የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ ከ5ሺህ 700 በላይ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠቅላይ ዐጨቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተፈጸሙ ወንጀሎች ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረው ምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት አቃቤ ሕግ በ5 ሺህ 728 ሰዎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የእርስ በእርስ ግጭት በመቀስቀስ በሚል ወንጀል ክስ መመስረቱን ዛሬ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቋል።
በወንጀል ምርመራው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ተሳታፊ ሆነው መቆየታቸውን ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፍቃዱ ጸጋ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል 3 ሺህ 377 በፌዴራል መንግሥት ስልጣን ስር የሚወድቅ እንዲሁም 2 ሺህ 351 በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገልጿል።
በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች በ114 በኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ደግሞ በ374 የክስ መዛግብት ክሱ መደራጀቱ ተጠቁሟል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ምርመራ ተጠናቆ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ክስ መመስረት እንደሚጀመር ከትናንት በስቲያ መግለጻቸው ይታወሳል።
ከተፈጸመው የወንጀል ስፋት አንጻር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው አንዳንዶች ከጅምላ እስር ጋር ቢያያይዙትም በወንጀሉ የተሳተፉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በርካቶች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደቻሉ አብራርተዋል።
በቁጥጥር ሥር ከሚገኙት መካከል ፖለቲከኞች መኖራቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፤ ፖለቲከኞቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግን በፖለቲካ ተሳትፏቸው አይደለም ብለዋል።
ከተጠርጣሪዎች ብዛት እና ከወንጀሉ ስፋት አንጻር የምርመራ ጊዜው ረዥም ጊዜ እንደወሰደ የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ጨምረው የተናገሩ ሲሆን፤ አነስተኛ የወንጀል ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎችም ጉዳያቸው እየታየ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በዋስትና እንደሚለቀቁ ተናግረዋል።
ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከት የ167 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም 360 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከ4.67 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ደግሞ መወድሙ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ቢቢሲ