September 30, 2020

በደቡብ ክልል የሚገኙ አምስት የዞንና አንድ የልዩ ወረዳ መስተዳድሮች የጋራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመመስረት ተስማሙ። ከደቡብ ክልል በመነጠል የጋራ ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት ውሳኔ ያሳለፉት የካፋ፣ የሸካ፣ የዳውሮ፣ የቤንች ሸኮ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ መስተዳድሮች ናቸው። መስተዳድሮቹ የጋራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት የየዞን ምክር ቤቶቻቸውን አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት ነው።

ውሳኔውን ካሳለፉት ዞኖች አንዱ የሆነው የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ት ልክየለሽ ኬቶ «ውሳኔው የዞኑ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት ሲያቀርቡት ለቆዩት የልማትና የፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄና ምላሽ የሚሰጥ ነው» ሲሉ ለዶቼ ቬለ /DW/ በስልክ ገልፀዋል። ዋና አፈጉባኤዋ አያይዘውም፤ «የብሔራዊ ክልላላዊ መንግሥት ምስረታው ከማንነት ጥያቄ ባሻገር ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት ምላሽ ለመስጠት ያስችላል። በተለይም ሕዝቡ አቤቱታዎችን ለማቅረብ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ወደ ደቡብ ክልል ሲያደርግ የነበረውን ጉዞ ያስቀርለታል» ብለዋል።

የዞንና የወረዳ መስተዳድሮቹ የጋራ ክልላዊ መንግሥት ለመመስረት ባሳለፉት ውሳኔ ዙሪያ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ። ዶቼ ቬለ /DW/ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሕግና የሥነ መንግሥት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሙሉጌታ ባካሎ በመስተዳድሮቹ ውሳኔ ተስፋም ስጋትም እንዳላቸው ይናገራሉ። አካባቢዎቹ በተለምዶ «ዳር አገር» በመባል የሚታወቁና የመሠረተ ልማት ችግር ያለባቸው ናቸው የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ ይህንን ችግር ለመፈታት ቅርበት ያለው መስተዳድር መመስረቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ አደረጃጀቱ ውሎ አድሮ ሌላ ጥያቄ እንዳይፈጥር በውሳኔው የሕዝብ ሥምምነት ሥለመኖሩ ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው ዶክተር ሙሉጌታ የተናገሩት። በደቡብ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት 13 የዞን መስተዳድሮች በክልል ለመደራጀት የሚያስችላቸው ውሳኔ በማሳለፍ ጥያቄዎቻቸውን ለክልሉ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸውን ዶቼ ቬለ /DW/ ከሀዋሳ ጠቅሷል።