያልሆነ ለራሱ ያልኖረ

ሰው ጥሩ ሰው ጥሩ ስንት ሰው ነበረ

እንዴት ላልቅስ ዛሬ እንዴት ላፍስ እንባ

ሞቷል ያሉት ጀግና መቃብር አልገባ

አታውጡለት ሙሾ አልቃሽ አታቁሙ

እሱ እኮ አልሞተም ህያው ሆኗል ስሙ

በአካል ባይመጣ እንጂ ባይኖር ከእኛ ጋራ

አልተቀላቀለም ከሙታኖች ጎራ

እንደዚህ ሰብስቦ እኛን ወልዶ አፍርቶ

ቀረ ይባላል ወይ ከመቃብር ገብቶ

ግን የቀረ ሰው አለ ያልሞተ የኖረ

መንገድ የቀየሰ ትግል ያስተማረ

ቢያየው መልካም ነበር ዛሬ ብቅ ብሎ

ያፈራውን ፍሬ በደሙ ተተክሎ

እንዴት የለም ይባል ሰው አለ የቀረ

ሸክም የበዛበት ወንዝ ያልተሻገረ

አይመጣም ብትሉኝ ይመጣል እላለሁ

ቃሉን በቃል ሽሮ እንዳይኖር አውቃለሁ

ይዘገያል እንጂ አይቀርም መምጣቱ

ህያው ነው ዘላለም አልተወራም ሞቱ

ውሎ ገባ ባይችል ረዝሞበት መንገዱ

ቢደክም ጉልበቱ ቢዝልበት ክንዱ

ሰብስቦን አንድ ላይ ከጫፍ ጫፍ ተጠራርቶ

ቃል ለምድር ለሰማይ አይቀርም ቃል ገብቶ

ሰው መጥቷል አልቀረም ተገኝቷል ካላችሁ

ጀግናው ሓይለማርያም የታል ከጎናችሁ

የት ጠፋ ስጦታው የቀትር ላይ መብረቅ

አለሁ ይላል ጥሩት እውነት አይደበቅ

ዮሴፍን ጎበኘሁ ሀውልቱንም ቃኘሁ

ላይ ቀጨኔ ወጣሁ ከሙታኖች መንደር አሉላንም አጣሁ

አልቀረም ካላችሁ ጃብርን ምን ዋጠው

ምድር ተሰኝጥቆ ሰማይ አፉን ከፍቶ ባህር አሰመጠው

ያልመጣ ሰው አለ የማይቀር የቀረ

ደረቱን ከሳንጃ ፊቱን ያላዞረ

መታሰቢያ ብለን ሀውልት አናቆምም

ዘገየብን እንጂ ሞቷል እኮ አላልንም

አንተ ፅልመተ ሞት

የት ገባ ደብተራው ምን በላው ምን ዋጠው

ጠረጠርኩህ አንተን እዚህ ስፍራ ሳጣው

የደም ሱስ ያለብህ ጥማትህ ያልረካ

ዲበኩሉን በልተህ ምኞትህ ተሳካ?

አይሆንም አልሞተም አመሃ በለጠ አፈር አልቀምስም

ጉዞ ጀመረ እንጂ ከጫፍ አልደረሰም

ማነው ሞተ ያለው ሩጫ ጨረሰ

ጉልበቱ ደከመ አሞቱ ፈሰሰ

በላ ልበልሃ ልሞግት ሞግተኝ

የማይሞተውን ሰው ማነው ሞተ ያለው

እርሱ አይደለም ወይ ሰንደቅ የሰቀለው

ተነሱ እናውርደው መሬት እንጣለው

ክብራችን ሆዳችን መቼ ሰንደቁ ነው

ብለው ቢማማሉ ቢስማሙ በአንድ ላይ

/ር ያስቀመጠው የደመና ቀለም አይወርድም ከሰማይ

አባይነህ ሽፈራው ጌታቸው ወርቅነህ

ገለብ ዳፍላ ጀብል ጀብር ይስሃቅ ገ/ጽዮን ዲበኩሉ አንተነህ

አስማረ መኳንንት ሐድሽና አበራሽ

ሙሉ አምባው አሉላ በርሄ ደመላሽ

እስቲ አምባዬን አምጡት ይታይ ለማ ሐይሌ

የት አለ ጀግናው ሰይፉ ከጊንር ከባሌ

አትበሉኝ አልቀረም ሰው ቀርቷል እላለሁ

መች ተሰማ ድምጹ ያድሉ ገበየሁ

ሕይወቱን ገብሮ ሕይወት ያተረፈ

ሞት ቢመጣ አፍጦ ፊቱን ያላጠፈ

የበረሀው ገግሳ ልበልህ አንተነህ

አልመች ብሎህ ነው ዛሬ እዚህ ያጣንህ

ብርሃኑ እጂጉ አዘናው ደምሴ

ወንዱ ሲራክ እዮብ ተፈራ ተካበ

ተሾመ ባዩ ጌታቸው አበበ

እስኪ ሰው እንጥራ ያልመጣ የቀረ

ዮሴፍ የከተመ በረሃ የቀረ

እሱ ለእሱ ያልሆነ ለራሱ ያልኖረ

ሰው ጥሩ ሰው ጥሩ ስንት ሰው ነበረ

እኛ ተገኝተናል ዘመን ተሻግረናል

በለቅሶ ሸለቆ ሰንጥቀን አልፈናል

እንደ ሻማ ቀልጦ እዚህ ያደረሰን አለ ሰው የቀረ

አጥንቱ እንደ ጀልባ ደሙ ባህር ሆኖ እኛን ያሻገረ

ትምጣ መድፈሪያሽ ወርቅ ያቺ የሴት ጉልላት

ጠዋት ታይታ አመሻሽ አውሬ ነው የበላት

ህብስቱ ሙስጠፋ ሕሩይና አክሊሉ

አብዩ ተፈራ ደመቀና ሉሉ

በግዜ አልደረሱም አልመጡም የት አሉ?

ወላይታ ሀዋሳ ከንባታና ሀዲያ

ወሎ ካራ ጉቱ ኮምቦልቻ ወልዲያ

ሐ ረር ድሬዳዋ በይፋ መስክሩ

እነማን ነበሩ መንገድ የጀመሩ ሳይደርሱ የቀሩ

ዳዲሞስ