ክርስቲያኖች ሆይ “የመስቀል በዓልን አታከብሩም!” ተብሎ ከመከልከልና ዜጎች ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ከመታረድ አብያተክርስቲያናትም ከመቃጠላቸው የትኛው ይከፋል??? የትኛው ይመራል??? የትኛውስ ያሳስባል???
ጠላት ተሻግሮ ሔዶ ክርስቲያንንና አብያተክርስቲያናትን ማጥፋት ማውደም ላይ ደርሶ ክርስቲያኖችንና አብያተክርስቲያናትን እያጠፉ ነው መንጋው “በዓል አታከብርም!” መባሉ ደንቆት ሲንጫጫ ማየቴ በእጅጉ ደንቆኛል!!!
አምና እና ታች አምና የጀመረው ይህ በዓል አከባበርን የመከልከል መንግሥታዊ ጋጠወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት ዘንድሮ ተጠናክሮ አድማሱን እያሰፋ መጥቷል፡፡ ከርሞ ደግሞ ምናልባትም እዚህ አዲስ አበባም “አታከብሩም!” እንባል ይሆናል፡፡ በእርግጠኝነት ግን ተጨማሪ የሚከለከሉ ከተሞች ይኖራሉ!!!
አምናና ታች አምና ሰበብ ተደርገው ይቀርቡ የነበሩ ምክንያቶች ከጸጥታና ደኅንነት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ እነኝህ ምክንያቶች ሐሰተኛ ሰበቦች መሆናቸው የተረጋገጠው ግን ዛሬ ያለምንም ምክንያት ናዝሬት፣ ደብረዘይትና ሞጆ “አታከብሩም!” ተብሎ ሲከለከል ሳይሆን ያኔውኑ በቀናት ልዩነት እሬቻ የሚሉትን በዓላቸውን በድምቀት ሲያከብሩ ነበር፡፡ የናዝሬት፣ የደብረዘይትና የሞጆ የቤተክርስቲያኗ አሥተዳደር አካላት ክልከላው በኮሮና ምክንያት ከሆነ በጣም በተመጠነ ቁጥር ለማክበር ዝግጁ መሆናቸውን ለአገዛዙ አካላት ቢያስታውቁም የተሰጣቸው ምላሽ በደፈናው “አታከብሩም ማለት አታከብሩም ነው!” የሚል ሆኗል፡፡ ምክንያቱም “አዎ በኮሮና ነው ዘንድሮን እንዲያልፋቹህ የወሰነው!” ቢሉ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ኢሬቻ ሲከበር ሊታይባቸው ነውና ነው፡፡ ጥላቻው ያለውና ይሄ ሊከተል እንደሚችል ማወቅ የነበረብን አገዛዙ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያንን የበዓል ማክበሪያ ስፍራዎቿን በተለያየ ምክንያት ሲቀማ ነበር!!!
እነኝህ የናዝሬት፣ የደብረዘይትና የሞጆ ከተሞች የዋሀን የቤተክርስቲያን አሥተዳደር አካላት በደፈናው “አታከብሩም!” ሲባሉ “እንዴ! ‘ኦርቶዶክስ ሀገር ናት‘ እየተባለ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? እንዴት እንደዚህ እንባላለን?” እያሉ ለመሟገት ሞክረዋል፡፡ ይሄንን የሚያህል ከባድ በነጻ የማምለክንና እምነትን በነጻነት የማከናወንን የዜጎችንና የሃይማኖት ሕገመንግሥታዊ መብት ወይም ድንጋጌን የጣሰ የነፈገ ክልከላና የመብት ጥሰት የፈጸሙት የእነዚህ ከተሞች አሥተዳደሮች መስለዋቸውም የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ አካል ቋሚ ሲኖዶስ ተብየውን “ኦርቶዶክስ ሀገር ናት!” እያለና “እንኳን ለደመራ በዓል አደረሳቹህ!” እያለ በአደባባይ በሚያወራው ሕዝበ ክርስቲያኑን እየገየደ ወይም እያታለለ ለአጥፊ ጭፍሮቹ ሽፋን በመስጠት ከጀርባ ደግሞ “የብልጽግና ፕሮግራም!” ብሎ ባወጣው ሰነድ ላይ ፕሮቴስታንትን እያደነቀና እያወደሰ ኦርቶዶክስን እያዋረደና እየኮነነ “የብልጽግና እንቅፋት ናት!” እያለ በቤተክርስቲያን ላይ ይሄንን ሁሉ መዓት እያዘነበ ላለው “ለተፈጸሙ ጥፋቶች ይቅርታ ጠይቅ!” ሲባልም “ይቅርታ አልጠይቅም!” ከማለትም አልፎ የቤተክርስቲያን መከራ ገና እንደሚቀጥል ቅንጣትም እንኳ ሳይፈራና ሳያፍር እንቅጩን ወደተናገረው የአውሬው መልእክተኛ የወያኔ ኩሊ ዐቢይ አሕመድ ፈጥነው እንዲያመለክቱ ወይም አቤቱታ እንዲያቀርቡ ጠይቀው ነበር፡፡ ቋሚ ሲኖዶስ ተብየው አቶ ዐቢይን ጠይቆ ይሁን አይሁን፤ ጠይቆም ከሆነ የተሰጠውን ምላሽ ባላውቅም!!!
