25 መስከረም 2020

አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ አፍሪካ አገራት የሚመጡ ተማሪዎችን አስመልክቶ በቅርቡ አንድ ረቂቅ መመሪያን አቅርባለች።
በዚህም ረቂቅ መሰረት የተማሪዎቹ ቪዛ በሁለት አመት እንዲገደብ የሚመክር ነው። ይህም ማለት የትምህርት ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ የቪዛ ጊዜያቸው ያልቃል ማለት ነው።
በአሜሪካው ሆምላንድ ሴኩሪቲ ቢሮ የወጣው ይህ መመሪያ ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ይሰጥ የነበረውን የቪዛ ህግም የቀየረ ነው ተብሏል። መመሪያውም ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
ረቂቁ የአራት አመት ቪዛ የሚሰጣቸው አገራትን ዝርዝር ያካተተ ሲሆን በሁለት አመት ደግሞ የሚገደብበትም አንደኛው ምክንያት “በከፍተኛ ሁኔታ ማጭበርበርና ብሄራዊ ደህንነት ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ ነው” ብሏል መረጃው
እነዚህ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ተብለው ከተጠቀሱት አገራት መካከል ሽብርን በመደገፍ የምትጠረጥራቸው እንደ ሱዳን ያሉ አገራት የሚመጡ ተማሪዎች ተፅእኖ ይደርሳል ተብሏል።
በዋነኝነት ግን ዝርዝሩ ቪዛው ከሚፈቅድላቸው በላይ የቆዩ ተማሪዎችን አገራትን ያካተተ ነው።
ቪዛው ከሚፈቅድላቸው በላይ የቆዩ ተማሪዎችን በአማካኝ አስልቶም 10 ከመቶ በላይ የቆዩ አገራት ዜጎችን በሁለት አመታት እንዲገደብም ይመክራል።
የኢትዮጵያና የናይጄሪያ ተማሪዎች ከ13 በመቶ በላይ እንደቆዩም መረጃው የጎሮጎሳውያኑን 2019 መረጃን አጣቅሶ አስፍሯል።
ከነዚህ አገራት በተጨማሪም ቡርኪናፋሶ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሮን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋቦን ፣ ዘ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያ፣ ማላዊና ኡጋንዳም ተካትተዋል።