=========

ለነገሩ ቀልቀሎ ስልቻ ነው አዲሱ ስም የቀየረው ኢሕአዴግ እረቀቅም ከበድም ያሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ይዞ ብቅ ያለ ይመስላል። አንዳንድ ጅል ከማህላቸው አልጠፉም እና የፕሮጀክቶቻቸውን መመሪያ ቀድመው ነግረውናል። ምናልባት ትዝ ይላችሁ ይሆናል የለማ መገርሳ የ 2010 የዝግ ስብሰባ እና አዲስ አበባን የመጠቅለሉን ሀሳብ ገላጭ ንግግር በቀጣይም ሌሎች እና የዛሬ አመት በእሬቻ ላይ የሽመልስ ነፍጠኛውን “ሰብረነዋል” የሚለው መሪ ንግግር እና ያን በተናገረ ሦስተኛው ወር ማለት ነው የዝግ ስብሰባ ላይ ያመኑትን አሳምነን ያላመኑትን ልክ አግብተን ተመልሰናል የምትለዋ ሌላዋ Revelation አካሄድ አረማመዳቸውን አስረጅ ምስሎች ነበሩ።

ዛሬ የጎጃም መንገድ መዘጋት እና የእሬቻ ዝግጅት ሌላው ሀገራችን ከአንድ የዘር አንባ ገነንነት ወደሌላ በተገላበጠች ቁጥር የሕዝብ እንግልት፣ እስር እና ሞት ቀጠይነት በባሰ የሚመጣ መሆኑን ጠቋሚ ይመስላል።

በበኩሌ ከባለግዜወች አንደበት እዚህም እዚያም ከተነገሩት ለቃቅሜ የዛሬው የሚኒሊክን ሀውልት የአባገዳ ሰንደቅ አላማ ማልበስ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድል አድርጎኛል። በእርግጥ ሚኒሊክን እኛም እኮ የአፍሪካ አባት እንዳልን የምናከብረው ታላቅ መሪ እንደነበር ሁሉ ጡት ቆራጭ ብለው የሚያብጠለጥሉት የቀኝ ኋላ ተሽከርክረው 360 ዲግሪ ማለት ነው የእኛ ነው ለማለት ሲነሱ እሰየው ትክክል አበጃችሁ መሆንም የነበረበት እንደዚህ ነው (ጎሽ) ማለት አማረኝ። ግን አንድ ነገር ደግሞ ብልጭ አለብኝ። የሚኒሊክን ሀውልት የአባ ገዳ ባንዲራ አልብሶ ሌላውን ወገን እሬቻ ሳያልፍ መናገሻ ከተማችን አትገባም ማለት ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

ሕብረተሰብን በሀይ መቀየር Revolution ነው እናም የአብዮታዊ ነውጥ ማቆሚያ ደግሞ አይታወቅም እናም የዛሬወቹ ኢትዮጵያን በኦሮሞ አምሳል እንፈጥራለን ብለው ሲነሱ ብዙ የማያውቁት እንደሚገጥማቸው ሊረዱት ይገባል። ኢትዮጵያን እንዳለች ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ አፍርሰን እንስራ የሚለው ምንም እንኳን ጨርሳ ትጥፋ ከሚሉት ቢሻልም ብዙ ጣጣ ያዘለ ፕሮጀክት እለዋለሁ። ለምን? መጀመሪያ እንደገና ለመስራት እና የአባገዳ ስርአት ለመፍጠር ለብዙ መቶወች – ሽሆቹ አመታት ቢቀሩ እንኳን በአዝጋሚ ለውጥ የተሰራ ኢትዮጵያዊ የአንድነት ድር እና ማግ እጅግ ጥልፍልፍ መሆኑ እንዴውም ከዚያው ከኦሮሚያ ደጃፍ ሳያልፉ ጠልፎ የሚጥል እንደሆነ አሁን እያየን ነው። ለምሳሌ የጉራጌ ክልል ጥያቄ (በበኩሌ እደግፋለሁ) ቀጥሎም የወላይታ የጋሞ እና ሌሎች በአንድነት እያነሱ ያለው የክልል ጥያቄ (ይህንም እደግፋለሁ) ከማን አንሸ ሳይሆን legitimate ነው። ምክንያቱም ግልጽ ነው። በተራበ ለመዋጥ ተኝቶ የሚጠብቅ ፍጡር አይኖርም። የኦሮሚያ መሪወች ኢትዮጵያን በእኛ መልክ እንስራ ሲሉ ሌሎችን ውጠን ሰልቅጠን እኛ እናድርጋቸው ማለት ነው። ይህን ነው Revolution ነው ያልሁት። እናም በአመጽ የሌላን ማንነት ማጥፋት የማይሞከር ነው።

በአለም ላይ ብዙ ቋንቋወች ባህሎች አሉ ዛሬ የምእራባውያንን ባሕል ብዙ የአለም ክፍል ሳይገደድ እየለበሰው ያለ በሀይል ስለጫኑበት አይደለም። ቋንቋቸውን እየተናገረ ያለው ተናገር ብለው በአመጽ ስላስገደዱት አይደለም። እንዲያውም ብዙ የተማሩ ሲሰሳቱ የሚታየው እንግሊዝኛ የማይሰማ እና የማይናገር አዋቂ እና የተማረ አልመስል ሲላቸው ስናይ ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙ ይግባን። አንዳንድ ሰወች Critical theory school of thought ወይንም የግራ ዝንባሌ ያላቸው የባሕል ቅኝ ግዛት ወይንም ወረራ ይሉታል። ይህን የሚጻረሩ ቀኛውያን ደግሞ ቅናት ብለውት ያርፋሉ። ለማነኛውም እንግሊዝኛን ሰው የመረጠው እና የእውቀት መመዘኛ እስከማድረግ የተሳሳተ ሀሳብ ያስገባው በኃይል ስለተጫነ ሳይሆን በፍላጎት እና በብዙሀን የአለም ነጋዴወች፣ ምሁራን፣ ጸሀፍያን ወዘተ ስለተወደደ ነው። አማርኛ ላይ ያለው ቅናትም ከዚህ የዘለለ አይደለም። የኦሮሞ ጽንፈኞች የተራቀቀ አማርኛ እየጻፉ በዚያው ጽሁፋቸው አክ እንትፍ ብለው ሲያቆሽሹት እናያለን። እንዴውም ከተባለ የስነልቦና ቅኝ ተገዥወች መባል ያለባቸው እነዚያ ናቸው።

ባጭሩ እና ይህችን ሽሙጥ ብጤ ነገሬን ለመጠቅለል ሚኒሊክ ሰራዊቱን መርቶ የዘመተው እና የጀኔራል ባራቴሪን ሰራዊት ድል ያደረገው በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ነው። ድል አድራጊው ሰራዊት ፈረሶቹን ሳይቀር ያለበሰውም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ነበር።፡የአባ ገዳ ሰንደቅ አላማ አለመልበሱን ግን በእርግጥ አሁንም መናገር ይገባል ለማለት ነው። ግን ሚኒሊክ የኛ (ኬኛ) ከተባለም እሰየው ግን እርሱ ያደረገውን ሁኑ እንጅ አፍርሰን እንስራ አትበሉ ነው ዋናው አላማ። ኢትዮጵያ አንድነቷ ሰላሟ ከተጠበቀ። ዜጎቿ በሰላም ውለው ከገቡ። ፖለቲካ ሳይሆን ስለኑሮ እና ስለስራ እንዲያስቡ ከሆነ። ተማሪወቿ ስለ ግኝት እሚበረታቱ ከሆነ እንኳን እኛን ሌሎች እኛን ሊመስሉ ይሽቀዳደማሉ። እናፍርስ ሳይሆን ምን እንጨምር ከተባለ አሁን የሚነገረው ቋንቋ ዳብሮ እና የሁሉም ሆኖ እንዴውም ልክ እንደእንግሊዝኛ አለም ሊሽቀዳደምበት ይችላል።

ደግ ደጉን እናስብ ኢሬቻውም የሁሉም ይሁን ያሻው በአሉን ይዝለልበት እና ያኔ ኦሮሙማ መሆኑ ይቀርና ኢትዮጵያ ይሆናል እጅ አፍርሶ መስራትን ምን አመጣው?

Adios!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

88