እኔ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር ይሄ ሕዝብ አንድ አካል አታሎ፣ አጭበርብሮ፣ አጃጅሎ ሊያጠፋው ቢፈልግ ከዚህ የወያኔ ኩሊ ዐቢይ ወይም አገዛዙ እያደረገው ካለው ውጭ እንዴት አድርጎ አታሎ፣ አጭበርብሮና አጃጅሎ ሊያጠፋው እንደሚችል ነው ግን የሚጠብቀው??? ከፊቱ ላይ ለማጃጃል በአፋቸው ከሚቀባጥሩት የማጃጃያ ወሬ ተቃራኒ የሆነ የመብት እረገጣ፣ እጅግ ዘግናኝ ጥቃት፣ ጥፋትና ግፍ እየተፈጸመበት እያየ እያጃጃሉት እንደሆነ እንዴት አይገባውም??? እንዴት መንቃት ያቅተዋል???
ስለማጃጃል ሳወራ ስለ አገዛዙ ወይም ስለ አቶ ዐቢይ አሕመድ ብቻ አይደለም እያወራሁ ያለሁት፡፡ ነገር ግን ከዘመነ ተጋዳላይ አቦይ ጳውሎስ ጀምሮ እስከ ዘመነ ተጋዳላይ አቦይ ማትያስ ድረስ በዐውደ ምሕረት ወይም በአደባባይ መልካም ቃል እየሰበኩ፣ የአዞ እንባቸውንም እያነቡ ከጀርባችን ግን ከቤተክርስቲያን ጠላት ወያኔ ጋር ለጥፋቷ ተማክረው እየሠሩ አቦይ ስብሐት ነጋ እንደተናገረው አከርካሪዋን ሲያሰብሩ የኖሩትን ሐሳዊ ጳጳሳት ጭምር እንጅ፡፡ በዚህ ዘመንም ሲኖዶስ ተብየው በቤተክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ያወገዘና የተቃወመ እየመሰለ ጥቃቱንና የመብት ጥሰቱን ግን ለመግታትና ለማስቆም ማድረግ የሚጠበቅበትን አሥተዳደራዊ፣ ቀኖናዊና ሥርዓታዊ እርምጃ መውሰድ የማይፈልገውና ሕዝበ ክርስቲያኑንም ለቤተክርስቲያኑ እንዲቆም የማያደርገውም ለዚህ ነው!!!
ባይገርማቹህ እናንተ ልትነቁ ሊገባቹህ አልቻለም እንጅ አቦይ ስብሐት ነጋ እንዳለው ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉ የቀረውን የቤተክርስቲያንን አከራካሪ ለመሰባበርና ቤተክርስቲያንን ቀስ በቀስ ለማክሰም ከቤተክህነት እስከ ቤተመንግሥት ያሉ አገዛዙ ያስቀመጣቸው ሹመኞች ቤተክርስቲያንን ቀስ እያደረጉ ለማክሰም ተማክረው ተቀናጅተውና ተስማምተው ነው እየሠሩ ያሉት!!!
ከዚህ ቀደም ቤተክርስቲያኗ በኢሉሚናቲዎች (ፀረ ቤተክርስቲያን የሰይጣን አምላኪዎች) እጅ እንደወደቀችና አብዛኛዎቹ የሲኖዶስ አባላት እና ሁሉም የአገዛዙ ባለሥልጣናት የዚህ ኢሉሙናቲ የተባለ ዓለማቀፋዊ የጥፋት ቡድን አባሎች መሆናቸውን ከገዳም አባቶች እስከ መረጃው ያላቸው ዘመናውያን ሰዎች ድረስ ሲነገር ስሰማ ወሬው የተራ ሰዎች ወሬ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካ ተራዎቹ በዓይናችን ስር በቤተክርስቲያን ላይ ይሄ ሁሉ ጥፋት ሲሠራ የማይገባንና የማንነቃው እኛ ኖረናል፡፡ ይሄ ወሬ እውነት ለመሆኑ ከዚህ በቤተክርስቲያን ላይ እጅግ በረቀቀ ዘዴ ተቀናጅቶ እየተሠራና እየተፈጸመ ካለው ፀረ ቤተክርስቲያን የመብት ጥሰት፣ ግፍና ጥቃት በላይ ማሳያ ወይም መረጃ ሌላ ምን ሊኖር ይችላል???
እንደ እውነቱ ከሆነ አእምሮና ማስተዋል የራቀንና የተነሳን ሆነን እንጅ በቤተክርስቲያን ላይ ጥፋት ታውጆ ቤተክርስቲያን እንዲህ መከራ ላይ ተጥዳ ልጆቿ ገና ሳይወለድ በፅንስ ውስጥ ካለው እስከ አረጋዊው የቤተመቅደሱ አገልጋይ ካህን ድረስ እንደበግ እየታረዱ፣ አብያተክርስቲያናት እየተቃጠሉና እየፈራረሱ ባሉበት በዚህ የቤተክርስቲያን መከራ ዘመን ለዚህ እጅግ አሳሳቢ የቤተክርስቲያን ችግር መፍትሔ ሳናመጣና ሳናገኝ አምረን፣ ተውበንና ደምቀን በዓልን በፌሽታና በደስታ የምናከብርበት ጊዜ ባልነበረ!!!
መድኃኔዓለም ክርስቶስ እውነቱን ይግለጥልን፣ ማስተዋሉን ይስጠን፣ ከእንቅልፍ መጃጃላችን ያንቃንና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለቤተክርስቲያን ጥፋት ተባባሪ ሆነን በፊቱ ተወቃሽ፣ ተከሳሽና ተኮናኝ እንዳንሆን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት የምንችልበትን አቅም፣ ጽናትና ጥንካሬ አድሎን ቤተክርስቲያንን ከጥፋት እንድንጠብቅ ያስችለን አሜን!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው