October 2, 202

(ኢዜአ) ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥሉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ሕገ-መንግስታዊ መሰረት እንዳለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ። ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች መደበኛ ስራቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።

በፌዴራል ደረጃ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት መራዘሙ ይታወቃል።ይሁን እንጂ የተወሰኑ ቡድኖች በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በተለያየ መልኩ ሕገ-መንግስታዊ ጥሰት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ኢዜአ ይህን ጉዳይ ጨምሮ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ዙሪያ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ጋር ቆይታ አድርጓል።አፈ-ጉባኤው እንደሚሉት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-መንግስታዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ምርጫውን አራዝሟል።ሆኖም ለሕገ-መንግስቱ ተገዥ ያልሆኑና ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ሕዝቡን የማወናበድ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።ከዚህ ውስጥ አንዱ የትግራይ ክልል መሆኑን የገለጹት አቶ አደም ፋራህ ”በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ክልሉ ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።

ምርጫ ማስፈጸም የምርጫ ቦርድ ስራ ሆኖ ሳለ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መልኩ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም፤ አግላይ በሆነ መንገድ ምርጫ አካሂዷል ነው ያሉት።አካሄዱ በግልጽ የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ የሚጥስና ክልሉም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ እንደጣለ ይቆጠራል ብለዋል።ክልሉ ይህን ድርጊት ፈጽሞ በመገኘቱ ሕገ-መንግስታዊ እርምጃ ሊያስወስድ የሚችል በቂ የሕገ-መንግስት መሰረት እንዳለ አመልክተዋል።

ከነዚህ እርምጃዎች መካከል ሕግ አውጪውንና ሕግ አስፈጻሚውን ማገድ የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ አካሄድ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።ቀጥሎ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግስት ማቋቋምና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በማሰማራት ሕገ-መንግስቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሌላው መሆኑን ይገልጻሉ።

አፈ-ጉባኤው አያይዘውም ከዚህ በኋላ ሕዝቡም ሆነ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለሚነዙ ቡድኖች ጆሯቸውን ሳይሰጡ መደበኛ ስራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል።እነዚህ ቡድኖች ለጥፋት መንገዳቸው ያመቻቸው ዘንድ በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉም ይገልጻሉ።በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶች እንደተለመደው አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠርና የመከታተል ስራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

”ይህ ቡድን አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታውን አሃዳዊ የማስመሰል እንቅስቃሴ ይስተዋልበታል” የሚሉት አፈ ጉባኤው ”እንደውም አሃዳዊነት ከለውጡ በፊት ነበር” ብለዋል።ከለውጡ በፊት በየአካባቢው ሕገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሰፋፊ ክፍተቶች ይታዩ ነበር ብለዋል።በየክልሉ የሞግዚት አስተዳደሮች ተመድበው ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አደም ”ከለውጡ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ለውጦች እየታዩ ነው” ብለዋል።

አቶ አደም በአንዳንድ አካባቢዎች የተዛቡ ትርክቶችን መነሻ ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቦችን እያጋጩ መሆኑንም ይገልጻሉ።እነዚህም ማንነትን፣ ብሔርንና ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሕዝቦች ወንድማማችነት ላይ የራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉም ብለዋል። በየአካባቢው ያሉ ምክር ቤቶችም ነገሮችን ከየአካባቢያቸው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ሰፋ አድርገው ማየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።የአቶ አደም ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።