ፀረ አማራው ብአዴን ከአማራ ሕዝብ ውስጥ የአማራ መከራ ፈጽሞ ቅንጣት ታክል እንኳ የማይሰማቸውን፣ የማይደንቃቸውንና ፈጽሞ ምንም የማይመስላቸውን ጭፍን ደጋፊዎቹንና ካድሬዎቹን ማፍራት የቻለው በጥረት ውስጥ ባሉ በርካታ የንግድ ድርጅቶቹና የአማራ ክልል በሚሉት ባሉ የመንግሥት ሥራዎች ነው፡፡ በሀገሪቱ ሕግ የፓርቲ የንግድ ተቋማትን መመሥረትና ማንቀሳቀስም ሆነ የመንግሥት ሥራን ለፓርቲ ጥቅም ማዋል ወንጀል ወይም ሕገወጥ መሆኑን አትርሱ!!!

 እነኝህ ብአዴን በአማራ ሕዝብ ላይ የፈለገውን ነገር ቢፈጽም ፈጽሞ የማይቀየሙ ይልቁንም ምንም ይሁን ምን ብአዴን ያደረገውን ሁሉ አጥብቀው የሚደግፉ ደጋፊዎቹና ካድሬዎቹ በሆዳቸው የተያዙና ለሆዳቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ ፀረ አማራውን ብአዴንን ለመደገፍ የተገደዱ በእነኝህ የንግድ ድርጅቶቹና በሚቆጣጠራቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞቹና ካድሬዎቹ ናቸው!!!

 ወያኔ በእራሱና በእኅት ድርጅቶቹ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን ስም ግዙፍ ግዙፍ አቅም ያላቸውን የንግድ ተቋማትን የመሠረተበት ዋነኛው ዓላማም ይሄው ነበረ፡፡ ማለትም የትም የማይሔድና ጠንካራ ድጋፍ የሚሰጥ በጥቅም የተገዛ ማኅበራዊ መሠረት (constituency) ለመፍጠር በማሰብ ነው!!!

 ይሄ ዓላማውም በሚገባ ተሳክቶለት እንደምታዩዋቸው አማራ ነን!” እያሉ ነገር ግን ፀረ አማራው ብአዴን የፈለገውን ዓይነት ግፍ በአማራ ላይ ቢፈጽምና ቢያስፈጽም ምንም የማይመስላቸው አማሮች ተፈጥረው እያየን ነው፡፡ ይሄንን በመረዳት ፀረ አማራው ብአዴን ከአማራ ውስጥ ጭፍን ደጋፊና ጠንካራ ምርኩዝ ማግኘቱ ሊገርመንና ሊደንቀን አይገባም፡፡ ይሄ ጉዳይ በብአዴንና አማራ ብቻ ያለ ሳይሆን በኦሕዴድና ኦሮሞ፣ በደኢሕዴንና ደቡብ ውስጥም ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በወያኔና ትግሬ ያለውን የጥቅምና የህልውና ቁርኝት መናገር የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም!!!

 በመሆኑም የወያኔ/ኢሕአዴግን ወይም ደግሞ ከሦስት ዓመት ወዲህ የለውጥ ኃይል እና ለውጥ አደናቃፊ ተባብሎ ተቧድኖ እየተወነብን ያለውን አገዛዝ ማሽመድመድና መጣል ከፈለግን በእነኝህ የንግድ ተቋማቶቹ ላይ ማነጣጠር ይኖርብናል ማለት ነው!!!

 እንደምታስታውሱት በሕዝባዊ ትግሉ ወቅት ሕዝባችን ዳሸን ቢራን አልጠጣም!” ብሎ አድሞ በዳሸን ቢራ ላይ ተአቅቦ (boycott) ማድረጉ የወያኔ/ኢሕአዴግን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም ምን ያህል እንዳዳከመውና እንዳሽመደመደው በቅርብ የምናስታውሰው ነው!!!

 አሁንም ያለ አንዳች የጥይት ጩኸት አገዛዙን ማንበርከክና ማሽመድመድ ከፈለግን ቀላሉ መፍትሔ፣ መላ፣ መሣሪያ፣ ድል መንሻ፣ በእጃችን ነው!!! መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነኝህ ማለትም በኤፈርት፣ በጥረት፣ በዲንሾና በወንዶ የወያኔ/ኢሕአዴግ የንግድ ተቋማት ላይ ወጥሮ እንደ ተአቅቦ (boycott) እና ክልከላ (ban) ያሉ የአድማ እርምጃዎችን መውሰድ ግዴታ ነው!!!

 መቸም ዋጋ የማያስከፍል ምንም ነገር የለምና እነኝህን ሕጋዊ የአድማ እርምጃዎችን ስትወስድ የፓርቲዎቹን የንግድ ተቋማትን ምርቶችና አገለግሎቶች አልጠቀምም!” ብለህ ምርቱንና አገልግሎቱን ከእነዚህ ተቋማት ውጭ የሚሰጥ ሌላ ተቋም ወይም ድርጅት በቅርብህ ብታጣ ከሚገጥምህ መጠነኛ እንግልት ጀምሮ የተቋማቱን ምርትና አገልግሎት ባለመጠቀምህ በአንባገነኑ አገዛዝ ሊገጥምህ እስከሚችለው ሕገወጥ የበቀል እርምጃ ድረስ ዋጋ መክፈልህ የማይቀር ነውና ለዚህ ወገብህን ጠበቅ ማድረግና እራስህን ማዘጋጀት ይኖርብሀል፡፡ ለድል መብቃት ከፈለክ የፈለገው ነገር ቢሆን ዋጋ ሳያስከፍል የሚገኝ ድልና ስኬት ፈጽሞ የለምና መጽናት ይኖርብሀል፡፡ ይህ አድማ የተባለ የሰላማዊ ትግል እርምጃህ ወይም እንቅስቃሴህ በየትኛውም የዓለም አቀፍ ሕግና ድንጋጌ ሁሉ ሕጋዊና መብት በመሆኑ አንዳችም ፍርሐትና ሥጋት ሊሰማህ አይገባም!!!

 እንደ ሰውና እንደዜጋ የሀገሬ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እጅግ በሚያሳዝንና ነውረኛ በሆነ መንገድ መገፈፍ ይመለከተኛል፣ ይገደኛል፣ ያሳስበኛል የሚል የፖለቲካ ድርጅት፣ ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች፣ የእምነት ተቋማትና መሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ አንቂዎች፣ ወዘተረፈ. ለዚህ ሕጋዊ የሰላማዊ ትግል እርምጃ ድጋፉን ካልሰጠና ካልተባበረ ከጠላት ጋር የወገነ የሕዝብና የሀገር ጠላት መሆኑን ጠንቅቆ ይወቅ!!!

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እንቅልፍና መጃጃል ይብቃህ! ወገብህን ጠበቅ አድርግና ዳይ ወደ ድል ትግል!!!

 እባክዎን ጽሑፉን ሼር በማድረግ የዜግነት ግዴታዎን ይወጡ???

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው