ሃይማኖታዊው እና ፖለቲካዊው ኢሬቻ –
( ሙሉአለም ገ/መድህን )
ኢሬቻ ሲባል በዋናነት ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የዋቄ ፈና (waaqeffannaa) ሃይማኖት ተከታዮች፣ በተከታይነት ከዋቄ ፈና ውጪ ያሉ ከሃይማኖት አንጻር ለዘብተኛ የሆኑ የቋንቋው ተናጋሪዎች፣ በአደባባይ ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ እና ዋነኛው ኢሬቻ ነው፡፡ ለበርካታ አስርት ዓመታት ከአዲስ አበባ፣ በ42 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ደብረዘይት ‹ሆራ አርሰዲ› ሐይቅ ሲከበር የነበረው ኢሬቻ ራሱን የቻለ የአከባበር ሥነ–ሥርዓት አለው፡፡ ባህላዊው የኦሮሞ ሃይማኖት ዋቄ ፈና ውስጥ ጉልህ በዓል ሆኖ የሚከበረው ኢሬቻ፣ በየዓመቱ መስከረም በገባ በአራተኛው ሳምንት የመጨረሻው እሁድ ላይ ይከበራል፡፡
ፕ/ር መኩሪያ ቡልቻ ‹‹Oromia’s Irreecha Festival – A Revival of an Ancient African Culture An Attempt to Understand and Explain›› በሚለው ጥናታቸው ኢሬቻ በአመት ሁለት ጊዜ እንደሚከበር ይገልጻሉ፡፡ Irreecha Birra በሚል ስያሜ የሚጠራው በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት የሚከበረው ሲሆን፤ Irreecha Arfaasaa ደግሞ በሚያዚያ ወር ላይ ይከበራል፡፡ በስፋት ሲከበር የምንመለከተው Irreecha Birra የዝናባማ ወቅት ማብቃቱንና እና የመኸር ወቅት መጀመሩን የሚያመለክተው የመስከረሙን በዓል ነው፡፡ በወንዝ እና በሐይቆች ዳርቻዎች ላይ በመሰባሰብ ስለ ችሮታው “ለዋቃ” ምስጋና የማቅረብ ሥነ–ስርዓት ይከናወናል፡፡ በሰዎች እና በዋቃ (ፈጣሪ) መካከል ሰላም (Nagaa) እና እርቅ (Araara ) እንዲፈጠር ጸሎት ይደረጋል፡፡ አለማየሁ ኃይሌ (1999) በበኩላቸው ‹‹Sirana Gada: Siyaasa Oromoo Tuulamaa›› በሚለው ጥናታቸው ሁለት አይነት ኢሬቻ እንዳለ በመጥቀስ በጸደይ ወራት የአከባበር ወር ላይ ከመኩሪያ ቡልቻ የተለየ ወር ይጠቅሳሉ፡፡ Irreechaa Malkaa በበልግ ወራት የሚከበር ሲሆን፤ Irreecha arfaasa ደግሞ በፀደይ ወቅት በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት በሚኖረው እሁድ ተራራ ላይ በመውጣት እንደሚከበር ይገልጻሉ፡፡
በዚህኛው የኢሬቻ በዓል ዓላማው ለሰው ልጆች እና ለእንስሳም አስቸጋሪ በሚሆነው በክረምቱ ወቅት በሰላም እንዲያልፍ፣ በክረምቱ ወቅት የደረቀውን ሣር እና ሌሎች ዛፎችን እንደገና እንዲለመልሙ ፈጣሪያቸውን ይለምኑታል ፡፡ አምላኪዎቹ በክረምትም ሆነ በበጋ በእጅ ሆኖ የሚቆየውን ሳር በመያዝ – ወደተራራ በመውጣት ዝናብ እንዲዘንብ ይጸልያሉ።
ከባህላዊው ሃይማኖት የሚቀዳው ይሄው የአደባባይ በዓል ራሱን የቻለ ትርጉም ያለው ሲሆን፤ ዋናው በዓል በመስከረም ወር አራተኛ ሳምንት የሚከበር በመሆኑ ‹‹የክረምቱን ጨለማ ጊዜ ተሻግረን ለብርሃን ስላበቃህን ዋቃ ክብርና ምስጋና ይገባሃል›› የሚል አንድምታ ያለው ስለመሆኑ Dirrib Damuse (2006) Ilaalcha Oromo በሚለው የጥናት ድርሳናቸው ያስረዳሉ፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው የጥናት ውጤቶችና ሌሎች መድብሎች ሲጠቃለሉ፣ ኤሬቻ ልምላሜ ያለው ሳር በመብቀሉና ተከታዮቹ እንደሚያምኑት ዋቃ ዓለምን የሚጠብቅበት፣ ፍጡራኑን ሁሉ የሚገዛበት መንፈሳዊ ኃይል ያለው በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡ የዋቃ መንፈስ በተራሮች አናት፣ በወንዞች፣ በባህር እና በሃይቆች ላይ ሰፍፎ ይገኛል፡፡ የበዓሉ ታዳሚያን ወደ እነዚህ አረንጓዴ አካባቢዎች በመሄድ፣ ቀለሙ ለሚሰመጠርበት ዝናብ፣ በረከትና ሠላምን መሻትን በማውሳት ይዘክራሉ፡፡ ያመሰግናሉ፡፡ ኤሬቻ የምስጋና በዓል ነው የሚለው ትርጓሜም ከእነዚህ ክዋኔዎች ጋር በተያያዘ ነው፡፡
ሃይማኖታዊው ኢሬቻ!
የኢሬቻ በዓል ከመከበሩ ከአንድ ቀን በፊት የዋቄ ፈና ሃይማኖት ተከታዮች በ Gaara Mudde (በተለመደው የአምልኮ ቦታ) በመሰብሰብ ለዋቃ ጸሎትና መባረክ ያደርሳሉ፡፡ ይሄ ቅድመ ዝግጅት ‹Jalabultii› በመባል ይጠራል፡፡ እንደባህላዊው ሃይማኖት የበዓል አከባበር ሥነ–ሥርዓት፣ የበዓሉ አክባሪዎች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀው ‹‹ከለቻቸው››ን እና ‹‹ጫጨዎቻቸው››ን ይዘው ወደ ሃይቁ/ወራጅ ወንዙ ይደርሳሉ፡፡ ቀጥሎ የሚኖረው ትዕይንት ለበዓሉ ሥነ–ሥርዓት የተዘጋጀው ትልቅ ኮርማ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ያልነጠረ ቅቤ በቄጤማ እየተነከረ/እየራሰ ኮርማው ከግንባሩ እስከ ጭራው ድረስ ሦስት ጊዜ ተመላልሶ እንዲቀባ ይደረጋል፡፡ ይህ ሥነ–ሥርዓት ሙዳ በመባል ይጠራል፡፡ ‹‹ሙዳ›› ‹መቀባት› የሚል አቻ የአማርኛ ቃል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ አባ–ሙዳ ምንጩ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ኤሬቻን በተመለከተ የተሰሩ ጥናቶች ያትታሉ፡፡
ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ስለ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ በዓልነት የሚከተለውን ብለዋል፤ «በኦሮሞ ዘንድ በገዳ ትዛዛት እየተመሩ የሁሉን ፈጣሪ አንድ አምላክ ዋቃን ማምለክ ዋቄፈና ይባላል። ዋቄፈና ሃይማኖት ነው። እሬቻ ደግሞ የዋቄፈና እምነት አካል ነው። ምዕመኑ ተሰብስቦ ለምለም ቄጠማ፤ አረንጓዴ ቅጠል፤ አበባ…ይዞ ፤ዋቃን በወንዝ ወይም በሐይቅ ዳርቻ ወይም በተራራ ላይ የማመስገን፤ የማክበር ፤የማምለክ በአል ነው – ኢሬቻ፤ የፀሎት ቀን ነው እሬቻ። ኢሬቻ ብዙ አይነት ቢሆንም ዋናዎቹ ሁለት ናቸው፡– ‹ኢሬቻ መልካ› እና ‹እሬቻ ቱሉ›።
‹ኢሬቻ መልካ› በውሃ ዳርቻ ክረምት እንደወጣ ይከበራል። ይበልጡን ምድርን በዝናብ ያጠገበውን ዋቃ በምስጋና የመዘከር በአል ነው። ‹እሬቻ ቱሉ› ደግሞ በተራራ ጫፍ ላይ በበጋው መሀል ይከበራል። ዝናቡ እንዳምናው በወቅቱ እንዲመጣ ዋቃ ይለመናል። ይበልጡን የፀሎት በአል ነው። ቢሆንም…ቡራኬው፤ምስጋናው፤ ፀሎቱ በሁለቱም ኢሬቻ አይቀርም። ለተራራው ወይም ለወንዙ አይሰገድም። እነሱን ለፈጠረ፤ አምላክ ነው የሚሰገደው። በእምነቱ ልምላሜ እና ውሃ የአምላክ መንፈስ ማደርያ፤ ንፁህ የአምልኮት ስፍራ ነው። ለፀሎት ምቹ እና ሰላማዊ ቦታ ነው። እናም በኢሬቻ መልካ በአል የተፈጥሮን ኡደት ሳያዛባ ያስቀጠለ ዋቃ ይመሰገናል። ዋቃ ይከበራል። ዋቅ ይመለካል።» [ምንጭ፡ ጦብያ መጽሔት፣ ቅጽ 5፣ ቁጥር 11፥ 1990 ዓ.ም.፤ ከገጽ 8-12]
ሎሬት ጸጋየ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በዓል መሆኑን አስረግጠው ጽፈዋል፡፡ እዚህ ላይ ኢሬቻ ባሕላዊ እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም የሚል ቢኖር ከሎሬቱ ሃሳብ ጋር መከራከር ይቻላል፡፡ ካስፈለገም እንደ አህመዲን ጀበል፣ ካሚል ሸምሱ ያሉ የኦሮሞ ኡስታዞች ወይም ሌሎች ቁርዓንን ያነበቡ ታላላቅ ሼኾች ቄጠማ ይዘው፣ ወንዝ ዳር ወርደው ኢሬቻን ሲያከብሩ ያሳዮን ?!… ሊደርጉት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በዓል እንደሆነ ስለሚያምኑ፡፡ ይሄን ቢያደርዱ በቁርዓን ህግ መሰረት እንደ ‹ከፈሩ› [እምነት እንደቀየሩ] ይቆጠራል፡፡ ባለፈው ዓመት Al-Furqan Islamic Center የተባለ ተቋም፤ ቁርዓንን እና ሐዲስን በማጣቀስ ኢስላም በዚህ መሰል የአምልኮ ስፍራ መገኘት የለበት በማለት የዳዕዋ መድረኩ ላይ መስበኩ ይታወሳል፡፡ ይህም ሆኖ፣ «መንግሥት» እና ሃይማኖት አንድ መሆናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ ያለፈው ዓመት አከባበር፣ ኢሬቻን መንግሥታዊ በዓል አስመስሎት ታይቷል፡፡
ፖለቲካዊው ኢሬቻ!
ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውን የኢሬቻን በዓል በተመለከተ የተሰሩ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው፣ ኢሬቻን ለማክበር የሚከበርበት አካባቢ ተራራ፣ ወራጅ ወንዝ አልያም ሐይቅ ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚህ ተለምዷዊ የበዓል አከባበር ጋር በተያያዘ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ማክበር መጀመሩ ከበዓሉ ይዘት ጋር ይጋጫል፡፡ ለበዓሉ አከባበር ግብዓት የሚሆኑ ወራጅ ወንዝ አለያም ሐይቅ በሌለበት ሁኔታ ውሳኔው ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ አንድምታ አላብሶታል፡፡ ተፈጥሯዊ ወንዝ አልያም ሐይቅ የግድ ለሚለው ለኢሬቻ በዓል፣ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ ለመናፈሻ የተሰራው ፓርክ ውስጥ ሰው ሰራሽ ኩሬ በመስራት በዓሉን ባለፈው ዓመት መከበሩ ይታወሳል፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ግልጽ ፖለቲካዊ ኢሬቻ ነው፡፡
በርግጥ ጉዳዮ በቀናነት ከታየ፦ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ እንዲከበር መታቀዱ አዲስ አበባን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ይበልጥ የሚያቆራኘው ባህላዊ ገመድ ይሆናል፡፡ የዋቄ ፈታ አማኞችም ሆነ ከእምነቱ ውጭ ያሉ በዓሉን ለማክበር ፍላጎት ያላቸው ወገኖች በጋራ ሲያከብሩ ሁነቱ የባህል ትውውቅ መድረክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ይህ የአደባባይ በዓል በአክራሪ ፖለቲከኞች ባይጠለፍ ኑሮ ለኢኮኖሚያዊ ትስስሩ የበለጠ መሰረት የመጣል ዕድል ነበረው፡፡ በተጨማሪም በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን ዘረኝነት ለማንበር የታሰበውን በመበጣጠስ አካባቢያዊ ጥምረትን ሊፈጥር የሚችልበት ዕድል ነበረው፡፡ ‘መጡ ደግሞ’ ከሚል የሕዝብ መነጠል ይልቅ እንደ ጋራ ፌስቲቫል የሚታይበትን ዕድል በእብሪታቸው የተነሳ አምክነውታል።
ኢሬቻን የዋቄ ፈታ ባህላዊ ሃይማኖት ተከታዮችና ከሃይማኖቱ ውጭ ያሉ ዜጎች ማክበራቸው ለእርስ በርስ ትውውቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም በዓሉ በኦሮሞ አክራሪ ብሄረተኞች ተጠልፏል፡፡ ይህ ነው የመምከኑ ምስጥር! ለአዲስ አበቤና ለአካባቢው ማህበረሰብ ግንኙነት ከመጥቀም አልፎ ለሀገራዊ የቱሪስት ፍሰትም አስተዋፅኦ ቢኖረውም ትርክቱ አደገኛ የፖለቲካ ካርድ የተመዘዘበት በመሆኑ፣ “The መጡ syndrome” አዲስ አበቤዎች ላይ አነብሯል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ኤሬቻን ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ የተደረገው ጥረት፣ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ኃላ ቀርነትን ያመላክታል፡፡ ‹‹ከመቶ ሃምሳ ዓመት በኃላ ኤሬቻ አዲስ አበባ ላይ ተከበረ›› የሚለው ተደጋጋሚ መግለጫ፣ ክህደት ከወለደው የታሪክ አረዳድ የሚመነጭ ፖለቲካዊ እብሪት ነው፡፡ አመታትን ወደ ኃላ እየቆጠሩ ታሪክ የማጦዝ ፖለቲካ በዶ/ር ዐቢይ ፖርቲ ውስጥ አለመቅረቱን ይመሰክራል፡፡ ‹ነፍጠኞች በሰበሩን ቦታ ሰበርናቸው› የሚለው የአክቲቪስት ሽመልስ ንግግር የኦሮሞ ፖለቲካ በታሪክ እውራን እና በፋሽስቶች እየተመራ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስክርነት የሰጠ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በ‹በራራ› (ቀዳሚት አዲስ አበባ) ታሪክ ውስጥ፡– ማን ‹ወራሪ›፤ ማን ‹ተወራሪ› እንደሆነ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ለአክራሪው ኃይል ታሪክ ሰፈር መሄዱ ባያዋጣውም፣ ፋሽስታዊ ባህሪውን በአደባባይ አስረግጧል፡፡ ‹‹ሆራ ፊንፊኔ›› የሚለው አዲስ ተረት ተረት ከአዲስ አበባ የቀደመ ታሪክ ጋር አንዳች ተዛምዶ የለውም፡፡ አለ የሚል ካለ በሰነድ የተደገፈ ታሪክ ያምጠና ይሞግት፡፡ በታሪክ እውራን ፋሽስታዊ ፖለቲካ ሀገር አይገነባም፡፡
አጀንዳውን ከመንግሥታዊ ተጠያቂነት አኳያ ከተመለከትነው፣ አሁን ባለው አወቃቀር የኢሬቻ በአል በአዲስ አበባ እንዲከበር ጨፌ ኦሮምያ የአዲስ አበባን ም/ቤት ሊጠይቅ ይችላል እንጂ ሊወስን አይችልም ነበር፤ ባለፈው ዓመት የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ጨፌ ወሰነ ታከለ ዑማ አስፈጸመ፡፡ ዘንድሮም በዛው ቅኝት ላይ እንደተጣዱ ነው፡፡ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ጥያቄውን ለፌደራል መንግስት ሊያቀርብ ይችላል እንጅ በራሱ መወሰን እንደማይችል መዋቅራዊ ክርክር ማቅረብ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ የኦሮሞ ገዥዎች በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የመጠቅለል ውሳኔ ስለመወሰናቸው ከአካሄዳቸው መረዳት ይቻላል፡፡ የዘንድሮው ኢሬቻ ደግሞ የተለዬ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሳምንቱን ሙሉ ለማክበር ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ አዳነች አበቤ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥታለች።
ይህ የማን አለብኝነት ፖለቲካዊ አካሄድ፣ በቀጣይ ጊዜያት መንገዱ የእልቂት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከፊት ለፊት ሊመጣ የሚችለውን የሕዝብ አመጽ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ማስተዳደር ይኖርባታል ለሚለው የአዲስ አበቤዎች ጥያቄ፤ ይህ የደፍጣጭነት ፖለቲካ እርስ በርስ ደም ከማፈሰስ በዘለለ ‹ረብ› የለውም፡፡ ግብ፣ ስልትና ስትራቴጅ ተቀምጦለት እየተሰራ ያለ የእብሪት መንገድ በግብር የሲሲሊ ማፍያዎችን ያስንቃል፡፡ ከፋሽስት ፖለቲካ አራማጆቹ አሁናዊ አቋም አኳያ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ የመጭው ጊዜ ቁልፍ ስጋት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሕዝብን የናቀ አገዛዝ መጨረሻው ምን እንደሆነ አፍሪቃ በቂ ትምህርት ቤት ብትሆንም የኦሮሞ ልሂቃን ለመማር ዝግጁ አይደሉም፡፡ በ’ማሳመን’ እና በ’ማደናገር’ ፖለቲካ፣ ቅራኔን የሚያረግቡ መስሏቸዋል፡፡ ይህ የከተማዋን ጸባይ ካለማወቅ የሚመንጭ እብሪት ከነሱ አልፎ ለሕዝብ እንዳይተርፍ ያሰጋል፡፡
ማስገንዘቢያ፤
የዘንድሮው ኢሬቻ ፖለቲካዊ በዓል ሆኖ ለሁለተኛ ጊዜ በመጭው እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ ሊከበር ከመሆኑ አኳያ፤ በብዙ ቅራኔ ውስጥ ያለው አዲስ አበቤ የገዛ ከተማውን ሠላምና ደህንነት የመጠበቁ ኃላፊነት የመላ አዲስ አበቤዎች ሊሆን ይገባል!! መንግሥትን ብቻ አምኖ መቀመጥ የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ የሠላም ዋስትናችን ያለው በእጃችን ነው፡፡
(ከአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ደኀንነት ስጋት አኳያ፤ ‹ምን መደረግ አለበት› በሚለው ነጥብ ዙሪያ መፍትኄ የምላቸውን ከሰሞኑ ይዤ እመለሳለሁ፤ በጽሁፉ ዙሪያ ሀሳብም ስድብም ይቻላል፤ አፀፋው ሳይዘነጋ!)
መረጃ .ካም