ስለወቅታዊ የመተክል ዞን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅሟል” ብለዋል፡፡ በክልሉ የሚስታዋለውን ጥቃት ለማስቆም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደተሠራ የተናገሩት አቶ ግዛቸው የክልሉ መንግሥት ለተጎዱ ዜጎች ቦታው ድረስ በመሄድ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው ችግር እየቀነሰና እልባትም እያገኜ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በመተከል ዞን በዳንጉር፣ ጉባ፣ ማንዱራ፣ ወንበራና ቡለን ወረዳዎች በታቀደና በተደራጄ የታጠቀ ኃይል “ወገኖቻችን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል” ነው ያሉት፡፡ በዚህ ጥቃትም “በርካታ ንጹሐን ሕይወታቸው አልፏል፣ ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረት ወድሟል፣ ተወልደው ባደጉበት ሥፍራም ተፈናቅለዋል” ነው ያሉት፡፡
በንጹሐን ላይ የተፈፀመው ተደጋጋሚ ግድያ የማፍያ ሥራና የውንብድና ተግባር የታዬበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ዋና ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱት ብሔርን ከብሔር ጋር ማጋጨት እንደሆነና ቀጣናውን በተለይም አማራ ክልልን የማተራመስ ስልት የነደፈ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ የአማራ ክልልን ሕዝብ ሥነ ልቦና የመስለብ፣ የማዳከምና ዝቅ ብሎ እንዲኖር ለማድረግ ተፈፀመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የጥፋት ኃይሎችን ዓላማቸውን ተረድቶ ተገቢውን የሕግ እርምጃ በመወሰድ አደብ በማስገዛትና የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ያለው ሂደት “የሚደነቅ ቢሆንም አርኪ አይደልም” ብለዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይቶች ተደርገው “አቅጣጫ ቢቀመጥም እስካሁን ድረስ መሬት ላይ አልደረሱም” ነው ያሉት፡፡ “የቤንሻንጉል ክልል መንግሥት መዋቅር ንጹሕ አለመሆን፣ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ ያለው የተቀላቀለ መሆንና ዜጎችን ያገለለ ሥራ በመሥራታቸው ምክንያት ችግር እየተፈጠረ ነው” ብለዋል፡፡ “የማዕከላዊ መንግሥቱም ቢሆን ያደረገው ጥረት ጥሩ ቢሆንም ዜጎችን ግን ከሞት እያዳነ አይደለም” ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል መንግሥትም ቢሆን ችግሮችን በውይይትና በዴሞክራሲ ለመፍታት ብዙ የተደከመ ቢሆንም ነዋሪዎችን “ከጥቃት መታደግ አልተቻለም” ነው ያሉት፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሞቱና ሲፈናቀሉ ማዬት ከልክ ያለፈ ስለሆነ ምርጫው ሁለት ብቻ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ አንደኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጉዳዩን በዋዛ ፈዛዛ ሳይመለከተው የአማራ ክልል ተወላጆችን እንደሌላው የክልሉ ነዋሪ በሰላም እንዲኖሩ የማደራጀት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚያስችል ሥራ በአጭር ጊዜ የመፍጠርና ግድያ የሚያስፈፅሙትን፣ የሚያፈናቅሉትንና ሀብት የሚዘርፉትን እርምጃ ወስዶ እንዲያሳዬን እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ግን “የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እርምጃ እስኪወስድ ብቻ አንጠብቅም፤ ብዙ ታግሰናል፤ እንደ አማራ ክልል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን አሠራሩ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በጥምረት በመሥራት የክልሉ ተወላጆች ከዚህ በኋላ ከጥፋት የመታደግ ሁኔታ የግድ ነው” ብለዋል፡፡ ይህን የማድረጉን ሥራ “ከዚህ በላይ የምንታገሰው አይደለም” ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትም በመተከልና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ለማጥቃት የታቀደውን በማክሸፍ ሕዝቡ የሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብም ከስሜታዊነት በመውጣት መንግሥትን መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የራሱን ሥራ ለመሥራት አቋም የወሰደ ስለሆነ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ እንዲደግፈውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዜጎች በግፍ እየተገደሉ የሚኖሩበት ጊዜ ማብቃት እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡
በጉዳዩ ያለበት ሁሉ በራሱ ላይ የእርምት እርምጃ ወስዶ መፍትሔ ካላመጣ “ከዚህ በላይ አንታገስም፤ በራሳችንም መንገድ ጭምር ሄደን ዜጎቻችን መታደግ አለብን” ነው ያሉት፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ይህን ለማድረግ ያሳዬው ቁርጠኝነት እንዳለ በመጥቀስና እንደ አንድ አቅም ለመጠቀሞ ክልሉ አብሮ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
መረጃ