በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በንገዝ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ሐሙስ መስከረም 14/2013 ሌሊት ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
ጥቃቱ የተፈጸመበት የበንገዝ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደምለው ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ቢያንስ 14 ሰዎች በጥይት መገደላቸውንና ከሰለባዎቹ መካከልም ወንድማቸው እንዳለበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ “በድጋሚ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉ” ገልጾ፤ ሁኔታው በእጅጉ አሳሳቢነቱ እንደጨመረ መሆኑን አመልክቷል።
የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ ደምለው እንዳሉት “ጥቃቱ የተፈጸመው ሌሊት 10 ሰዓት ነው። ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልቻልንም። የጥይት ተኩስ ብቻ ነበር በአካባቢው የሚሰማው፤ ብዙ ሰው ነው ያለቀው” በማለት “የእኔ ወንድምም በጥቃቱ ተገድሏል” ሲሉ አስራ አራት ሰዎች መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ባወጣው መረጃ ደግሞ “በጥቃቱ የተገደሉት ንጹሃን ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ” እንደሆነ ዘግቧል።
እስካሁን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን ጥቃት ማን እንደሚፈጽመው በግልጽ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ማብቂያ ጀምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች እንደተገደሉ እየተነገረ ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከሰተ ያለውን ጥቃት በተመለከተ “በክልሉ ጸጥታን ማስፈን፣ የሕግ በላይነትን ማረጋገጥና በሰላማዊ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት እያደረሱ ያሉትን አድኖ ለፍትሕ ማቅረብ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል” ሲሉ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ መለሰ በየነ ሐሙስ ሌሊት የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የተጠናቀረ መረጃ እንደሌላቸው ጠቅሰው ጥቃት መፈፀሙን ግን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግን አርብ እስከ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ ባሰባሰበው መረጃ 15 ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ከእነሱም ውስጥ 11ዱ ወንዶች 4ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ከአካባቢው የመንግሥት ምንጮች ማረጋገጡን አመልክቷል።
ቀደም ሲል መተከል ዞን የተከሰተውን ችግር ተከትሎ አካባቢው በኮማንድ ፖስት ስር እንዳለ እንዳለ የሚናገሩት አቶ መለሰ ኅብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም ዳንጉር ወረዳ አይሺካ ቀበሌ ልዩ ስሙ በንገዝ የሚባል ስፍራ ላይ እንዲሁም ባለፈው ወንበራና ቡለን ወረዳ ላይ በሚገኙ ቀበሌዎች ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩ ታጣቂዎች ሐሙስ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ወደ ማኀበረሰቡ በመግባት ጥቃቱን ፈጽመዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በቦታው የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የክልሉ ፀጥታ ኃይል በጋራ በመሆን የማረጋጋት ሥራዎች እየሰሩ ነውም ብለዋል።
የክልሉ የኮሙኑኬሽን ቢሮ ኃላፊ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ሽፍቶች እንደሆኑ በመጥቀስ “በውስጥም በውጪም ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው” ካሉ በኋላ፣ በዚህ ጥቃት ውስጥ የተለያዩ አካላት እጃቸው አለበት ሲሉ ከሰዋል።
የሚፈጸመውን ጥቃት በተመለከተም አቶ መለሰ አጥቂዎቹ ብሔርን እንደማይለዩና በቦታው ያገኟቸውን በሙሉ እንደሚገድሉ በመግለጽ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን የሚጻፉት ነገሮች ከእውነታው የራቁ ናቸው ብለዋል።
በአካባቢው እንዲህ አይነት ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን በማንሳት የክልሉ መንግሥት እንዲህ ያለውን ክስተት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ የተጎዱ ሰዎችን ለማግኘት አሰሳ እያካሄደ ሲሆን፤ በዚህም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋት እንዳለ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ጨምሮም ጥቃቱ የተፈጸመው በሕገ ወጥ ታጣቂዎች እንደሆነ መረጃዎች የሚያመለክቱ መሆኑን ጠቅሶ፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ ካካሄዱ በኋላ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን እንደተቆጣጠረ” ማረጋገጡን አመልክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ ከባለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር ጀምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት እስካሁን ቁጥራቸው በይፋ ያልተገለጸ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን የሚያመለክት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይ በመተከል ዞን የተለያዩ ስፍራዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ እያጋጠሙ ያሉትን ጥቃቶች ተከትሎ በአካባቢው ያሉ አራት ወረዳዎች በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ መደረጉ ይታወቃል።
ቢቢሲ